Friday, 7 December 2018

ሥር ሰዳችሁ


የክርስትና ሕይወት ማደግ የሚጀምረው ወደ ታች ነው። መሰረቱ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። የሚታየው ማንነታችን የሚቆመው በመሰረቱ ነው። አንድ ዛፍ ወይም ትልቅ ሕንጻ መቆሙ የሚመሰረተው በያዘው መሰረት ነው። ክክርስቲያንም እንዲሁ በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ሕይወቱ ሊመሰረት የግድ ይሏል።

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር
'' ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ። ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም። ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ። '' (ሉቃ 6፥47-49)

ከፍታችን የሚለካው ወደ ታች ባደግንበት መጠን ነው። በቃሉ ተሞልተን  ሕይወታችንን ቃሉ እንደሚያዘው ብንኖር ወይም ብንታዘዝ እግዚአብሔርን ደስ እናሰኛለን እኛም አንወድቅም አልጥላችሁም ከቶ አልተዋችሁም ከእጄ መዳፍ ማንም አይወስዳችሁም ብሏልና። በአንፃሩ ደግሞ ካየነው የጠላት ዲያብሎስን ሽንገላ በቃሉ እየተቃወምንና እያሸነፍን እንድንኖር ያስችለናል። ስለሆነም ሥር ሰደን በማደግ ወደ ከፍታ መውጣት በክርስቶስ ትምህርት መሆንን ይጠይቃል።

" ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። " (ቆላ  2፥7)
በአጭሩ ከዚህ የምንረዳው ሥር በመስደድ የሚመጣ ጉዳይ አለ እነርሱም መታነፅና መጽናት። እንዚህ የሌሉበት ሥር መስደድ ከንቱ ነው። እንደቃሉ ያልሆነ ሥር መስደድ ሰማይ የማያውቀው ነው። ነገር ግን በነዚህ የታነፀ ሥር መስደድ ወደ ላይ የመውጣታችንን አቅም ይወስናል።

ያለን ምርጫ ሁለት ነው ወይ እንደ አረም መሬት ላይ ተንሳፎ በመኖር ነፋስም ሆነ ዝናብም ሲመጣ መርገፍ ወይ እንደ ዛፍ ስር ሰደን በመመስረት ምንም ቢከሰት ባለንበት መጽናት። የሚበልጠውን ቃሉ በግልፅ ነግሮናል በክርስቶስ ትምህርት ራሳችንን አንፀን በማደግ የእግዚብሔር መንግስት አገልጋይ እንድንሆን ኢየሱስ ጸጋና ኋይል ያብዛልን።

No comments:

Post a Comment