Friday, 7 December 2018

በጌታ ደስ ይበላችሁ


                  ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ!!!
                                  ፊሊጵ 4፥4
        ደስታ ለሁሉም የሰው ልጅ የተሰጠ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የደስታቸው ምንጭ ዘመናዊ መኪና፣ አካውንታቸው ውስጥ የተቀመጠ ዳጎስ ያለ ጥሬ ገንዘብ፣ ጥሩ ሥራ፣ ዝና፣ ትልቅ ቤት በዘመናዊ  ፈርኒቸሮችና ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች የተሞላ እንዲሁም ማራኪ ተክለ ሰውነት ለደስታ ቁልፎች እንደሆኑ የሚሰማቸው ብዙዎች ናቸው። ይህ ሁሉ ግን ጊዜያዊ ከመሆናቸውም ባሻገር እውነተኛ ደሰታ መስጠት አይችሉም።
           ደስታ ከላይ ከአባታችን ከእግዚአብሔር የሚስጥ በፍፁም ሀሴት የምናገኝበት በምናገኘውና በምናጣው ነገር ላይ ያለተመረኮዘ ነገር ግን ራሱን የቻለ ልዩ መለኮታዊ ሙላት ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሁሌ በጌታ ደስ እንድንሰኝ ያዛል።  በትክክል እንደ እግዚአብሔር ቃል ለሚመላለስ ሰው ለዚህ ደስታ ተገዢ ነው። ደስተኞች እንዳንሆን የሚያደርጉንና የሚያስጨንቀንን አንዳች ባለማስቀረት ጌታ ለእያንዳንዳችን ፈንታ ሆኖ ወስዶልናል።
          በዚህ እንደ እንግዳና መፃተኛ ሆነን በምንኖርበት ምድር በየትኛውም፣ በማናቸውም ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ ብንሆን ፈልገን ብናጣ፣ ሽተን ቢቀር፣ ሞክረን ባይሳካ፣ ጠይቀን ብንከለከል፣ ፈልገን ባናገኝ፣ ጠብቀን ባይመጣ፣  በጌታ ያለንን ደስታ የሚያሳጠና ከሆነ That is the question?
         የደስታችን ምንጭ ሊሆን የሚገባው ቃሉ እንደሚለው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለዚህም ደሰታችን የተጠበቀ እንዲሆን በሚያሰፈልገን ጊዜ የሚረዳን የእግዚአብሔር ፀጋ አለና። ሐዋርያው ቅዳስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በፃፈው መልእክቱ  በምዕራፍ 4፥13 ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ ይላል። ለሚያስፈልገን  ማንኛውም  ውጫዊ ነገር (ለምንም ነገር) ውስጣዊ ዝግጁነት ሊኖረን እንደሚገባ ያስገነዝበናል። ኋይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ለምንም ነገር ዝግጁ ነኝ ማለት ይገባናል።
        እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ነን፣ የእርሱ ልጆች ከሆንን ደግሞ የምንመራው በእርሱ መንፈስ ነውና እውነተኛውን 
 የደስታ እርካታ ወደምናገኝበት መቅረብ አለብን። የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። (1ኛ ዮሐ 3፥1) እግዚአብሔር ለእኛ ፍቅሩን የገለጸው አንድያ ልጁን በመስጠት ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ ምንም ስጦታ የለምና ደስታችንን በጌታ ሙሉ እናድርገው። ካነበብኩት አንድ ታሪክ ልንገራችሁ
         በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ጊዜ በአንድ አገር አየር ኋይል ውስጥ የሚሰራ አውሮፕላን አብራሪ ነበረ።  ይህ ሰው ብቸኛ አንድ ወንድ ልጁንና ባለቤቱን በሞት የተለዩት ሲሆን በወቅቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት ያበራት የነበረችው አውሮፕላን ተመታ ትወድቃለች እሱም ይሞታል። ታዲያ ሰውዬው በሕይወት እያለ በዓለም በሚታወቁ ሠዓሊያንና ቀራጺያን የተሰሩ እጅግ ውድ ሥዕሎችና በከበሩ ማህድናት የተሰሩ ጌጦችን ይሰበስብ የነበረ ሲሆን ምንም ወራሽ ባለመኖሩ ስሞት እነዚህ ንብረቶቼ በጨረታ ተሽጠው ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይሰጡልኝ ብሎ ስለነበር በጠበቃው አማካኝነት ንብረቶቹ ለጨረታ ይቀርባሉ።
         ጨረታውን ለመሳተፍ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍል የተሰበሰቡ ቱጃሮችና ጨረታውን ለመዘገብ የታደሙ ጋዘጠኞች ጨረታው በሚካሄድበት አዳራሽ ውስጥ ተሰግስገዋል። የሰውዬው ጠበቃ መድረኩን በመቀበል የሰውዬውን የመጀመሪያ ኑዛዜ አነበበና ከመንግስት ለተመደቡት አጫራች ስፍራውን ለቀቀ። በኑዛዜው መሰረት በቅድሚያ መሸጥ ያለበት የተናዛዡ ብቸኛ ልጅ መልክ የሚያሳይ በእጅ የተሰራ ሥዕል ነበረ የዚህ ሥዕል ሰዓሊውም ሆነ የተሳለው ልጅ ታዋቂ ባለመሆናቸው የተነሳ ጨረታውን የሚሳተፍ ሰው ጠፋ። ሁሉም ፀጥ አለ ሥዕሉንም የሚፈልገ ሰው ጠፋ። ጨረታውን ሊመለከት ከገባ ውስጥ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የሟች አገልጋይ የነበረ አንድ ሰው ነበረ። ይህ ሰው የተናዛዡን ሰውዬ ልጅንም ከልጅነቱ ጀምረው ያውቁት ስለነበር ምስሉን በእጁ ቢያስገባ መልካም እንደሆነ አሰበ። አንድም ማንም ሰው ለዚህ ምስል ፍላጎት ስላላሳዩና ሠዓሊምው በማንም የማይታወቅ በመሆኑ፣ አንድም ደግሞ ልጁን ስልሳደጉት ማስታወሻ ይሆናቸው ዘንድና አነስተኛ ዋጋ ቢጠሩ የሚፎካከር አይኖርም ብለው ስላሰቡ እጃቸውን አውጥተው አነስተኛ ዋጋ ይሰጣሉ። ሰውዬውም እንዳሰበው ማንም ምሥሉን ለመግዛት ፍላጎት ሳያሳይ ቀረና ሰውዬው ሥዕሉን አሸነፈ።
        በዛው ቅፅበት አጫራቹ ክብራትና ክቡራን ጨረታው ተጠናቋል ብሎ ተናገረ። ሁሉም የሰሙትን ሊያምኑት አልቻሉም ባሉበት ደንዝዘው ቀሩ። አጫራቹም በመቀጠል በኑዛዜው መሰረት የልጁን ሥዕል በጨረታ ያሸነፈ ያለምንም ተጨማሪ  ክፍያ ለልጁ በተሰጠው ዋጋ ሁሉንም እንደሚወስድ ኑዛዜው ያስገድዳል ብሎ የጨረታውን ማለቅ በያዘው የአጫራች መዶሻ ጠረጴዛው መታ።

ልጁ ያለው ሕይወት አለው።

ደግሜ እላለው ደስ ይበላችሁ።

ይህ ነው የእኛ ደስታ ሊሆን  የሚገባው። በዚህ መለኮታዊ እርካታና ደስታ ውስጥ ሁሌም መገኘት እንዲሆንልን እየተመኘው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ የእዚአብሔር አብ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።

No comments:

Post a Comment