#ማሳሰቢያ:- የእግዚአብሔርን ክብር መግለጥ ማለት የቅዳሳንን ክብር ማቅለል አይደለም። ቀድሞውኑ የሰው ልጅ ምን ክብር አለውና የቅዱሳን ክብር እግዚአብሔር አይደለምን?
=}} (ዮሐንስ ወንጌል 2፥1-2)
" በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። "
በዚህ ምንባብ ሶስት ሀሳቦች ላይ ጥያቄ በመመለስ እናያለን።
ሀ) ድርጊቱ የተፈፀመው የት ነው?
ቃና ከናዝሬት ሰባት ኪሎ ሜትር ርቃ በሰሜን እስራኤል የምትገኝ ትንሽ ከተማ ነች። ቃና ዘገሊላ የተባለችው ሌላ ቃና የሚባል ስፍራ ስላለ ለመለየት ሲባል ነው። ይህ ማለት የኮተኬ ካራና የአየር ጤና ካራ እንደማለት ነው። ገሊላ ደግሞ ጌታ ያደገበት ስፍራ ወይም አቅራቢያ መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። ከዚህም በመነሳት ለሰርግ ጥሪው የቅርብ ሰው እንደሆነ መረዳት እንችላለን። እናቱ ድንግል ማርያም በዛ አካባቢ የምትታወቅና ለሰርጉ ቤተ ሰዎች የቅርብ ሰው እንደሆነች ታሪኩ ያሳያል። ይህን ማወቅ ታሪኩን በትክክል እንድንረዳ ይጠቅመናል። በእርግጥ ቦታውን ማወቅ በራሱ የታሪኩን አግባብነት እንድናውቅ ካልሆነ በቀር በራሱ መንፈሳዊ ጉዳይ (Theologies) መሆን አይችልም። Theology ያለው ምልክቱ ላይ ነው።
ለ) ቀኑ መች ነው?
በሶስተኛው ቀን የሚለው ብዙ አስተምህሮዎች እንደሚያመለክቱት ከትርጓሜ መፅሐፍ ጨምሮ ጌታ ከተጠመቀበት ቀን ጀምሮ እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን ጌታ ከተጠመቀ በኃላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በሲና በረሃ እንዳሳለፈና ከዛ ወዲህ ደግሞ ፊሊጶስ ናትናኤልን ወደ ኢየሱስ እስኪጠራበት ድረስ ሁለት በነገው የሚሉ ቀኖች እናነባለን (ዮሐ 1፥29 1፥35 ተመልከቱ)። በአጠቃላይ አርባ ሁለት ቀኖች በመኖራቸው ከተጠመቀ በኃላ ባለው በሶስተኛወ ቀን ነው ማለት እንዳንችል ይገድቡናል። ታዲያ ይህ ሶስተኛ ቀን የሚያመለክተው መች ነው የምትሉ ከሆነ ናትናኤል ከተጠራ ከቁጥር 44 ላይ ከተፃፈው በነገው በኃላ እንደሆነ ግን ጥርጥር የለውም። ጌታ ናትናኤልን ገና ከዚህ የሚበልጥ ታያለህ ካለው በኃላ ባለው በሶስተኛው ቀን ማለት ነው።
ሐ) የሰርጉ ዓይነት ምን ዐይነት ነበር?
በእስራኤል ባህል የሰርግ ስነ ስርአት ለቀናቶች የሚቆይ ሲሆን ብዙ ማህበረሰብ የሚሳተፍበት ነው። በዚህም ምክንያት የሰርጉ ድምቀት በሚሳተፉት ሰዎች ላይ የተመሰረተ ነው። የተሳካ ከሆነ የሁሉም ተሳታፊ ዘመድ አዝማዝ ክብር ሲሆን በአንፃሩም ሰርጉ ቢበላሽ ወይም ቢደበዝዝ ውርደቱ፣ ሀፍረቱና ተጠያቂነቱ በሰርጉ ለተሳተፉ ሁሉ እንጂ ለባለ ሰርጉ ብቻ አይደለም። የሰርጉን ቦታ እንዳየነው የጌታ እናት ማርያም ሳትጠራ እንደሄደች የምናውቀው ለሰርጉ ቤት የቅርብ ሰው እንደሆነች ስለሚያመለክት ነው። ደግሞ ሰርግ ስላለ ብቻ አይኬድም ጥሪ ወይም ዝምድና ያስፈልጋልና።
'' የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች '' ሲል ታዳሚ ከመሄዱ በፊት በዛ ስለመኖሩዋን ያሳያል። ይህ ማለት በጥሪ ሳይሆን በቅርበት ወይም በአገልግሎት እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ነው። የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል የሚለው ጥያቄ የሚነግረን ይህንኑ ነው። የቅርብ ተቆርቋሪ እንደነበረችና ድንግል ማርያምም በሰርጉ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት ጌታን እንደጠየቀች ጥርጥር የለውም።
"ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። "
መታደም ከላይ እንደገለፅኩት መጠራትን ያሳያል። የእንግሊዝኛውም መጽሀፍ ቅዱስ የሚነግረንም ይህን ነው (Jesus was called ይላል)። ጌታ በዚህ ጊዜ ሰላሳ ዓመት ስለሞላውና ራሱን ችሎ አገልግሎት ስለጀመረ እንዲሁም ደቀመዛሙርት ስላፈራ ከእናቱ ተለይቶ ብቻውን መጠራት ጀምሯል።
#ምልከታ:-
ብዙ አስተምህሮዎች ጌታ በሰርጉ የተገኘበት ምክንያት ነው የሚሉት
1) ማህበራዊ ጉዳይ (ዝምድና) ስለነበረው ነው የሚሉ አሉ
2) ሰርግ ሊባርክ የሚሉ አሉ
3) ክብሩን ሊገልጥ ነው።
የመጀመሪያውና ቀጥሎ ያሉው ሁለቱም ጥያቄ ያስነሳሉ ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ጌታ የትም ቦታ ለማህበራዊ ግንኙነቶች ተልእኮ ሲያደርግ አናይም ከመለኮታዊ አጀንዳ ውጪ። ሲቀጥል ሰርግ በተፈጥሮው የተባረከ ስለሆነ የትኛውም ጋብቻ ከርኩሰትነት ወደ ቅዱስነት የሚለወጥ አይደለም (Declaration ግን ሊኖር ይችላል)። ዋናው ነገር የሰርጉ ጥሪ ምልክት በማድረግ መለኮታዊ አጀንዳውን ሊፈፅምና ክብሩን ሊገልጥ ምክንያት ሆኖል። ስለሆነም ጥሪው ጌታ የሄደበትን ጉዳይ ያገናዘበ ሳይሆን ለቤተሰቡ ቅርብ በመሆኑ ነው። ምንም እንኳ ለሰርግ ቢጠራም ጌታ የተንቀሳቀሰው የአባቱን ፍቃድ ለመፈፀም ነው።
=}} (የዮሐንስ ወንጌል 2፥3)
" የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። "
እዚህ ክፍል ላይ ብዙዎችን ሲያጨቃጭቅ የኖሩ ጥያቄዎች አሉ።
1) የጌታ እናት ድንግል ማርያም የወይን ጠጅ ማለቁን እንዴን አወቀች?
2) ለምን ልጅዋን ጠየቀችው?
3) ወሃውን ወደ ወይን ይቀየራል ብላ አምና ነው ወይስ መፍትሄ ይሰጣል ብላ አስባ ነው የጠየቀችው?
እነዚህን ጥያቄዎች በታሪኩ አግባብ ከታዩ ለመመለስ ቀላል ነው። ግን በሃይማኖተኝነት ግለት (ግብዝነት) እዚህ ታሪክ ውስጥ የተደረጉትን በሙሉ መንፈሳዊ አድርጎ በማሰብ ከሆነ የተዛባና ከእግዚአብሔር ሀሳብና እቀድ ውጪ ያደርገናል።
ድንግል ማርያም የወይን ጠጁ እንዳለቀ ለማወቅ በቦታው መሆኗ በቂ ነው። እዛ በመሆንና በማየት የመጣ እውቀት ስለሆነ። መቼም እንዳሁኑ ዘመን አባባል ሳሎን ቅጭ ብላ ጓዳ ያለውን የጠጅ ጋን በመንፈስ አይታው ነው አንልም። ይገርማል የሰርጉን ቤት ጓዳ እንደሞላሽ የእኛንም ቤት ጓዳ ጎብኚ የሚሉ እጅግ ብዙ አሉና። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ድንግል ማርያም ሁሉንም ነገር ታውቃለች ብለው ያምናሉ ይህ ደግሞ ስህተት ከመሆን ባለፈ በእግዚአብሔር ህልውና ላይ አመፃን ማድረግ ነው። ለዚህ ማመሳከሪያ ጌታ ኢየሱስ በአስራ ሁለት ዓመቱ በጠፋባቸው ጊዜ ዮሴፍና ማርያም ለሶስት ቀን በፍለጋ ባለፉ ነበር።
ልጅዋን የጠየቀችበት ምክንያት ድንግል ማርያም የእምነት ሰው ስለሆነች ነው። መፅሐፍም እንደሚል በልቧ ትጠብቀው እንደነበር ይናገራል። ይህ ደግሞ በልጇ ላይ ያላትን እምነት ያሳያል። ከጽንሰቱ ብስራት ጀምሮ የተከናወነውን ነገር ሁሉ ታውቃለች። የልጇን ማንነት በሚገባ የተነረዳች ከመሆኑም አንፃር የፈለገውን አድርጎም ቢሆን መፍትኤ ይሰጣል ብላ እርግጠኛ ስለነበረች ልጇን ጠይቃለች። '' ይኩነኒ በከመ ትበሌኒ '' ይሁን ይደረግልኝ ማለቷ ብቻ እኮ ስለ እምነቷ ማውራት ከበቂ በላይ ነው።
ጌታ ውሃውን ወደ ወይን ይቀይራል ብላ specifically እውቀት አላት ማለት አንችልም ነገር ግን ቀድሜ እንዳልኩት የልጇን ማንነት ላይ ባለ እምነት ግን ጠይቃለች። ማወቅ ያለብን ጉዳይ ማርያም ይህን ስትል ከማህበራዊ ግዴታን ወይም ከማህበራዊ ችግር ከፍታት የቀረበ ከመሆኑ ባሻገር ልንወስደው አንችልም። ምንም እንኳ እሷ ብትጠይቀውም ጌታ የእሷን ጥያቄ በእሱ መለኮታዊ እቅድ ውስጥ አስገብቶ ምልክት አድርጓል።
ይቀጥላል.............................
No comments:
Post a Comment