Friday, 7 December 2018

ዋላ


እንዴት ''ዋላ''ችሁ
የጌታ ኢየሱስ ሰላምና ፍቅር በያለንበት ይብዛልን!!! 

ተጠማች ነፍሴ ናፍቃህ እንደ ዋላ
የለኝም ዋስትና መድን ካንተ ሌላ
የሕይወት  ውሃዬ ፍሰስ በልቤ ላይ
ኢየሱስ ድምፅህን አሰማኝ ከሰማይ
                 
            ዋላ በአማርኛ ዲክሽነሪ ላይ እንደተገለፀው ከዱር አራዊት የምትመደብ፣ በበረሀ የምትኖር የፍየል ወገን ነች። መፅሐፍ ቅዳስ ዋላን በእንዲህ መልኩ ያነሳታል በመዝሙር 41፥1-2 

'' ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ? ''

             ዋላ እንደልቧ ሲጠማት በቀላሉ ውሃ ልታገኝ የማትችል የሁልጊዜ ተጠሚ ስትሆን ጥሟን ለማስታገስ ሌት ከቀን ወደ ምንጭ  ትዳክራለች። ዋላ ውሃ የምታገኘው ከአዳኟ ተደብቃና ካያትም ሸሽታ ብዙ ዋጋ ከፍላ ነው። አብዛኛውን ኑሮዋንም የምታደርገው በምንጩ ዙሪያ ነው።

             ዋላ ለስጋ ጥም እርካታ ውሃ ያስፈልጋታል እኛ ግን ጠጥተን ወደማንጠማበት የእርካታ ጥግ እንዳንደርስ በብዙ መሰናክሎች ተወጥረን እንገኛለን። ጌታችን  መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰማሪያዋ ሴት እንደነገራት

 "፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። "
(የዮሐንስ ወንጌል 4: 14)። ወደዚህ ዘላለማዊ እርካታ እንዳንቀርብ ጠላት ዲያብሎስ ብዙ ይታገላል። ዋላ በራሷ ጥረት ከአዳኟ ታመልጣለች እኛ ግን አሳላፊው ጌታ ያለአንዳች ያሳልፈናል። አንዳንዴ የእርሱ ጥበቃ በዝቶም እኛ ግን ራሳችን በራሳችን ላይ እንቅፋት እስከመሆን እንደርሳለን። 
       
             እኛም ከዋላ ብዙ የምንማር ይመስለኛል። እንደዋላ መውጣት መውረድ ሳይኖርብን ጌታ በሰራው ስራ ዘላለማዊ ጥጋብ ዘንቦልናል። እርሱ በመስቀል ላይ ተጠማው ብሎ መራራውን ሆምጣጤ ጠጥቶ ለእኛ ግን አንዴ ጣፍጦን ጠጥተነው ዘላለም እረክተን እንድንኖር የሚያስችለንን ፀጋ ሰጥቶናል ስሙ ይቀደስ። ታዲያ በዚህ እርካታ ውስጥ ሆነን የጌታን ድምፅ እንድንሰማ የማይወደውና የማይፈልገው ጠላት እንደሚያገሳ አንበሳ ዙሪያችን ይዞራል። ዋላም በቀላሉ ጠላት ሊይዛት የሚችለው ጥሟን ከምታገኝበት ከምንጩ ስፍራ ሲሆን እኛንም ከዘላለማዊ ምንጭ እንዳንገናኝ ከእርካታችን ትይዩ ሆኖ ይጠብቀናል። ከምናውቀውም ከማናውቀውም ጠላት የሚጠብቅ የማይተኛ፣ የማያንቀላፋው አምላካችን ክብርና ምስጋና አምልኮትና ውዳሴ ለእርሱ ይሁንለት።

               እግዚአብሔርን በተጠማነው መጠን እንረካለን። ትናንት ከነበረን እግዚአብሔርን መጠማት ዛሬ ላይ በይበልጥ ሊኖረን ይገባል። ነገ ደግሞ ከዛሬ። እግዚአብሔርን የምናወቀው ልናውቀው በፈለግነው መጠን ነው። ባለን አቅም ቃሉን እየታጠቅን፣ ለቃሉም እየታዘዝን፣ በፀሎትም እየተጋን እንድንኖር የእግዚአብሔር ጸጋ ይርዳን። በሚያስፈልጋችሁም  ጊዜ የሚረዳ የእግዚአብሔር ጸጋ አለ ተብሎም እንደተፃፈ በነገሮች ሁሉ ማድረግንም መፈለግንም በእኛ ላይ  የሚሰራ አምላክ ያስችለን።

11 comments:

  1. ኢየሱሲ ፀጋውን ያብዛልህ

    ReplyDelete
  2. ጌታ ይባርክህ

    ReplyDelete
  3. የጌታ ጸጋ ይብዛልህ ግን ጥቅሱ መዝሙር 41 ምዕራፍ 42 ላይ ነው ቃሉ የሚገኘው ይስተካከል

    ReplyDelete
  4. waw God bless you, ጸጋው ይብዛልህ

    ReplyDelete
  5. God bless you 🙏

    ReplyDelete
  6. ዋው
    ተባረክ ይብዛልህ

    ReplyDelete
  7. ዋላ ውሃ ለመጠጣት ብቻ ነው የምትጠቀመው plz melesulgn

    ReplyDelete
  8. ተባረክክክክልኝ

    ReplyDelete