'' ስብሀት ለእግዚአብሔር ወሰማያት ወሰላም ወምድር ስምረቱ ለሰው። ''
ይህን መዝሙር ብዙ ጊዜ ዘምረነው እናውቃለን ነገር ግን የተዘመረበትን ዓላማው አስተውለነዋል ብዬ አላምንም። ይህ ምስጋና መላእክት ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በመወለዱ የተነሳ ያቀረቡት ሰማይና ምድር የተገናኙበት ምስጋና ነው። በጌታ የማዳን ስራ በመደነቅ በጠባብ ደረት ተወስኖ ሰው ሆኖ ሲያዩት እልፍ ሰራዊት ወደ ምድር መጡና የሰማይና ምድር መጋጠምን አበሰሩ። በእርሱ መሰላልነት ይወጡና ይገቡ ጀመር።
ይህ አስቀድሞ ያዕቆብ መላእክት ሲመላለሱበት ያየው መሰላል እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
'' ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ። ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፥ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ፤ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሣ፥ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ። ሕልምም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር። እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር። '' (ዘፍ 28፥10-13)
አዎ በምድር የተተከለ ወደ ሰማይ የደረሰ እንደ ኢየሱስ ያለ ማንም የለም። ኢየሱስ በመዋህለ ሥጋዌ ምድርን ከመርገጡ በፊት ገና ሳይፀነስ ለእናቱ ምሥራች ከተነገረበት ጊዜና ለዓለም በከፈለው ዋጋ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶ የሞትን ጣር በማጥፋት ድል አድርጎ ከተነሳ እንዲሁም ስፍራ ሊያዘግጅልን ወደ ግርማው ቀኝ በሄደበት እስከ ዕለተ እርገቱ ድረስ የመላእከት ወደ ምድር መውጣትና መግባት ይህን ያረጋግጣል። ማራናታችን ዳግም ሊወስደን ሲመጣም በአእላፍ መላእክት አጀብ እንደሆነም ሌላኛው ማረጋገጫ ነው።
ገና በግርግም ሳለ:-
"ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። " (ሉቃ 2፥13-14)የጌታ መወለድ ሰማይና ምድር የተገናኙበት ነው። ሁለቱንም የሚወክል በምድር ለምንኖር ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን መሰለ። ሰማይ ዙፋኑ የሆነው እርሱ በእግዚአብሔር መልክ የሚኖር ለዘመኑ መጀመሪያና ፍፃሜ የሌለው አልፋ ኦሜጋ ፊተኛውና ኋለኛው ሁሉን የፈጠረ የተባረከ አምላክ ነው። ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ።
ምድራዊያን ምድርን ብቻ ነው የነኩት ሊወክሉ የሚችሉት ሰማይ የለም። እግዚአብሔርም ሉአላዊ አምላክ ነውና ክብሩን ለሌላ በፍፁም አሳልፎ የሚሰጥ አይደለም። ሰማይን የሚወክል ከልጁ በቀር ሌላ አላዘጋጀልንም። መሰላል የተባለ ሁሉ ሰማይ አያደርስም። ኢየሱስ እውነተኛ መንገድ ነው። ለሰው ልጅ ሁሉ መሰማሪያ ቅጥር መሄጃ መንገዱ ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው።
" ኢየሱስም። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። " (ዮሐ 14፥6)
በትንሳኤ ጊዜ:-
መላእክት መወለዱን እንዳበሰሩት ሁሉ ትንሳኤውንም የተናገሩት እነርሱ ናቸው። ይህ መላእክት በጌታ ኢየሱስ ላይ ያላቸውን መመላለስ ያስረዳል። (ማቴ 28፥2-6)
በዕርገት ጊዜ:-
ጌታ የመጣበትን ዓላማ የሰውን ልጅ ከኃጡአት ባርነት ነፃ በማውጣት ወደ አባቱ ሲያርግ መላእክት ነበሩ። (ሐዋ 1፥10-11)
ያዕቆብ ያየው መሰላል የተባለው ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሆኑ እነዚህ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች ቢሆንም ጉዳዩን ግልፅ የሚያደርግልን ቃል አለ። እርሱም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ አንደበት የተናገረው ነው። ናትናኤልን አውቅሃለው በማለቱ ባሳየው እምነት የተነሳ ገና ብዙ ነገር ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ እንዳለው። ናትናኤል ሊያየው ከሚገባ የሚበልጥ ነገር አንዱ የኢየሱስን አማናዊ መሰላልነት ነው። ለዚህ ነው ጌታ
" እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው። "(ዮሐ 1፥52)
'' የሰው ልጅ '' ደግሞ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን ኢየሱስን ለማመልከት እንደሆነ በወንጌላቱ በተደጋጋሚ ተነግረዋል። (እነዚህን ጥቅሶች ተመልከቱ ማቴ 16፥13 ሉቃ 2፥48 )
No comments:
Post a Comment