Monday, 31 December 2018

የጌታ ክብር መገለጥ (ክፍል ሦስት)

በክፍል ሁለት ላይ የጌታ እናት ድንግል ማርያም በሰርጉ ቤት የተከሰተውን ክፍተት/ጉድለት ልጇ እንዲሞላላት መጠየቋን በተያያዘ የሚነሱ ሀሳቦችን ተመልክተናል። በዚህ ክፍልም ያልዳሰስናቸውን  ሁለት ነገሮች ላይ ትኩረት እናድርጋለን።

" የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። " (ዮሐ 2፥3)

'' የወይን ጠጁ አልቆባቸዋል አለች። ''
ይህን የድንግል ማርያም ጥያቄ ያለ አግባብ ተለጥጦና ተመናፍሶ በዓለም ላያ የሚኖረውን የሰው ዘር በሙሉ ከዘላለም የሞት ፍርድ የሚያድን ምልጃ አድርገው የሚያስተምሩ አሉ። ይህ '' አልቆባቸዋል '' ወይም '' የላቸውየ '' የሚሰራው (Addressed የሚያደርገው) ላለቀው የወይን ጠጅ ብቻ እንጂ በኃጢአት ባርነትና በሞት ቀጠና ውስጥ የተዘፈቀውን የሰውን ልጅ የነፍስ ጉዳይ የሚመለከት አይደለም። ይሄ ዓለምን ያናጋ የሰውን ልጅ ሕይወት እንደቀየረ ተደርጎ የጌታን ወደ ምድር መምጣት የሚያደብዘዝ የሰውን ማስተዋል ያጨለመ ድፍን ውሸት ነው። ይሄ ከነፍስ ጥያቄ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ጉዳይ የለውም።

የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የተጣላበት ምክንያት ኃጢአት ነው ምልጃም ካስፈለገው በዚህ ጉዳይ እንጂ በሰርግ ቤት ውስጥ ባለቀ የወይን ጠጅ ፍጆታ አይደለም። በሰርጉ ላይ ምልጃ ያስፈልገዋል ብለን ልናነሳው የምንችለው  ምንም ዓይነት ጥል የለም። እንደውም ጌታ በዚህ ሰርግ ላይ በወዳጅነት ነው የታደመው። ስለሆነም የወይን ጠጅ በማለቁ ከጌታ ጋር የተገባ ጥል ባለመኖሩ ምልጃ ልንለው እንኳ አንችልም።

ሲቀጥልም ይሄ ጥያቄ ምልጃ ነው እንኳ ብንል አሁን ካለው የምልጃ ፅንሰ ሀሳብ ጋር ፍፁም አይገናኝም። በሰርጉ ላይ ድንግል ማርያም በስጋዊ ሕይወት እያለች የተከናወነ ሲሆን አሁን በአፀደ ነፍስ እያለች አማላጅ ለማድረግ ይህን መጥቀስ በፍፁም አያስኬድምም ተገቢም አይደለም።

እረ ለመሆኑ ሌሎች ለጌታ የቀረቡትን ተማፅኖዎች ምን እንበላቸው? ለአብነት ያህል በማርቆስ ወንጌል 5፥22-43 (ሙሉውን እንድታነቡት እየመከርኩ) የምናገኘውን የምኩራብ አለቃ ጌታን የጠየቀው ጥያቄ የሞተችውን የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ ብላቴናን ከሞት ያስነሳው ምልጃ ምን ሊባል ነው? በቅንነት አስቡት።

እንደ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን እንደ ባለ አእምሮ ብናስበው ውሃን ወደ ወይን ጠጅ መቀየር ወይስ የሞተን ማስነሳት ያስገርመናል? እንደኔ ግን ሁለቱም ጌታ ሁሉን ቻይ በመሆኑና በኃይሉ ብዛት በችሎቱም ብርታት እንድስኳ የሚሳነው እንደሌለው እርግጥ ቢሆንም እጄን በአፌ የሚያስጭነኝ ግን የሞተን ማስነሳት ነው።

እንደ ዘመኑ የምልጃ አራጋቢዎች ቢሆን ኖሮ የምኵራብ አለቃው የኢያኢሮስ ምልጃ ዛሬም እየተወሳ አንዱ አማላጃችን አድርገውት ወርሃዊና ዓመታዊ የበአል ቀን ተሰይሞለት ባየን ነበር ነገር ግን በብልሃት አድርጎ ተረት የፈጠረው ዲያብሎስ አዋጭነቱ ላይ አላመነበትም ለማለት እገደዳለው።

'' የኢየሱስ እናት ''
ዮሐንስ ድንግል ማርያምን በቀራኒዮ መስቀል ስር ከጌታ አደራ የተሰጠው እናቱ እንደመሆኗ ደግሞም ወደ ቤቱም እንደወሰዳትና አብረው እንደመኖራቸው መጠን ጠለቅ ያለ ግንኙነት (የእናት ልጅ) ይኖራቸዋል ነገር ግን በወንጌሉ ላይ አንድም ቦታ በስሟ ወይም አሁን ዘመን ላይ እየተነሳች ባለው ልማድ መልኩ አልጠቀሳትም ለምን ይሆን? የእኔ ጥያቄ ነው።

እንደኔ መረዳት ግን በየትኛውም መልኩ ከመግለፅ የጌታ ወይም የኢየሱስ እናት ማለቱ የበለጠ ይገልጣታል እላለው። መቼም እንደ ባለ ዘመናችን ሰባኪያንና ቲቮዞአዊያን የዘርዓ ያዕቆብ እመቤት (ሲያሻቸውም የዘርዓ ያዕቆብ አምላክ ሲሏትም በጆሮዬ ሰምቻለው) ማለት ድንግል ማርያምን ከማቅለል ባለፈ አላየውም። አዎ ኢየሱስን መውለዷ ማንም የሚቀማት ወይም የሚጋራት የለም። እሱን በመውለዷ ብቸኛ ፀጋ አላት። ይህንን ግን አውርደው ወንጌል እንኳ ባልተጠቀመበት መንገድ መጥራት ወንጌሉን መፃረር ነው።

ይቀጥላል..................

Wednesday, 26 December 2018

የጌታ ክብር መገለጥ (ክፍል ሁለት)

በክፍል አንድ የምንነጋገርበትን የፅሐፍ ሀሳብ እንደ መግቢያ እንዳየን የሚታወስ ነው። እነሆ አሁን ደግሞ ቃል በቃል ያለውን ሀሳብ እናያለን። የማስተዋል መንፈስ፣ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራ መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፤  መንፈስ ቅዱስ ሁላችንንም ይርዳ።

#ማሳሰቢያ:- የእግዚአብሔርን ክብር መግለጥ ማለት የቅዳሳንን ክብር ማቅለል አይደለም። ቀድሞውኑ የሰው ልጅ ምን ክብር አለውና የቅዱሳን ክብር እግዚአብሔር አይደለምን?

 =}} (ዮሐንስ ወንጌል 2፥1-2)


" በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። "

በዚህ ምንባብ ሶስት ሀሳቦች ላይ ጥያቄ በመመለስ እናያለን።

ሀ) ድርጊቱ የተፈፀመው የት ነው?
ቃና ከናዝሬት ሰባት ኪሎ ሜትር ርቃ በሰሜን እስራኤል የምትገኝ ትንሽ ከተማ ነች። ቃና ዘገሊላ የተባለችው ሌላ ቃና የሚባል ስፍራ ስላለ ለመለየት ሲባል ነው። ይህ ማለት የኮተኬ ካራና የአየር ጤና ካራ እንደማለት ነው። ገሊላ ደግሞ ጌታ ያደገበት ስፍራ ወይም አቅራቢያ መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። ከዚህም በመነሳት ለሰርግ ጥሪው የቅርብ ሰው እንደሆነ መረዳት እንችላለን። እናቱ ድንግል ማርያም በዛ አካባቢ የምትታወቅና ለሰርጉ ቤተ ሰዎች የቅርብ ሰው እንደሆነች ታሪኩ ያሳያል። ይህን ማወቅ ታሪኩን በትክክል እንድንረዳ ይጠቅመናል። በእርግጥ ቦታውን ማወቅ በራሱ የታሪኩን አግባብነት እንድናውቅ ካልሆነ በቀር በራሱ መንፈሳዊ ጉዳይ (Theologies) መሆን አይችልም። Theology ያለው ምልክቱ ላይ ነው።

ለ) ቀኑ መች ነው?
በሶስተኛው ቀን የሚለው ብዙ አስተምህሮዎች እንደሚያመለክቱት ከትርጓሜ መፅሐፍ ጨምሮ ጌታ ከተጠመቀበት ቀን ጀምሮ እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን ጌታ ከተጠመቀ በኃላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በሲና በረሃ እንዳሳለፈና ከዛ ወዲህ ደግሞ ፊሊጶስ ናትናኤልን ወደ ኢየሱስ እስኪጠራበት ድረስ ሁለት በነገው የሚሉ ቀኖች እናነባለን (ዮሐ 1፥29 1፥35 ተመልከቱ)። በአጠቃላይ አርባ ሁለት ቀኖች በመኖራቸው ከተጠመቀ በኃላ ባለው በሶስተኛወ ቀን ነው ማለት እንዳንችል ይገድቡናል። ታዲያ ይህ ሶስተኛ ቀን የሚያመለክተው መች ነው የምትሉ ከሆነ ናትናኤል ከተጠራ ከቁጥር 44 ላይ ከተፃፈው በነገው በኃላ እንደሆነ ግን ጥርጥር የለውም። ጌታ ናትናኤልን ገና ከዚህ የሚበልጥ ታያለህ ካለው በኃላ ባለው በሶስተኛው ቀን ማለት ነው።

ሐ) የሰርጉ ዓይነት ምን ዐይነት ነበር?
በእስራኤል ባህል የሰርግ ስነ ስርአት ለቀናቶች የሚቆይ ሲሆን  ብዙ ማህበረሰብ የሚሳተፍበት ነው። በዚህም ምክንያት የሰርጉ ድምቀት በሚሳተፉት ሰዎች ላይ የተመሰረተ ነው። የተሳካ ከሆነ የሁሉም ተሳታፊ ዘመድ አዝማዝ ክብር ሲሆን በአንፃሩም ሰርጉ ቢበላሽ ወይም ቢደበዝዝ ውርደቱ፣ ሀፍረቱና ተጠያቂነቱ በሰርጉ ለተሳተፉ ሁሉ እንጂ ለባለ ሰርጉ ብቻ አይደለም። የሰርጉን ቦታ እንዳየነው የጌታ እናት ማርያም ሳትጠራ እንደሄደች የምናውቀው ለሰርጉ ቤት የቅርብ ሰው እንደሆነች ስለሚያመለክት ነው። ደግሞ ሰርግ ስላለ ብቻ አይኬድም ጥሪ ወይም ዝምድና ያስፈልጋልና።

'' የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች '' ሲል ታዳሚ ከመሄዱ በፊት በዛ ስለመኖሩዋን ያሳያል። ይህ ማለት በጥሪ ሳይሆን በቅርበት ወይም በአገልግሎት እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ነው። የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል የሚለው ጥያቄ የሚነግረን ይህንኑ ነው። የቅርብ ተቆርቋሪ እንደነበረችና ድንግል ማርያምም በሰርጉ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት ጌታን እንደጠየቀች ጥርጥር የለውም።

"ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። "

መታደም ከላይ እንደገለፅኩት መጠራትን ያሳያል። የእንግሊዝኛውም መጽሀፍ ቅዱስ የሚነግረንም ይህን ነው (Jesus was called ይላል)። ጌታ በዚህ ጊዜ ሰላሳ ዓመት ስለሞላውና ራሱን ችሎ አገልግሎት ስለጀመረ እንዲሁም ደቀመዛሙርት ስላፈራ ከእናቱ ተለይቶ ብቻውን መጠራት ጀምሯል።

#ምልከታ:-
ብዙ አስተምህሮዎች ጌታ በሰርጉ የተገኘበት ምክንያት ነው የሚሉት
1) ማህበራዊ ጉዳይ (ዝምድና) ስለነበረው ነው የሚሉ አሉ
2) ሰርግ ሊባርክ የሚሉ አሉ
3) ክብሩን ሊገልጥ ነው።

የመጀመሪያውና ቀጥሎ ያሉው ሁለቱም ጥያቄ ያስነሳሉ ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ጌታ የትም ቦታ ለማህበራዊ ግንኙነቶች ተልእኮ ሲያደርግ አናይም ከመለኮታዊ አጀንዳ ውጪ። ሲቀጥል ሰርግ በተፈጥሮው የተባረከ ስለሆነ የትኛውም ጋብቻ ከርኩሰትነት ወደ ቅዱስነት የሚለወጥ አይደለም (Declaration ግን ሊኖር ይችላል)። ዋናው ነገር የሰርጉ ጥሪ ምልክት በማድረግ መለኮታዊ አጀንዳውን ሊፈፅምና ክብሩን ሊገልጥ ምክንያት ሆኖል። ስለሆነም ጥሪው ጌታ የሄደበትን ጉዳይ ያገናዘበ ሳይሆን ለቤተሰቡ ቅርብ በመሆኑ ነው። ምንም እንኳ ለሰርግ ቢጠራም ጌታ የተንቀሳቀሰው የአባቱን ፍቃድ ለመፈፀም ነው።

=}} (የዮሐንስ ወንጌል 2፥3)


" የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። "

እዚህ ክፍል ላይ ብዙዎችን ሲያጨቃጭቅ የኖሩ ጥያቄዎች አሉ።
1) የጌታ እናት ድንግል ማርያም የወይን ጠጅ ማለቁን እንዴን አወቀች?
2) ለምን ልጅዋን ጠየቀችው?
3) ወሃውን ወደ ወይን ይቀየራል ብላ አምና ነው ወይስ መፍትሄ ይሰጣል ብላ አስባ ነው የጠየቀችው?

እነዚህን ጥያቄዎች በታሪኩ አግባብ ከታዩ ለመመለስ ቀላል ነው። ግን በሃይማኖተኝነት ግለት (ግብዝነት) እዚህ ታሪክ ውስጥ የተደረጉትን በሙሉ መንፈሳዊ አድርጎ በማሰብ ከሆነ የተዛባና ከእግዚአብሔር ሀሳብና እቀድ ውጪ ያደርገናል።

ድንግል ማርያም የወይን ጠጁ እንዳለቀ ለማወቅ በቦታው መሆኗ በቂ ነው። እዛ በመሆንና በማየት የመጣ እውቀት ስለሆነ። መቼም እንዳሁኑ ዘመን አባባል ሳሎን ቅጭ ብላ ጓዳ ያለውን የጠጅ ጋን በመንፈስ አይታው ነው አንልም። ይገርማል የሰርጉን ቤት ጓዳ እንደሞላሽ የእኛንም ቤት ጓዳ ጎብኚ የሚሉ እጅግ ብዙ አሉና። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ድንግል ማርያም ሁሉንም ነገር ታውቃለች ብለው ያምናሉ ይህ ደግሞ ስህተት ከመሆን ባለፈ በእግዚአብሔር ህልውና ላይ አመፃን ማድረግ ነው። ለዚህ ማመሳከሪያ ጌታ ኢየሱስ በአስራ ሁለት ዓመቱ በጠፋባቸው ጊዜ ዮሴፍና ማርያም ለሶስት ቀን በፍለጋ ባለፉ ነበር።

ልጅዋን የጠየቀችበት ምክንያት ድንግል ማርያም የእምነት ሰው ስለሆነች ነው። መፅሐፍም እንደሚል በልቧ ትጠብቀው  እንደነበር ይናገራል። ይህ ደግሞ በልጇ ላይ ያላትን እምነት ያሳያል። ከጽንሰቱ ብስራት ጀምሮ የተከናወነውን ነገር ሁሉ ታውቃለች። የልጇን ማንነት በሚገባ የተነረዳች ከመሆኑም አንፃር የፈለገውን አድርጎም ቢሆን መፍትኤ ይሰጣል ብላ እርግጠኛ ስለነበረች ልጇን ጠይቃለች። '' ይኩነኒ በከመ ትበሌኒ '' ይሁን ይደረግልኝ ማለቷ ብቻ እኮ ስለ እምነቷ ማውራት ከበቂ በላይ ነው።

ጌታ ውሃውን ወደ ወይን ይቀይራል ብላ specifically እውቀት አላት ማለት አንችልም ነገር ግን ቀድሜ እንዳልኩት የልጇን ማንነት ላይ ባለ እምነት ግን ጠይቃለች። ማወቅ ያለብን ጉዳይ ማርያም ይህን ስትል ከማህበራዊ ግዴታን ወይም ከማህበራዊ ችግር ከፍታት የቀረበ ከመሆኑ ባሻገር ልንወስደው አንችልም። ምንም እንኳ እሷ ብትጠይቀውም ጌታ የእሷን ጥያቄ በእሱ መለኮታዊ እቅድ ውስጥ አስገብቶ ምልክት አድርጓል።

ይቀጥላል.............................

Tuesday, 18 December 2018

የጌታ ክብር መገለጥ (ክፍል አንድ)


በዮሐንስ ወንጌል ተከታታይ ጥናት እየተማርኩት ካለው ውስጥ በምዕራፍ ሁለት መጀመሪያ ላይ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተለምዶ ወይም በአብዛኛ አጠራር በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት የተደረገውን የጌታ ክብር መገለጥ ላካፍላችሁ በመሻቴ የእግዚአብሔር መንፈስ በረዳኝ መጠን እንዲህ አቀርበዋለው። ወደ ዋናው ሀሳቤ ከመግባቴ በፊት ታሪኩን እንድታነቡ እጋብዛችኅለው።

'' በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ። ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ። '' (ዮሐ 2፥1-11)

ይህ ክፍል ብዙ የተባለበት ብዙ መፅሐፍ የተፃፈበት ብዙ ስብከት የተሰበከበት ክፍል ነው። ነገር ግን አብዛኛውን ሰምተን ያደግነው መፅሐፉ ሊናገረን ባሰበው መንገድ አይደለም የሰማነውም፣ ያነበብነውም፣ ያጠናነውም። ለዚህ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል የተለያዩ ርዕሶች ተሰጥተውታል። ለአብነት ያህልም በዋናነት የሚታወቁት የመጀመሪያው ተአምር፣ ቃና ዘገሊላ፣ በእርሱ አመኑ፣ የሚላችሁን አድርጉ፣ የድንግል ማርያም ምልጃ ልንል እንችላለን። በዚህ ታሪክ ውስጥ ብዙ ክንውን ተደርጓል ነገር ግን ታሪኩን የሚያገናኝ ሀሳቡን የሚሰበሰብና የሚጠቀልል ወይም ሁሉንም ድርጊትና ንግግሮችን የሚገዛ አንድ ወሳኝ ግንድ አለ። እርሱም የጌታ ክብር መገለጥ።

ቀድሞ የሆነውን ሰርጉን በምክንያትነት የደቀ መዛሙርቱ ማመን በውጤትነት የጌታ ኢየሱስ ክብር መገለጥ ማዕከልነት በማድረግ የተከናወነ ታሪክ ነው። በዚህ ታሪክ ብቻም አይደለም በአዲስ ኪዳን በዋናነት የጌታን ክብር መገለጥን ነው የሚነግረን ስለሆነም ለፅሁፋችን '' የጌታ ክብር መገለጥ '' የሚል ርዕስ ስጥተነዋል። በዚህ ታሪክ ውስጥ ማንም ይናገር፣ ምንም ይደረግ፣ ማንም ይሳተፍ በዛ የተደረገው ሁሉ የጌታ ክብር ለመግለጥ ነው።

ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት አብዛኛው በዚህ ታሪክ ዙሪያ የተደረጉ አስተምህሮዎች በተሳሳተና የጌታን ክብር መገለጥ በሚሸፍን መልኩ ነው የተላለፉት። ለዚህም አብዛኛው አስተምህሮዎች ርዕሶች ምስክር ናቸው። የአንድ ትምህርት ርዕስ የትምህርቱ ዋና ሀሳብን የሚይዝ ሲሆን በዙሪያው ያለውን ሁኔታ በሙሉ ለርዕሱ ተገዢ ያደርገዋል። በዚህ መልኩ የሚያስተምሩ አስተማሪዎችና መምህራን ይህን ያደረጉት አውቀውም ይሁን ሳያውቁ

ሀ) የጌታ ክብር ለማደብዘዝ

ይህንንም ለማሳካት ሶስት መንገዶችን ወይም ዘዴዎችን ተጠቅመዋል።

1) ርዕስ ሲመርጡ ከገቢር ግስ ይልቅ ተገብሮ ግስ ይጠቀማሉ (they prefer passive rather than active)  ድርጊቱን የሚገልፀውን ወይም ድርጊቱን የፈፀመውን አካል በመተው የድርጊቱን ባለቤት ማደብዘዝ/መሸፈን (ከድርጊቱ ማስወጣት ነው) እና ሌላ ነገር ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።
                                                                                           ምሳሌ ሀ:-
'' The man kill the Dog.'' ከሚለው ይልቅ  '' A Dog is killed.'' በመጀመሪያው ላይ ሰውዬው ውሻውን እንደገደለ ግልፅ ነው። የሰውዬውን ማንነት በድርጊት ተገልጿል። በመሆኑም አድራጊው የታወቀ ነው። በሁለተኛው ውሻው ተገሎ መሞቱን እንጂ ማን እንደገደለው አይገልፅም በዚህ ርዕስ ውስጥ ተናጋሪው አድራጊውን አስወጥቶቷል። ይህ ደግሞ መረጃነቱን ባሳጣት ክፍተት ፈጥሯል። ፍንጭ እንጂ ማስረጃው ደብዝዟል።

ምሳሌ ለ:-                                                                     '' ኢየሱስ ውሃውን ወይን ጠጅ አደረገው '' ከሚለው ግስ ይልቅ '' ውሃው ወደ ወይን ጠጅ ተለወጠ '' ይሉታል። '' አደረገ '' የሚለው ገቢር ግስ ሲሆን '' ተለወጠን '' በማምጣት ተገብሮ ግስን በመውሰድ ድርጊቱን የፈፀመውን አካል ቸል ይሉታል። ርዕሱ እውነት ይመስላል ግን ኢየሱስን አውጥቶታል።

2) ርዕስ ሲመርጡ ለአድራጊው ማንነት ላይ ትኩረት አለመስጠት። በቃና ዘገሊላ ጌታ ኢየሱስ ካደረገውና ከተገለጠው ክብር ይልቅ  ሰርጉ ላይ ማተኮር፣ በሰርጉ የታደሙ ሰዎች ላይ ማነጣጠር፣ የተደረገው ተአምራት ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ፣ የወይኑ መጣፈጥ ላይና ድንግል ማርያም የተናገረችውን ለጥጦ ማየት።

ምሳሌ ሐ:-
የኢየሱስ የመጀመሪያው ምልክት ከሚለው ይልቅ የመጀመሪያወ ምልክት ብቻ በማለት ኢየሱስን ማስወጣት። አዲሱ መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሚለው '' ኢየሱስ ውሃውን የወይን ጠጅ አደረገ '' ይላል። ይህ ሙሉ ነው በዛ ላይ Active ነው። ሙሉ መረጃ መስጠት ይችላል ነገር ግን ኢየሱስን በማውጣት የተፈጠረውን ምልክት ላይ ብቻ ማተኮር። የዚህም ዓላማ ኢየሱስን ማደብዘዝ ነው።

3) ታሪኩን በመቆራረጥ የተለያየ ርዕሶችን መስጠት። 11 ቁጥሮች ያሉት ይህ ታሪክ ብዙ የተቆራረጡ ርዕሶችን በመስጠት ዋና ሀሳብ እንዳይነሳ ማድረግ።                 

ምሳሌ መ:-                                                          የ2000 ዓ.ም የታተመው ሰማንያ አሐዱ መፅሐፍ ቅዱስ ይህን ታሪክ በሶስት ከፋፍሎ ርዕስ ስጥቶታል ግን ሶስቱም ስር ኢየሱስ የለም።
=}} ከቁጥር 1-2 በቃና ዘገሊላ ስለተደረገው ሰርግ ይላል
=}} ከቁጥር 3-5 ስለ እናቱ ምልጃ ይላል
=}} ከቁጥር 6-11 ስለ መጀመሪያ ተአምር ይላል።
መፅሐፍ ቅዱስ ሊነግረን ያለውን በመተው ሃይማኖታዊ ፓለቲካ ፍጆታ ሰበብ (For Denomination Purpose) የገቡ ርዕሶች እንዳሉ ማየት ቀላል ነው። እንዲገባ የተፈለገ ሀሳብ በግድ ተጠምዝዞ ገብቷል። ከእውነት ይልቅ ለብዙ ዘመናት የነበረውን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን አስተምህሮ የማስቀጠል አጀንዳ መያዙን መረዳት እንችላለን።

ይቀጥላል................................

Tuesday, 11 December 2018

የያዕቆብ መሰላል


'' ስብሀት ለእግዚአብሔር ወሰማያት ወሰላም ወምድር ስምረቱ ለሰው። '' 

ይህን መዝሙር ብዙ ጊዜ ዘምረነው እናውቃለን ነገር ግን የተዘመረበትን ዓላማው አስተውለነዋል ብዬ አላምንም። ይህ ምስጋና መላእክት ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በመወለዱ የተነሳ ያቀረቡት ሰማይና ምድር የተገናኙበት ምስጋና ነው። በጌታ የማዳን ስራ በመደነቅ በጠባብ ደረት ተወስኖ ሰው ሆኖ ሲያዩት እልፍ ሰራዊት ወደ ምድር መጡና የሰማይና ምድር መጋጠምን አበሰሩ። በእርሱ መሰላልነት ይወጡና ይገቡ  ጀመር።

ይህ አስቀድሞ ያዕቆብ መላእክት ሲመላለሱበት ያየው መሰላል እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።

'' ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ። ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፥ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ፤ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሣ፥ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ። ሕልምም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር። እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር። '' (ዘፍ 28፥10-13)

አዎ በምድር የተተከለ ወደ ሰማይ የደረሰ እንደ ኢየሱስ ያለ ማንም የለም። ኢየሱስ በመዋህለ ሥጋዌ ምድርን ከመርገጡ በፊት ገና ሳይፀነስ ለእናቱ ምሥራች ከተነገረበት ጊዜና ለዓለም በከፈለው ዋጋ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶ የሞትን ጣር በማጥፋት ድል አድርጎ ከተነሳ እንዲሁም ስፍራ ሊያዘግጅልን ወደ ግርማው ቀኝ በሄደበት እስከ ዕለተ እርገቱ ድረስ የመላእከት ወደ ምድር መውጣትና መግባት ይህን ያረጋግጣል። ማራናታችን ዳግም ሊወስደን ሲመጣም በአእላፍ መላእክት አጀብ እንደሆነም ሌላኛው ማረጋገጫ ነው።

ገና በግርግም ሳለ:-

"ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። " (ሉቃ 2፥13-14) 

የጌታ መወለድ ሰማይና ምድር የተገናኙበት ነው። ሁለቱንም የሚወክል በምድር ለምንኖር ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን መሰለ። ሰማይ ዙፋኑ የሆነው እርሱ በእግዚአብሔር መልክ የሚኖር ለዘመኑ መጀመሪያና ፍፃሜ የሌለው አልፋ ኦሜጋ ፊተኛውና ኋለኛው ሁሉን የፈጠረ የተባረከ አምላክ ነው። ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ።

ምድራዊያን ምድርን ብቻ ነው የነኩት ሊወክሉ የሚችሉት ሰማይ የለም። እግዚአብሔርም ሉአላዊ አምላክ ነውና ክብሩን ለሌላ በፍፁም አሳልፎ የሚሰጥ አይደለም። ሰማይን የሚወክል ከልጁ በቀር ሌላ አላዘጋጀልንም። መሰላል የተባለ ሁሉ ሰማይ አያደርስም። ኢየሱስ እውነተኛ መንገድ ነው። ለሰው ልጅ ሁሉ መሰማሪያ ቅጥር መሄጃ መንገዱ ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው።

" ኢየሱስም። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። " (ዮሐ 14፥6)

በትንሳኤ ጊዜ:-
መላእክት መወለዱን እንዳበሰሩት ሁሉ ትንሳኤውንም የተናገሩት እነርሱ ናቸው። ይህ መላእክት በጌታ ኢየሱስ ላይ ያላቸውን መመላለስ ያስረዳል። (ማቴ 28፥2-6)

በዕርገት ጊዜ:- 
ጌታ የመጣበትን ዓላማ የሰውን ልጅ ከኃጡአት ባርነት ነፃ በማውጣት ወደ አባቱ ሲያርግ መላእክት ነበሩ። (ሐዋ 1፥10-11)

ያዕቆብ ያየው መሰላል የተባለው ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሆኑ እነዚህ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች ቢሆንም ጉዳዩን ግልፅ የሚያደርግልን ቃል አለ። እርሱም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ አንደበት የተናገረው ነው። ናትናኤልን አውቅሃለው በማለቱ ባሳየው እምነት የተነሳ ገና ብዙ ነገር ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ እንዳለው። ናትናኤል ሊያየው ከሚገባ የሚበልጥ ነገር አንዱ የኢየሱስን አማናዊ መሰላልነት ነው። ለዚህ ነው ጌታ

" እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው። "(ዮሐ 1፥52)


'' የሰው ልጅ '' ደግሞ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን ኢየሱስን ለማመልከት እንደሆነ በወንጌላቱ በተደጋጋሚ ተነግረዋል። (እነዚህን ጥቅሶች ተመልከቱ ማቴ 16፥13 ሉቃ 2፥48 )

Friday, 7 December 2018

ዋላ


እንዴት ''ዋላ''ችሁ
የጌታ ኢየሱስ ሰላምና ፍቅር በያለንበት ይብዛልን!!! 

ተጠማች ነፍሴ ናፍቃህ እንደ ዋላ
የለኝም ዋስትና መድን ካንተ ሌላ
የሕይወት  ውሃዬ ፍሰስ በልቤ ላይ
ኢየሱስ ድምፅህን አሰማኝ ከሰማይ
                 
            ዋላ በአማርኛ ዲክሽነሪ ላይ እንደተገለፀው ከዱር አራዊት የምትመደብ፣ በበረሀ የምትኖር የፍየል ወገን ነች። መፅሐፍ ቅዳስ ዋላን በእንዲህ መልኩ ያነሳታል በመዝሙር 41፥1-2 

'' ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ? ''

             ዋላ እንደልቧ ሲጠማት በቀላሉ ውሃ ልታገኝ የማትችል የሁልጊዜ ተጠሚ ስትሆን ጥሟን ለማስታገስ ሌት ከቀን ወደ ምንጭ  ትዳክራለች። ዋላ ውሃ የምታገኘው ከአዳኟ ተደብቃና ካያትም ሸሽታ ብዙ ዋጋ ከፍላ ነው። አብዛኛውን ኑሮዋንም የምታደርገው በምንጩ ዙሪያ ነው።

             ዋላ ለስጋ ጥም እርካታ ውሃ ያስፈልጋታል እኛ ግን ጠጥተን ወደማንጠማበት የእርካታ ጥግ እንዳንደርስ በብዙ መሰናክሎች ተወጥረን እንገኛለን። ጌታችን  መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰማሪያዋ ሴት እንደነገራት

 "፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። "
(የዮሐንስ ወንጌል 4: 14)። ወደዚህ ዘላለማዊ እርካታ እንዳንቀርብ ጠላት ዲያብሎስ ብዙ ይታገላል። ዋላ በራሷ ጥረት ከአዳኟ ታመልጣለች እኛ ግን አሳላፊው ጌታ ያለአንዳች ያሳልፈናል። አንዳንዴ የእርሱ ጥበቃ በዝቶም እኛ ግን ራሳችን በራሳችን ላይ እንቅፋት እስከመሆን እንደርሳለን። 
       
             እኛም ከዋላ ብዙ የምንማር ይመስለኛል። እንደዋላ መውጣት መውረድ ሳይኖርብን ጌታ በሰራው ስራ ዘላለማዊ ጥጋብ ዘንቦልናል። እርሱ በመስቀል ላይ ተጠማው ብሎ መራራውን ሆምጣጤ ጠጥቶ ለእኛ ግን አንዴ ጣፍጦን ጠጥተነው ዘላለም እረክተን እንድንኖር የሚያስችለንን ፀጋ ሰጥቶናል ስሙ ይቀደስ። ታዲያ በዚህ እርካታ ውስጥ ሆነን የጌታን ድምፅ እንድንሰማ የማይወደውና የማይፈልገው ጠላት እንደሚያገሳ አንበሳ ዙሪያችን ይዞራል። ዋላም በቀላሉ ጠላት ሊይዛት የሚችለው ጥሟን ከምታገኝበት ከምንጩ ስፍራ ሲሆን እኛንም ከዘላለማዊ ምንጭ እንዳንገናኝ ከእርካታችን ትይዩ ሆኖ ይጠብቀናል። ከምናውቀውም ከማናውቀውም ጠላት የሚጠብቅ የማይተኛ፣ የማያንቀላፋው አምላካችን ክብርና ምስጋና አምልኮትና ውዳሴ ለእርሱ ይሁንለት።

               እግዚአብሔርን በተጠማነው መጠን እንረካለን። ትናንት ከነበረን እግዚአብሔርን መጠማት ዛሬ ላይ በይበልጥ ሊኖረን ይገባል። ነገ ደግሞ ከዛሬ። እግዚአብሔርን የምናወቀው ልናውቀው በፈለግነው መጠን ነው። ባለን አቅም ቃሉን እየታጠቅን፣ ለቃሉም እየታዘዝን፣ በፀሎትም እየተጋን እንድንኖር የእግዚአብሔር ጸጋ ይርዳን። በሚያስፈልጋችሁም  ጊዜ የሚረዳ የእግዚአብሔር ጸጋ አለ ተብሎም እንደተፃፈ በነገሮች ሁሉ ማድረግንም መፈለግንም በእኛ ላይ  የሚሰራ አምላክ ያስችለን።

ኢየሱስ


ኢየሱስ የሚለው ስም ትርጉም ሕዝቡን ሁሉ ከኋጢአታቸው የሚያድን አዳኝ ማለት ነው። ስሙ ከማዳን ጋር የተገናኘ ሲሆን አባታችን እግዚአብሔር እንደባለጠግነቱ መጠን ለእኛ በበደላችንና በኋጢአታችን ሙትን ለነበርነው እንድንበት ዘንድ የሰጠን በዚህም ዓለም ደግሞ ለሚመጣውም ዓለም ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ነው።

ስሙ ማትረፊያ ነው። ከዚህ ስም ብቻ የተነሳ መፅሐፍ ቅዱሳችን አንዲህ በማለት ትርፋችንን ይነግረናል።

1) ከዘላለም ፍርድ ያድናል።

"፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል። " (የሐዋርያት ሥራ 10: 43)

2) ከሃጢያት ያድናል።

"፤ ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። " (የማቴዎስ ወንጌል 1: 21)

"፤ መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና። " (የሐዋርያት ሥራ 4: 12)

3) የልጀነት ስልጣን ይሰጣል።

"፤ ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ "
(የዮሐንስ ወንጌል 1: 12)

4) ወደ እግዚአብሄር አብ ያቀርባል።

"፤ እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ። " (የዮሐንስ ወንጌል 15: 16)

5) ለሚጠሩት ሁሉ ባለጠጋ የሆነ ስም ነው፡፡

"፤ በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ "
(ወደ ሮሜ ሰዎች 10: 12)

6) የምንበረከክለት ብቸኛ ስም።

"፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ " (ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2: 10) ስለሆነም ለሌላ ስም ከቶ እንዳንበረከክ ይህ ያስረዳል።

7) ድርጊት መፈፀሚያ።

"፤ እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። " (ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3: 17)

እነዚህ ጥቂቶች ናቸው። ይህ ስም ለእኛ ለክርስቲያኖች የምንመካበት አዝለን ይዘነው የምንሄደው ከብዙ ነገር የምንወጣበት ማምለጫችን ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ማለት በአሁን ሰአት ብዙ ነቃፋን የሚያስገኝ እየሆነ መሄዱ የተለመ ሆኗል።

ብፁህ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የተባሉ አባት ተናገሩት የተባለው ትዝ አለኝ። አንድ ሰካኪ በስብከቱ ውስጥ ኢየሱስ እያለ በተደጋጋሚ በመጥራቱ ወደ እኝህ  አባት ቅሬታ ይቀርብበታል። አቡኑም ቅሬታው ምንድነው ብለው ይጠይቃሉ። ቅሪ የተሰኘውም ሰው ይህ ሰው ጌታችን በቁንፅላ ብቻ ኢየሱስ እያል በአንድ ስበከት ውስጥ በተደጋጋሚ ጠራው እንዴት ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይልም ድስት እንኳ ሁለት ጆሮ አለው አይደለም እንዴ አባታችን ይላል። እሳቸውም አንተ ሞኝ ድስት ራሱን አይችልም ኢየሱስ የሚለው ስም ግን ብቻውን ኋያል ነው። ያ '' ኢየሱስ '' ነው ጌታችንና መድሃኒታችን አሉትና መለሱት።

ኢየሱስ ከሚለው ስም ጋር በተያያዘ ሁላችንም በየራሳችን የማንረሳው ክስተት ይኖራል ብዬ አስባለው። እኔ ስሙ ከሆነልኝና በሰሙ ካገኘውት መዳንና በረከት ሌላ የማልረሳው አንድ ትወስታ አለኝ።

የዛሬ ዘጠኝ ወይም አስር ዓመት ገደማ ከስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ወጥቼ በዋናው በር ላይ የሜክሲኮ ታክሲ ይዤ መሄዴ ትዝ ይለኛል። አሁን የማላስታውሰው ነገር ግን በወቅቱ ለእኔ ወሳኝ ሆኖብኝ  የነበረ ጉዳይ ነበረ። አካሌ ታክሲ ሲሳፈር አእምሮዬ በሀስብ ባህር ተሳፍሮ ጭልጥ አርጎኛል።

 ታዲያ በዚህ ሀሳቤን በሙሉ በወሰደው ነገር እልም ካልኩበት ሰመመን ያነቃኝ ገጠመኝ ለእኔ አዲስ ክስተት ነበረ። እንዴትና በምን ሁኔታ ከተሳፈረኩበት ከስድስት ኪሎ አራት ኪሎ ታክሲው እንደደረሰ እንኳን አላወኩም፣ ነገር አንዳች ከተመሰጥኩበት ሀሳብ የሚያነቃ ድምፅ በድንገት በኋይል በጆሮዬ ገባ።

አንድ  ረዥም ቀጠን ያለ የቀይ ዳማ ጎልማሳ ከእሱ የወጣ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር ተጠምጄ ከነበረው ወሳኝ ሀሳቤ ሁለንተናዊ መነቃቃት በሚፈጥር ሁኔታ ከተሳፈርኩበት የሀሳብ ባህር በድንገት መለሰኝ።

ሰውዬው '' ኢየሱስ ጌታ ነው '' እያለ  በተደጋጋሚ ሳያቋርጥ ይናገራል። ሳልፈልግ ከሀሳቤ በመመለሴ ብቻ ሳይሆን የሰውዬው ድምፅ ጉልበት ለጆሮዬ ድንገት የመጣ አደጋ እስኪመስለኝ ድረሰ አስደንግጦኝ ስለነበረ እጅግ ተናድጄ ስለነበረ አፀፋዬን መለስኩለት እንዲህ በማለት
'' ኢየሱስ የጌቶች ጌታ የንጉሶች ንጉስ የአማልክት አምላክ  ነው'' ። እናም በወቅቱ አፀፋዬን በመመለሴ ውስጤን አረጋጋው። ልክም እንደሆንኩኝ ይሰማኝ ነበረ።  እውነት ነው ኢየሱስ የጌቶች ጌታ የንጉሶች ንጉስ የአማልክት አምላክ  ነው ነገር ግን መፅሐፍም እንደሚል ኢየሱስ ጌታ ነው።

"፤ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። "
(ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2: 11)

ስለዚህም የእኔ መልስ መሆን ይገባው የነበረ አሜን እንጂ አፀፋ አልነበረም። በወቅቱ በነበረው መናደድ '' ኢየሱስ ጌታ ነው '' የሚለውን በመቃወም የጌቶች ጌታ ማለቴ ልክ አልነበረም። እርሱ ጌታ የሆነው ነው የጌቶች ጌታ። አዎ ምላስም ሁሉ እንደሚል ቃሉ ምላሴ ለዚህ እውነት ህብረት ሊያደርግ ሲገባ የተነገረውን ቃል በመተው ሰውዬውን በመመልከቴ አፀፋ ሰነዘርኩ። ሰውን መመልከት መጨረሻው ጥፋት ነው። የሌላን መቃወም የእኔን ልክ አያረገውም። የሌላን መኮነን የእኔን እውነት አያረጋግጥም። የእሱን በማፍረስ የእኔን አይገነባም።

ኢየሱስ ከስም ሁሉ በላይ ነህ። ስምህን ሰምቶ ሞት ይደንግጥ ቀላያትም ይሰንጠቁ አለማመን ይራቅ ተብሎ እንደተፃፈ የስምህ ኋይል ስለገባኝ አመሰግናለው። እርቃንህን ስለእኔ በመስቀል የተቸነከርክ ስምህን በዘመኔ ሁሉ አውጃለው። ኢየሱስ ስምህን ለአዋጅ እንጂ ለሹክሹክታ እንኳ አይመችም።

በጌታ ደስ ይበላችሁ


                  ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ!!!
                                  ፊሊጵ 4፥4
        ደስታ ለሁሉም የሰው ልጅ የተሰጠ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የደስታቸው ምንጭ ዘመናዊ መኪና፣ አካውንታቸው ውስጥ የተቀመጠ ዳጎስ ያለ ጥሬ ገንዘብ፣ ጥሩ ሥራ፣ ዝና፣ ትልቅ ቤት በዘመናዊ  ፈርኒቸሮችና ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች የተሞላ እንዲሁም ማራኪ ተክለ ሰውነት ለደስታ ቁልፎች እንደሆኑ የሚሰማቸው ብዙዎች ናቸው። ይህ ሁሉ ግን ጊዜያዊ ከመሆናቸውም ባሻገር እውነተኛ ደሰታ መስጠት አይችሉም።
           ደስታ ከላይ ከአባታችን ከእግዚአብሔር የሚስጥ በፍፁም ሀሴት የምናገኝበት በምናገኘውና በምናጣው ነገር ላይ ያለተመረኮዘ ነገር ግን ራሱን የቻለ ልዩ መለኮታዊ ሙላት ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሁሌ በጌታ ደስ እንድንሰኝ ያዛል።  በትክክል እንደ እግዚአብሔር ቃል ለሚመላለስ ሰው ለዚህ ደስታ ተገዢ ነው። ደስተኞች እንዳንሆን የሚያደርጉንና የሚያስጨንቀንን አንዳች ባለማስቀረት ጌታ ለእያንዳንዳችን ፈንታ ሆኖ ወስዶልናል።
          በዚህ እንደ እንግዳና መፃተኛ ሆነን በምንኖርበት ምድር በየትኛውም፣ በማናቸውም ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ ብንሆን ፈልገን ብናጣ፣ ሽተን ቢቀር፣ ሞክረን ባይሳካ፣ ጠይቀን ብንከለከል፣ ፈልገን ባናገኝ፣ ጠብቀን ባይመጣ፣  በጌታ ያለንን ደስታ የሚያሳጠና ከሆነ That is the question?
         የደስታችን ምንጭ ሊሆን የሚገባው ቃሉ እንደሚለው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለዚህም ደሰታችን የተጠበቀ እንዲሆን በሚያሰፈልገን ጊዜ የሚረዳን የእግዚአብሔር ፀጋ አለና። ሐዋርያው ቅዳስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በፃፈው መልእክቱ  በምዕራፍ 4፥13 ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ ይላል። ለሚያስፈልገን  ማንኛውም  ውጫዊ ነገር (ለምንም ነገር) ውስጣዊ ዝግጁነት ሊኖረን እንደሚገባ ያስገነዝበናል። ኋይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ለምንም ነገር ዝግጁ ነኝ ማለት ይገባናል።
        እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ነን፣ የእርሱ ልጆች ከሆንን ደግሞ የምንመራው በእርሱ መንፈስ ነውና እውነተኛውን 
 የደስታ እርካታ ወደምናገኝበት መቅረብ አለብን። የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። (1ኛ ዮሐ 3፥1) እግዚአብሔር ለእኛ ፍቅሩን የገለጸው አንድያ ልጁን በመስጠት ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ ምንም ስጦታ የለምና ደስታችንን በጌታ ሙሉ እናድርገው። ካነበብኩት አንድ ታሪክ ልንገራችሁ
         በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ጊዜ በአንድ አገር አየር ኋይል ውስጥ የሚሰራ አውሮፕላን አብራሪ ነበረ።  ይህ ሰው ብቸኛ አንድ ወንድ ልጁንና ባለቤቱን በሞት የተለዩት ሲሆን በወቅቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት ያበራት የነበረችው አውሮፕላን ተመታ ትወድቃለች እሱም ይሞታል። ታዲያ ሰውዬው በሕይወት እያለ በዓለም በሚታወቁ ሠዓሊያንና ቀራጺያን የተሰሩ እጅግ ውድ ሥዕሎችና በከበሩ ማህድናት የተሰሩ ጌጦችን ይሰበስብ የነበረ ሲሆን ምንም ወራሽ ባለመኖሩ ስሞት እነዚህ ንብረቶቼ በጨረታ ተሽጠው ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይሰጡልኝ ብሎ ስለነበር በጠበቃው አማካኝነት ንብረቶቹ ለጨረታ ይቀርባሉ።
         ጨረታውን ለመሳተፍ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍል የተሰበሰቡ ቱጃሮችና ጨረታውን ለመዘገብ የታደሙ ጋዘጠኞች ጨረታው በሚካሄድበት አዳራሽ ውስጥ ተሰግስገዋል። የሰውዬው ጠበቃ መድረኩን በመቀበል የሰውዬውን የመጀመሪያ ኑዛዜ አነበበና ከመንግስት ለተመደቡት አጫራች ስፍራውን ለቀቀ። በኑዛዜው መሰረት በቅድሚያ መሸጥ ያለበት የተናዛዡ ብቸኛ ልጅ መልክ የሚያሳይ በእጅ የተሰራ ሥዕል ነበረ የዚህ ሥዕል ሰዓሊውም ሆነ የተሳለው ልጅ ታዋቂ ባለመሆናቸው የተነሳ ጨረታውን የሚሳተፍ ሰው ጠፋ። ሁሉም ፀጥ አለ ሥዕሉንም የሚፈልገ ሰው ጠፋ። ጨረታውን ሊመለከት ከገባ ውስጥ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የሟች አገልጋይ የነበረ አንድ ሰው ነበረ። ይህ ሰው የተናዛዡን ሰውዬ ልጅንም ከልጅነቱ ጀምረው ያውቁት ስለነበር ምስሉን በእጁ ቢያስገባ መልካም እንደሆነ አሰበ። አንድም ማንም ሰው ለዚህ ምስል ፍላጎት ስላላሳዩና ሠዓሊምው በማንም የማይታወቅ በመሆኑ፣ አንድም ደግሞ ልጁን ስልሳደጉት ማስታወሻ ይሆናቸው ዘንድና አነስተኛ ዋጋ ቢጠሩ የሚፎካከር አይኖርም ብለው ስላሰቡ እጃቸውን አውጥተው አነስተኛ ዋጋ ይሰጣሉ። ሰውዬውም እንዳሰበው ማንም ምሥሉን ለመግዛት ፍላጎት ሳያሳይ ቀረና ሰውዬው ሥዕሉን አሸነፈ።
        በዛው ቅፅበት አጫራቹ ክብራትና ክቡራን ጨረታው ተጠናቋል ብሎ ተናገረ። ሁሉም የሰሙትን ሊያምኑት አልቻሉም ባሉበት ደንዝዘው ቀሩ። አጫራቹም በመቀጠል በኑዛዜው መሰረት የልጁን ሥዕል በጨረታ ያሸነፈ ያለምንም ተጨማሪ  ክፍያ ለልጁ በተሰጠው ዋጋ ሁሉንም እንደሚወስድ ኑዛዜው ያስገድዳል ብሎ የጨረታውን ማለቅ በያዘው የአጫራች መዶሻ ጠረጴዛው መታ።

ልጁ ያለው ሕይወት አለው።

ደግሜ እላለው ደስ ይበላችሁ።

ይህ ነው የእኛ ደስታ ሊሆን  የሚገባው። በዚህ መለኮታዊ እርካታና ደስታ ውስጥ ሁሌም መገኘት እንዲሆንልን እየተመኘው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ የእዚአብሔር አብ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።

ሥር ሰዳችሁ


የክርስትና ሕይወት ማደግ የሚጀምረው ወደ ታች ነው። መሰረቱ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። የሚታየው ማንነታችን የሚቆመው በመሰረቱ ነው። አንድ ዛፍ ወይም ትልቅ ሕንጻ መቆሙ የሚመሰረተው በያዘው መሰረት ነው። ክክርስቲያንም እንዲሁ በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ሕይወቱ ሊመሰረት የግድ ይሏል።

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር
'' ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ። ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም። ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ። '' (ሉቃ 6፥47-49)

ከፍታችን የሚለካው ወደ ታች ባደግንበት መጠን ነው። በቃሉ ተሞልተን  ሕይወታችንን ቃሉ እንደሚያዘው ብንኖር ወይም ብንታዘዝ እግዚአብሔርን ደስ እናሰኛለን እኛም አንወድቅም አልጥላችሁም ከቶ አልተዋችሁም ከእጄ መዳፍ ማንም አይወስዳችሁም ብሏልና። በአንፃሩ ደግሞ ካየነው የጠላት ዲያብሎስን ሽንገላ በቃሉ እየተቃወምንና እያሸነፍን እንድንኖር ያስችለናል። ስለሆነም ሥር ሰደን በማደግ ወደ ከፍታ መውጣት በክርስቶስ ትምህርት መሆንን ይጠይቃል።

" ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። " (ቆላ  2፥7)
በአጭሩ ከዚህ የምንረዳው ሥር በመስደድ የሚመጣ ጉዳይ አለ እነርሱም መታነፅና መጽናት። እንዚህ የሌሉበት ሥር መስደድ ከንቱ ነው። እንደቃሉ ያልሆነ ሥር መስደድ ሰማይ የማያውቀው ነው። ነገር ግን በነዚህ የታነፀ ሥር መስደድ ወደ ላይ የመውጣታችንን አቅም ይወስናል።

ያለን ምርጫ ሁለት ነው ወይ እንደ አረም መሬት ላይ ተንሳፎ በመኖር ነፋስም ሆነ ዝናብም ሲመጣ መርገፍ ወይ እንደ ዛፍ ስር ሰደን በመመስረት ምንም ቢከሰት ባለንበት መጽናት። የሚበልጠውን ቃሉ በግልፅ ነግሮናል በክርስቶስ ትምህርት ራሳችንን አንፀን በማደግ የእግዚብሔር መንግስት አገልጋይ እንድንሆን ኢየሱስ ጸጋና ኋይል ያብዛልን።

ማዳን የፈጣሪ የባሕሪው ገንዘብ ስለ ሆነ በፍጡር መዳን አይቻልም።



"እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም።" (ኢሳ 43፥11)

ማዳን የእግዚአብሔር የባሕሪው ገንዘቡ ነው። መላእክትም ሆኑ ሌሎች ፍጥረታት የእግዚአብሔር የባሕሪይ ገንዘብ የሆነውን ማዳን የራሳቸው ሊያደርጉት አይችሉም፤ አይፈልጉምም። ነገር ግን ይህን ማዳን በመላላክ ሊያገለግሉ ይችላሉ። ለምሳሌ:- 
እግዚአብሔር ሠለስቱ ደቁቅን (አናንያ አዛርያ ምሳኤል) ከእሳት ዳንኤልን ከተራቡ አናብስት ሊያድናቸው በፈለገ ጊዜ ማዳኑን የፈጸመው በመላእክት ተልእኮ በኩል እንደ ሆነ ከቅዱስ መጽሐፍ እናነባለን።

ሆኖም ይህ ከመከራ ሥጋ የማዳን ሥራ አሁንም የእግዚአብሔር እንጂ የተላከው መልአክ ገንዘብ አልነበረም። ለዚህም ነው ናቡከደነጾር እግዚአብሔር የፈጸመውን የማዳን ሥራ ካየ በኋላ

 ''...#መልአኩን_የላከ_ከአምላካቸውም_በቀር_ማንንም_አምላክ_እንዳያመልኩ_ለእርሱም_እንዳይሰግዱ_ሰውነታቸውን_አሳልፈው_የሰጡትን_የንጉሡንም_ቃል_የተላለፉትን_በእርሱ #የታመኑትን_ባሪያዎቹን_ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ። ''   ሲል የማዳኑን ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን ያመሰገነው። (ዳን 3፥2)

ዳንኤልንም ዳርዮስ፣                                                        " የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን? " ሲል በጠየቀው ጊዜ ለዳርዮስ በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና በአንተም ፊት ደግሞ ንጉሥ ሆይ አልበደልሁምና #አምላኬ_መልእኩን_ልኮ_የአንበሶቹን_አፍ_ዘጋ እነርሱም አልጎዱኝም (ዳን 6፥20-22) ሲል ያዳነውን እግዚአብሔርን በሚገባ ክብር አክብሮታል።

ከመከራ ሥጋ መዳንን በተመለከተ ይህን ሁሉ ካየን፣ ከመከራ ነፍስ መዳን (ከኋጢአትና በኋጢአት ምክንያት ከመጣብን ፍዳ መዳን) እንዴት በፍጡራን ሊፈጸምና ሊሰጥ ይችላል? የሚል ጥያቄ ከባድ አይሆንብንም። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን በተመለከተ የተናገረውን ከዚህ እንመልከት።

''ወኢያንሥአ ለነ ሊቀ ካህናት እመላእክት ወኢ እም ኀይላት እለ እሙንት ይቀውሙ ዐውደ መንበሩ አላ አሐዱ ለሊሁ ወረደ ወተሠገወ እምህላዌነ ወኮነነ ሊቀ ካህናት ወአዕረገ በእንቲአነ ሥጋሁ መሥዋዕት ለአቡሁ በአብጽሐነ ሎቱ በዘቦተ ሐመ''

ትርጉም
" ዙፋኑን ከብበው ከሚቆሙ ከመላእክት ከኀይላትም ወገን ሊቀ ካህናት አልሾመልንም። እርሱ አንዱ ወደዚህ ዓለም ወርዶ ባሕሪያችንን ብሕርይ አድርጎ ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) ሆነን እንጂ ስለ እኛም ሥጋውን መሥዋዕት አድርጎ ወደ አባቱ አቀረበ፤ በታመመበት በሥጋው ለእርሱ ገንዘብ ለመሆን አበቃን ''

ከዚህ ሁሉ ማስረጃ የምናስተውለው ነጥብ ቢኖር፣ መጸሐፍ ቅዱስም ሆነ የአባቶች ትምህርት በመላእክት የተፈጸመ ወይም የሚፈጸም ከኋጢአት ሰውን የማዳን ሥራ ፈጽሞ የሌለ መሆኑን ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች ሁሉ መላእክትን ያከበርን መስሏቸው ከመላእክት መዳንን በመፈለግ እግዚአብሔርን እንዳያስቆጡና ራሳቸውንም ከእውነተኛው የመዳን መንገድ እንዳያወጡ በክርስቶስ ፍቅር እንመክራለን።

በአሁን ሰአት የብዙዎችን ጥያቄ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሀሳብ እየመለሰና እያስተማረ ከሚገኘው በመጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር የተጻፈው ምርጥ መጽሐፍ ከሆነው '' መዳን በሌላ በማንም የለም '' ከሚለው ከገጽ 55-56 የተወሰደ። መጽሐፉን በመግዛትና በማንበብ እንድትጠቀሙበት በጌታ ፍቅር ጋበዝኳችሁ።

በሥራ መዳን


መዳን በሥራ ነው።
ነገር ግን በማን ሥራ?

እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን በቃሉ ከፈጠረ በኋላ የሰው ልጅ በእጁ አበጀው ይህ ማለት እርሱ ሥራ ሰርቷል ለማለት ሙሉ ድፍረት ይሰጠናል። እንዲሁም ደግሞ አዳም ትዕዛዝ ከተላለፈ በኋላ ዳግም ሥራ በመስራት የቁርበትን ልብስ አለበሰው። የሰውማ ሥራ ራሱን እንኳ የማይሸፍን ከየበለስ ቅጠሎች ሰፍቶ ግልድም ማድረግ ነው (ዘፍ 3:፥7)። የእግዚአብሔር ልብስ ግን ማንነትን የሚሸፍን፣ ነውርን የሚደብቅ፣ እርግማንን የሚያርቅ ነው። ይህን ልብስ  እግዚአብሔር ዝም ብሎ ከየትም አላመጣውም ይልቁንም ለሁለተኛ ጊዜ ስራ በመስራት ዳግም በእጁ ጣልቃ ገብነት ነው። እግዚአብሔር ስለ ሰው ስራ መስራት የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይደለም ከፍጥረቱ ጀምሮ ነው ማዳኑም እንዲሁ። በአሮጌው ኪዳን እንደተፃፈ

" እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም " (ኢሳ 43፥11) ያለው የሰው ልጅም ሆነ ሌላ የነፍስ ድህነትን መስጠት የሚችል ማንም ስለሌለ ነው።

እንዲሁም በአዲሱም ኪዳን መጽሐፍ ቅዱሳችን ይህን ይደግመዋል። አይደለም አንድያ ልጁ ላይ በጨከነበት በዚህ በጌታ ኢየሱስ  ጸጋ ዘመን በዚያኛውም ስለ መሲሑ መምጣት በተነገረበት በጥላው ዘመንም የሚያድን አልነበረም። እግዚአብሔር እንዴት ልጁን ኢየሱስ ላይ ጨክኖ  የማዳንን መንገድ በሌላ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል?

አዎ እግዚአብሔር ያዘጋጀው የመዳን መንገድ ሥራ ነው ነገር ግን በማን የተባለ እንደሆነ በኢየሱስ ሥራ ብቻ ነው ይለናል መጽሐፋችን።

Saturday, 1 December 2018

የሚመካ በጌታ ይመካ!


       '' የሚመካ በጌታ ይመካ''  (2ኛ ቆሮ 10፥17)

ትላንት የነበረህ ነገር ዛሬ አይኖርህም። ማንም ባለበት መቀጠል እንዳይችል የተፈጥሮ ግዴታ ነው። ትናንት ላይመለስ እንደሄደ ሁሉ ዛሬም ትናንት መባሉ አይቀሬ ነውና በዛሬው ማንነትህም ላይ ራስህን አታቁም። በነበረውና ባለው በሚኖረውም አልፋ ኦሜጋ በሆነው በእግዚአብሔር ተማመን።  እርሱ ከፍታና ዝቅታ የሚታዘዙለት ሁሉን ማድረግ የሚችል በኋይሉ ብዛት በችሎቱም ብርታት እንድ ስንኳ የማይታጣው፣ ከመንፈሱ የማይሰፍር ወደ ላይ ብትወጣ እርሱ በዚያ አለ፣ ወደ ታች ብትወርድ እርሱ በዚያ አለና ከእርሱ እይታ አትወጣም። እርሱ የማያንቀላፉ ቸልታ የሌለበት ተመልካች ነውና እርሱን ተመካ።

ችግር ቢመጣ ብለህ ተጠንቅቀህ ይሆናል ነገር ግን የተጠነከክለት ነገር በራሱ ከፈራከው ወጥመድ አያስመልጥክምና አትመካ። የቱንም ያህል የጥንቃቄ ሰው ብትሆን ከምታውቀውም ከማታውቀውም፣ ካስተዋልከውም ካላስተዋልከውም የጠበቀህ እርሱ ብቻ ነው። አይተህ የተሻገርከውም ሳታይ የተሻገርከውም እግዚአብሔር ፈቅዶልህ ነውና በጥበቃው እምነት ይኑርህ ያ ነውና እውነተኛ ትምክህት።

የእነ እንትና ዘመድ ነኝ ብለህ ራስህን የተሻለ አማራጭ እንዳለው ሰው አድርገህ አትቁጠር። ከሰው መዛመድ ማምለጫ አይደለም ይልቅ እግዚአብሔርን በልጁ በኢየሱስ ተወዳጀው። ገና ችግር ሳይመጣ በተጠባባቂነት የያዝከው የሰው መከታ ካለ አራግፈው ሰው የጌታ ጸጋ ካልረዳው በቀር እንኳን ለአንተ ለራሱም አይሆን። ስለ አንተ ማንም ከእግዚአብሔር ፊት የሚቆምልህ የለም ከኢየሱስ በቀር። አንተን ያለ ኢየሱስ አየህ ማለት ፍፁም በደለኛና ሞት የሚገባህ ነህ። በሕይወት ዘመንህ ሁሉ በኢየሱስ መሆንህን ለአፍታ እንኳ አትርሳው። ትምክህትህ ይህ ነው።

የፈጠረህ በዓላማ ነውና የምትኖረውም በተፈጠርክበት ዓላማ ይሁን። በዓላም የፈጠረህ እርሱ ስትቆሽሽም የሚያነፃ እርሱ ነው። አፈጣጠርህንም አነፃፅህንም ያውቅበታል። መፍጠር የእርሱ እንደሆነ ሁሉ ማዳንም ገንዘቡ ነው። እነ እከሌ የቱንም ያህል በእርሱ ፊት ሞገስ ቢኖራቸውም እነሱ እንኳ በራሳቸው በፊቱ መሆን አይችሉምና በሰው አትመካ። መጽሐፍ እንደሚል '' መላእክት ስንፍና ይከሳቸዋል ሰማያትም በፊትህ ንጽሐን አይደሉም '' እኛማ እንዴት እናድፍ ይሆን???

ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ይሆን ዘንድ፥ ከሴትስ የተወለደ ንጹሕ ይሆን ዘንድ እንዴት ይችላል? እነሆ፥ ጨረቃ እንኳ ብሩህ አይደለም፥ ከዋክብትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም። ይልቁንስ ብስብስ የሆነ ሰው፥ ትልም የሆነ የሰው ልጅ ምንኛ ያንስ! (ኢዮ 25፥4-6) 

ወዳጄ ትታይበት ዘንድ የተፈቀደልህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ማንንም አዳኝ አድርገህ አትመካ። መዳን በኢየሱስ ብቻ ነውና በዚህ ተመካ።