ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌ 2፥4-5
Tuesday, 18 December 2018
የጌታ ክብር መገለጥ (ክፍል አንድ)
በዮሐንስ ወንጌል ተከታታይ ጥናት እየተማርኩት ካለው ውስጥ በምዕራፍ ሁለት መጀመሪያ ላይ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተለምዶ ወይም በአብዛኛ አጠራር በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት የተደረገውን የጌታ ክብር መገለጥ ላካፍላችሁ በመሻቴ የእግዚአብሔር መንፈስ በረዳኝ መጠን እንዲህ አቀርበዋለው። ወደ ዋናው ሀሳቤ ከመግባቴ በፊት ታሪኩን እንድታነቡ እጋብዛችኅለው።
'' በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ። ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ። '' (ዮሐ 2፥1-11)
ይህ ክፍል ብዙ የተባለበት ብዙ መፅሐፍ የተፃፈበት ብዙ ስብከት የተሰበከበት ክፍል ነው። ነገር ግን አብዛኛውን ሰምተን ያደግነው መፅሐፉ ሊናገረን ባሰበው መንገድ አይደለም የሰማነውም፣ ያነበብነውም፣ ያጠናነውም። ለዚህ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል የተለያዩ ርዕሶች ተሰጥተውታል። ለአብነት ያህልም በዋናነት የሚታወቁት የመጀመሪያው ተአምር፣ ቃና ዘገሊላ፣ በእርሱ አመኑ፣ የሚላችሁን አድርጉ፣ የድንግል ማርያም ምልጃ ልንል እንችላለን። በዚህ ታሪክ ውስጥ ብዙ ክንውን ተደርጓል ነገር ግን ታሪኩን የሚያገናኝ ሀሳቡን የሚሰበሰብና የሚጠቀልል ወይም ሁሉንም ድርጊትና ንግግሮችን የሚገዛ አንድ ወሳኝ ግንድ አለ። እርሱም የጌታ ክብር መገለጥ።
ቀድሞ የሆነውን ሰርጉን በምክንያትነት የደቀ መዛሙርቱ ማመን በውጤትነት የጌታ ኢየሱስ ክብር መገለጥ ማዕከልነት በማድረግ የተከናወነ ታሪክ ነው። በዚህ ታሪክ ብቻም አይደለም በአዲስ ኪዳን በዋናነት የጌታን ክብር መገለጥን ነው የሚነግረን ስለሆነም ለፅሁፋችን '' የጌታ ክብር መገለጥ '' የሚል ርዕስ ስጥተነዋል። በዚህ ታሪክ ውስጥ ማንም ይናገር፣ ምንም ይደረግ፣ ማንም ይሳተፍ በዛ የተደረገው ሁሉ የጌታ ክብር ለመግለጥ ነው።
ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት አብዛኛው በዚህ ታሪክ ዙሪያ የተደረጉ አስተምህሮዎች በተሳሳተና የጌታን ክብር መገለጥ በሚሸፍን መልኩ ነው የተላለፉት። ለዚህም አብዛኛው አስተምህሮዎች ርዕሶች ምስክር ናቸው። የአንድ ትምህርት ርዕስ የትምህርቱ ዋና ሀሳብን የሚይዝ ሲሆን በዙሪያው ያለውን ሁኔታ በሙሉ ለርዕሱ ተገዢ ያደርገዋል። በዚህ መልኩ የሚያስተምሩ አስተማሪዎችና መምህራን ይህን ያደረጉት አውቀውም ይሁን ሳያውቁ
ሀ) የጌታ ክብር ለማደብዘዝ
ይህንንም ለማሳካት ሶስት መንገዶችን ወይም ዘዴዎችን ተጠቅመዋል።
1) ርዕስ ሲመርጡ ከገቢር ግስ ይልቅ ተገብሮ ግስ ይጠቀማሉ (they prefer passive rather than active) ድርጊቱን የሚገልፀውን ወይም ድርጊቱን የፈፀመውን አካል በመተው የድርጊቱን ባለቤት ማደብዘዝ/መሸፈን (ከድርጊቱ ማስወጣት ነው) እና ሌላ ነገር ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።
ምሳሌ ሀ:-
'' The man kill the Dog.'' ከሚለው ይልቅ '' A Dog is killed.'' በመጀመሪያው ላይ ሰውዬው ውሻውን እንደገደለ ግልፅ ነው። የሰውዬውን ማንነት በድርጊት ተገልጿል። በመሆኑም አድራጊው የታወቀ ነው። በሁለተኛው ውሻው ተገሎ መሞቱን እንጂ ማን እንደገደለው አይገልፅም በዚህ ርዕስ ውስጥ ተናጋሪው አድራጊውን አስወጥቶቷል። ይህ ደግሞ መረጃነቱን ባሳጣት ክፍተት ፈጥሯል። ፍንጭ እንጂ ማስረጃው ደብዝዟል።
ምሳሌ ለ:- '' ኢየሱስ ውሃውን ወይን ጠጅ አደረገው '' ከሚለው ግስ ይልቅ '' ውሃው ወደ ወይን ጠጅ ተለወጠ '' ይሉታል። '' አደረገ '' የሚለው ገቢር ግስ ሲሆን '' ተለወጠን '' በማምጣት ተገብሮ ግስን በመውሰድ ድርጊቱን የፈፀመውን አካል ቸል ይሉታል። ርዕሱ እውነት ይመስላል ግን ኢየሱስን አውጥቶታል።
2) ርዕስ ሲመርጡ ለአድራጊው ማንነት ላይ ትኩረት አለመስጠት። በቃና ዘገሊላ ጌታ ኢየሱስ ካደረገውና ከተገለጠው ክብር ይልቅ ሰርጉ ላይ ማተኮር፣ በሰርጉ የታደሙ ሰዎች ላይ ማነጣጠር፣ የተደረገው ተአምራት ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ፣ የወይኑ መጣፈጥ ላይና ድንግል ማርያም የተናገረችውን ለጥጦ ማየት።
ምሳሌ ሐ:-
የኢየሱስ የመጀመሪያው ምልክት ከሚለው ይልቅ የመጀመሪያወ ምልክት ብቻ በማለት ኢየሱስን ማስወጣት። አዲሱ መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሚለው '' ኢየሱስ ውሃውን የወይን ጠጅ አደረገ '' ይላል። ይህ ሙሉ ነው በዛ ላይ Active ነው። ሙሉ መረጃ መስጠት ይችላል ነገር ግን ኢየሱስን በማውጣት የተፈጠረውን ምልክት ላይ ብቻ ማተኮር። የዚህም ዓላማ ኢየሱስን ማደብዘዝ ነው።
3) ታሪኩን በመቆራረጥ የተለያየ ርዕሶችን መስጠት። 11 ቁጥሮች ያሉት ይህ ታሪክ ብዙ የተቆራረጡ ርዕሶችን በመስጠት ዋና ሀሳብ እንዳይነሳ ማድረግ።
ምሳሌ መ:- የ2000 ዓ.ም የታተመው ሰማንያ አሐዱ መፅሐፍ ቅዱስ ይህን ታሪክ በሶስት ከፋፍሎ ርዕስ ስጥቶታል ግን ሶስቱም ስር ኢየሱስ የለም።
=}} ከቁጥር 1-2 በቃና ዘገሊላ ስለተደረገው ሰርግ ይላል
=}} ከቁጥር 3-5 ስለ እናቱ ምልጃ ይላል
=}} ከቁጥር 6-11 ስለ መጀመሪያ ተአምር ይላል።
መፅሐፍ ቅዱስ ሊነግረን ያለውን በመተው ሃይማኖታዊ ፓለቲካ ፍጆታ ሰበብ (For Denomination Purpose) የገቡ ርዕሶች እንዳሉ ማየት ቀላል ነው። እንዲገባ የተፈለገ ሀሳብ በግድ ተጠምዝዞ ገብቷል። ከእውነት ይልቅ ለብዙ ዘመናት የነበረውን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን አስተምህሮ የማስቀጠል አጀንዳ መያዙን መረዳት እንችላለን።
ይቀጥላል................................
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment