ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌ 2፥4-5
Friday, 7 December 2018
ማዳን የፈጣሪ የባሕሪው ገንዘብ ስለ ሆነ በፍጡር መዳን አይቻልም።
"እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም።" (ኢሳ 43፥11)
ማዳን የእግዚአብሔር የባሕሪው ገንዘቡ ነው። መላእክትም ሆኑ ሌሎች ፍጥረታት የእግዚአብሔር የባሕሪይ ገንዘብ የሆነውን ማዳን የራሳቸው ሊያደርጉት አይችሉም፤ አይፈልጉምም። ነገር ግን ይህን ማዳን በመላላክ ሊያገለግሉ ይችላሉ። ለምሳሌ:-
እግዚአብሔር ሠለስቱ ደቁቅን (አናንያ አዛርያ ምሳኤል) ከእሳት ዳንኤልን ከተራቡ አናብስት ሊያድናቸው በፈለገ ጊዜ ማዳኑን የፈጸመው በመላእክት ተልእኮ በኩል እንደ ሆነ ከቅዱስ መጽሐፍ እናነባለን።
ሆኖም ይህ ከመከራ ሥጋ የማዳን ሥራ አሁንም የእግዚአብሔር እንጂ የተላከው መልአክ ገንዘብ አልነበረም። ለዚህም ነው ናቡከደነጾር እግዚአብሔር የፈጸመውን የማዳን ሥራ ካየ በኋላ
''...#መልአኩን_የላከ_ከአምላካቸውም_በቀር_ማንንም_አምላክ_እንዳያመልኩ_ለእርሱም_እንዳይሰግዱ_ሰውነታቸውን_አሳልፈው_የሰጡትን_የንጉሡንም_ቃል_የተላለፉትን_በእርሱ #የታመኑትን_ባሪያዎቹን_ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ። '' ሲል የማዳኑን ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን ያመሰገነው። (ዳን 3፥2)
ዳንኤልንም ዳርዮስ፣ " የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን? " ሲል በጠየቀው ጊዜ ለዳርዮስ በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና በአንተም ፊት ደግሞ ንጉሥ ሆይ አልበደልሁምና #አምላኬ_መልእኩን_ልኮ_የአንበሶቹን_አፍ_ዘጋ እነርሱም አልጎዱኝም (ዳን 6፥20-22) ሲል ያዳነውን እግዚአብሔርን በሚገባ ክብር አክብሮታል።
ከመከራ ሥጋ መዳንን በተመለከተ ይህን ሁሉ ካየን፣ ከመከራ ነፍስ መዳን (ከኋጢአትና በኋጢአት ምክንያት ከመጣብን ፍዳ መዳን) እንዴት በፍጡራን ሊፈጸምና ሊሰጥ ይችላል? የሚል ጥያቄ ከባድ አይሆንብንም። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን በተመለከተ የተናገረውን ከዚህ እንመልከት።
''ወኢያንሥአ ለነ ሊቀ ካህናት እመላእክት ወኢ እም ኀይላት እለ እሙንት ይቀውሙ ዐውደ መንበሩ አላ አሐዱ ለሊሁ ወረደ ወተሠገወ እምህላዌነ ወኮነነ ሊቀ ካህናት ወአዕረገ በእንቲአነ ሥጋሁ መሥዋዕት ለአቡሁ በአብጽሐነ ሎቱ በዘቦተ ሐመ''
ትርጉም
" ዙፋኑን ከብበው ከሚቆሙ ከመላእክት ከኀይላትም ወገን ሊቀ ካህናት አልሾመልንም። እርሱ አንዱ ወደዚህ ዓለም ወርዶ ባሕሪያችንን ብሕርይ አድርጎ ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) ሆነን እንጂ ስለ እኛም ሥጋውን መሥዋዕት አድርጎ ወደ አባቱ አቀረበ፤ በታመመበት በሥጋው ለእርሱ ገንዘብ ለመሆን አበቃን ''
ከዚህ ሁሉ ማስረጃ የምናስተውለው ነጥብ ቢኖር፣ መጸሐፍ ቅዱስም ሆነ የአባቶች ትምህርት በመላእክት የተፈጸመ ወይም የሚፈጸም ከኋጢአት ሰውን የማዳን ሥራ ፈጽሞ የሌለ መሆኑን ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች ሁሉ መላእክትን ያከበርን መስሏቸው ከመላእክት መዳንን በመፈለግ እግዚአብሔርን እንዳያስቆጡና ራሳቸውንም ከእውነተኛው የመዳን መንገድ እንዳያወጡ በክርስቶስ ፍቅር እንመክራለን።
በአሁን ሰአት የብዙዎችን ጥያቄ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሀሳብ እየመለሰና እያስተማረ ከሚገኘው በመጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር የተጻፈው ምርጥ መጽሐፍ ከሆነው '' መዳን በሌላ በማንም የለም '' ከሚለው ከገጽ 55-56 የተወሰደ። መጽሐፉን በመግዛትና በማንበብ እንድትጠቀሙበት በጌታ ፍቅር ጋበዝኳችሁ።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)

No comments:
Post a Comment