በክፍል ሁለት ላይ የጌታ እናት ድንግል ማርያም በሰርጉ ቤት የተከሰተውን ክፍተት/ጉድለት ልጇ እንዲሞላላት መጠየቋን በተያያዘ የሚነሱ ሀሳቦችን ተመልክተናል። በዚህ ክፍልም ያልዳሰስናቸውን ሁለት ነገሮች ላይ ትኩረት እናድርጋለን።
" የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። " (ዮሐ 2፥3)
'' የወይን ጠጁ አልቆባቸዋል አለች። ''
ይህን የድንግል ማርያም ጥያቄ ያለ አግባብ ተለጥጦና ተመናፍሶ በዓለም ላያ የሚኖረውን የሰው ዘር በሙሉ ከዘላለም የሞት ፍርድ የሚያድን ምልጃ አድርገው የሚያስተምሩ አሉ። ይህ '' አልቆባቸዋል '' ወይም '' የላቸውየ '' የሚሰራው (Addressed የሚያደርገው) ላለቀው የወይን ጠጅ ብቻ እንጂ በኃጢአት ባርነትና በሞት ቀጠና ውስጥ የተዘፈቀውን የሰውን ልጅ የነፍስ ጉዳይ የሚመለከት አይደለም። ይሄ ዓለምን ያናጋ የሰውን ልጅ ሕይወት እንደቀየረ ተደርጎ የጌታን ወደ ምድር መምጣት የሚያደብዘዝ የሰውን ማስተዋል ያጨለመ ድፍን ውሸት ነው። ይሄ ከነፍስ ጥያቄ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ጉዳይ የለውም።
የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የተጣላበት ምክንያት ኃጢአት ነው ምልጃም ካስፈለገው በዚህ ጉዳይ እንጂ በሰርግ ቤት ውስጥ ባለቀ የወይን ጠጅ ፍጆታ አይደለም። በሰርጉ ላይ ምልጃ ያስፈልገዋል ብለን ልናነሳው የምንችለው ምንም ዓይነት ጥል የለም። እንደውም ጌታ በዚህ ሰርግ ላይ በወዳጅነት ነው የታደመው። ስለሆነም የወይን ጠጅ በማለቁ ከጌታ ጋር የተገባ ጥል ባለመኖሩ ምልጃ ልንለው እንኳ አንችልም።
ሲቀጥልም ይሄ ጥያቄ ምልጃ ነው እንኳ ብንል አሁን ካለው የምልጃ ፅንሰ ሀሳብ ጋር ፍፁም አይገናኝም። በሰርጉ ላይ ድንግል ማርያም በስጋዊ ሕይወት እያለች የተከናወነ ሲሆን አሁን በአፀደ ነፍስ እያለች አማላጅ ለማድረግ ይህን መጥቀስ በፍፁም አያስኬድምም ተገቢም አይደለም።
እረ ለመሆኑ ሌሎች ለጌታ የቀረቡትን ተማፅኖዎች ምን እንበላቸው? ለአብነት ያህል በማርቆስ ወንጌል 5፥22-43 (ሙሉውን እንድታነቡት እየመከርኩ) የምናገኘውን የምኩራብ አለቃ ጌታን የጠየቀው ጥያቄ የሞተችውን የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ ብላቴናን ከሞት ያስነሳው ምልጃ ምን ሊባል ነው? በቅንነት አስቡት።
እንደ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን እንደ ባለ አእምሮ ብናስበው ውሃን ወደ ወይን ጠጅ መቀየር ወይስ የሞተን ማስነሳት ያስገርመናል? እንደኔ ግን ሁለቱም ጌታ ሁሉን ቻይ በመሆኑና በኃይሉ ብዛት በችሎቱም ብርታት እንድስኳ የሚሳነው እንደሌለው እርግጥ ቢሆንም እጄን በአፌ የሚያስጭነኝ ግን የሞተን ማስነሳት ነው።
እንደ ዘመኑ የምልጃ አራጋቢዎች ቢሆን ኖሮ የምኵራብ አለቃው የኢያኢሮስ ምልጃ ዛሬም እየተወሳ አንዱ አማላጃችን አድርገውት ወርሃዊና ዓመታዊ የበአል ቀን ተሰይሞለት ባየን ነበር ነገር ግን በብልሃት አድርጎ ተረት የፈጠረው ዲያብሎስ አዋጭነቱ ላይ አላመነበትም ለማለት እገደዳለው።
'' የኢየሱስ እናት ''
ዮሐንስ ድንግል ማርያምን በቀራኒዮ መስቀል ስር ከጌታ አደራ የተሰጠው እናቱ እንደመሆኗ ደግሞም ወደ ቤቱም እንደወሰዳትና አብረው እንደመኖራቸው መጠን ጠለቅ ያለ ግንኙነት (የእናት ልጅ) ይኖራቸዋል ነገር ግን በወንጌሉ ላይ አንድም ቦታ በስሟ ወይም አሁን ዘመን ላይ እየተነሳች ባለው ልማድ መልኩ አልጠቀሳትም ለምን ይሆን? የእኔ ጥያቄ ነው።
እንደኔ መረዳት ግን በየትኛውም መልኩ ከመግለፅ የጌታ ወይም የኢየሱስ እናት ማለቱ የበለጠ ይገልጣታል እላለው። መቼም እንደ ባለ ዘመናችን ሰባኪያንና ቲቮዞአዊያን የዘርዓ ያዕቆብ እመቤት (ሲያሻቸውም የዘርዓ ያዕቆብ አምላክ ሲሏትም በጆሮዬ ሰምቻለው) ማለት ድንግል ማርያምን ከማቅለል ባለፈ አላየውም። አዎ ኢየሱስን መውለዷ ማንም የሚቀማት ወይም የሚጋራት የለም። እሱን በመውለዷ ብቸኛ ፀጋ አላት። ይህንን ግን አውርደው ወንጌል እንኳ ባልተጠቀመበት መንገድ መጥራት ወንጌሉን መፃረር ነው።
ይቀጥላል..................
No comments:
Post a Comment