Friday, 7 December 2018

ኢየሱስ


ኢየሱስ የሚለው ስም ትርጉም ሕዝቡን ሁሉ ከኋጢአታቸው የሚያድን አዳኝ ማለት ነው። ስሙ ከማዳን ጋር የተገናኘ ሲሆን አባታችን እግዚአብሔር እንደባለጠግነቱ መጠን ለእኛ በበደላችንና በኋጢአታችን ሙትን ለነበርነው እንድንበት ዘንድ የሰጠን በዚህም ዓለም ደግሞ ለሚመጣውም ዓለም ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ነው።

ስሙ ማትረፊያ ነው። ከዚህ ስም ብቻ የተነሳ መፅሐፍ ቅዱሳችን አንዲህ በማለት ትርፋችንን ይነግረናል።

1) ከዘላለም ፍርድ ያድናል።

"፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል። " (የሐዋርያት ሥራ 10: 43)

2) ከሃጢያት ያድናል።

"፤ ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። " (የማቴዎስ ወንጌል 1: 21)

"፤ መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና። " (የሐዋርያት ሥራ 4: 12)

3) የልጀነት ስልጣን ይሰጣል።

"፤ ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ "
(የዮሐንስ ወንጌል 1: 12)

4) ወደ እግዚአብሄር አብ ያቀርባል።

"፤ እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ። " (የዮሐንስ ወንጌል 15: 16)

5) ለሚጠሩት ሁሉ ባለጠጋ የሆነ ስም ነው፡፡

"፤ በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ "
(ወደ ሮሜ ሰዎች 10: 12)

6) የምንበረከክለት ብቸኛ ስም።

"፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ " (ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2: 10) ስለሆነም ለሌላ ስም ከቶ እንዳንበረከክ ይህ ያስረዳል።

7) ድርጊት መፈፀሚያ።

"፤ እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። " (ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3: 17)

እነዚህ ጥቂቶች ናቸው። ይህ ስም ለእኛ ለክርስቲያኖች የምንመካበት አዝለን ይዘነው የምንሄደው ከብዙ ነገር የምንወጣበት ማምለጫችን ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ማለት በአሁን ሰአት ብዙ ነቃፋን የሚያስገኝ እየሆነ መሄዱ የተለመ ሆኗል።

ብፁህ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የተባሉ አባት ተናገሩት የተባለው ትዝ አለኝ። አንድ ሰካኪ በስብከቱ ውስጥ ኢየሱስ እያለ በተደጋጋሚ በመጥራቱ ወደ እኝህ  አባት ቅሬታ ይቀርብበታል። አቡኑም ቅሬታው ምንድነው ብለው ይጠይቃሉ። ቅሪ የተሰኘውም ሰው ይህ ሰው ጌታችን በቁንፅላ ብቻ ኢየሱስ እያል በአንድ ስበከት ውስጥ በተደጋጋሚ ጠራው እንዴት ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይልም ድስት እንኳ ሁለት ጆሮ አለው አይደለም እንዴ አባታችን ይላል። እሳቸውም አንተ ሞኝ ድስት ራሱን አይችልም ኢየሱስ የሚለው ስም ግን ብቻውን ኋያል ነው። ያ '' ኢየሱስ '' ነው ጌታችንና መድሃኒታችን አሉትና መለሱት።

ኢየሱስ ከሚለው ስም ጋር በተያያዘ ሁላችንም በየራሳችን የማንረሳው ክስተት ይኖራል ብዬ አስባለው። እኔ ስሙ ከሆነልኝና በሰሙ ካገኘውት መዳንና በረከት ሌላ የማልረሳው አንድ ትወስታ አለኝ።

የዛሬ ዘጠኝ ወይም አስር ዓመት ገደማ ከስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ወጥቼ በዋናው በር ላይ የሜክሲኮ ታክሲ ይዤ መሄዴ ትዝ ይለኛል። አሁን የማላስታውሰው ነገር ግን በወቅቱ ለእኔ ወሳኝ ሆኖብኝ  የነበረ ጉዳይ ነበረ። አካሌ ታክሲ ሲሳፈር አእምሮዬ በሀስብ ባህር ተሳፍሮ ጭልጥ አርጎኛል።

 ታዲያ በዚህ ሀሳቤን በሙሉ በወሰደው ነገር እልም ካልኩበት ሰመመን ያነቃኝ ገጠመኝ ለእኔ አዲስ ክስተት ነበረ። እንዴትና በምን ሁኔታ ከተሳፈረኩበት ከስድስት ኪሎ አራት ኪሎ ታክሲው እንደደረሰ እንኳን አላወኩም፣ ነገር አንዳች ከተመሰጥኩበት ሀሳብ የሚያነቃ ድምፅ በድንገት በኋይል በጆሮዬ ገባ።

አንድ  ረዥም ቀጠን ያለ የቀይ ዳማ ጎልማሳ ከእሱ የወጣ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር ተጠምጄ ከነበረው ወሳኝ ሀሳቤ ሁለንተናዊ መነቃቃት በሚፈጥር ሁኔታ ከተሳፈርኩበት የሀሳብ ባህር በድንገት መለሰኝ።

ሰውዬው '' ኢየሱስ ጌታ ነው '' እያለ  በተደጋጋሚ ሳያቋርጥ ይናገራል። ሳልፈልግ ከሀሳቤ በመመለሴ ብቻ ሳይሆን የሰውዬው ድምፅ ጉልበት ለጆሮዬ ድንገት የመጣ አደጋ እስኪመስለኝ ድረሰ አስደንግጦኝ ስለነበረ እጅግ ተናድጄ ስለነበረ አፀፋዬን መለስኩለት እንዲህ በማለት
'' ኢየሱስ የጌቶች ጌታ የንጉሶች ንጉስ የአማልክት አምላክ  ነው'' ። እናም በወቅቱ አፀፋዬን በመመለሴ ውስጤን አረጋጋው። ልክም እንደሆንኩኝ ይሰማኝ ነበረ።  እውነት ነው ኢየሱስ የጌቶች ጌታ የንጉሶች ንጉስ የአማልክት አምላክ  ነው ነገር ግን መፅሐፍም እንደሚል ኢየሱስ ጌታ ነው።

"፤ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። "
(ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2: 11)

ስለዚህም የእኔ መልስ መሆን ይገባው የነበረ አሜን እንጂ አፀፋ አልነበረም። በወቅቱ በነበረው መናደድ '' ኢየሱስ ጌታ ነው '' የሚለውን በመቃወም የጌቶች ጌታ ማለቴ ልክ አልነበረም። እርሱ ጌታ የሆነው ነው የጌቶች ጌታ። አዎ ምላስም ሁሉ እንደሚል ቃሉ ምላሴ ለዚህ እውነት ህብረት ሊያደርግ ሲገባ የተነገረውን ቃል በመተው ሰውዬውን በመመልከቴ አፀፋ ሰነዘርኩ። ሰውን መመልከት መጨረሻው ጥፋት ነው። የሌላን መቃወም የእኔን ልክ አያረገውም። የሌላን መኮነን የእኔን እውነት አያረጋግጥም። የእሱን በማፍረስ የእኔን አይገነባም።

ኢየሱስ ከስም ሁሉ በላይ ነህ። ስምህን ሰምቶ ሞት ይደንግጥ ቀላያትም ይሰንጠቁ አለማመን ይራቅ ተብሎ እንደተፃፈ የስምህ ኋይል ስለገባኝ አመሰግናለው። እርቃንህን ስለእኔ በመስቀል የተቸነከርክ ስምህን በዘመኔ ሁሉ አውጃለው። ኢየሱስ ስምህን ለአዋጅ እንጂ ለሹክሹክታ እንኳ አይመችም።

No comments:

Post a Comment