ፒስቲስ በግሪክ ቋንቋ እምነት ማለት ሲሆን ትርጉሙም ሙሉ የልብ መሰጠት፣ በጥልቀት የተያዘ ከአመክንዮ ኋይል በላይ የሆነውን እግዚአብሔርን ማመን ማለት ነው። ከአህምሮአዊ እውቀት ወይም አቀባበል በላይ ማለት ነው። ፒስቲስ የመወሰን ትርጉምም አለው። የዚህ የፒስቲስ እምነት ያለው አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር እውነት መሆኑን ጥልቅ በሆነ የልብ መሰጠት በመግባባት የተቀበለና በልበ ሙሉነት የሚጠብቅ ወይም እንደሆነ አድርጎ የደመደመ ሰው ማለት ነው።
የዕብራዊያን ፀሐፊ ሐዋርያው ጳውሎስ እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። (ወደ ዕብራውያን 11: 1) ይላል። የዚህ ዓይነት እምነት ለእግዚአብሔር መንግስት የተገባና ለመንግስቱም የመገበያያ ገንዘብ ነው።
ሰማያዊው ሀገር አሁን ባይታየንም ሀገር ሲሆን መገበያያውም እምነት ነው። በዚህ ዓለም ገንዘብ ሳይኖረን አንድ ነገር መግዛት እንደማንችል ሁሉ ካለእምነት ከሰማያዊ መንግስት ንጉስ ጋር ግንኙነት አይኖረንም ማለት ነው። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም ተብሎ እንደተፃፈ።
የማታምነውን ነገር ለመቀበል አትችልም የማትጠባበቀውንም ነገር ለማየት አትችልም። ታዲያ ይህ እምነት የሚገበያየው ተስፋ ባደረገው ላይ በሚኖረው እምነት ነው። የሰው ልጅ በተፈጥሮ አንድን ነገር በመገመት (predict በማድረግ ወይም ይሆናል በሚል) አውጥቶና አውርዶ ስለ አንድ ነገር ይወስናል። እምነት ያለው ሰው ግን ግምትን አይጠቀምም ይልቁንም እንደሚሆን ቆጥሮ በዛ ጉዳይ ላይ ይወስናል እንጂ። እግዚአብሔር ያደርገዋል የሚል የእምነት ገንዘብ መጠን አለው።
ሙሴ በንጉስ ፈርዖን ቤት እንደ ልዑል አድጎ ነገር ግን መፅሐፍ እንደሚል በእምነት ስሌት ልጅ መባልን አልፈለገም።
ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና።
ዕብ 11፥24-26
እምነት ያለው ሰው በሚያየው ሳይሆን በሚያምነው ይኖራል። ሙሴ መጨረሻውን በእምነት አይቶ ጊዜአዊ ጥቅሙን ተው። አዎ ሙሴ እምነቱ ገንዘብ ሆነለት አሻግሮ መመልከት ስለቻለ መግዛት ያለበትን ገዛ። በምድር ላይ በሚያየውን ሳይሆን በእግዚአብሔር እውነተኛነት በእርሱም የተስፋ ቃሎች ላይ የተመሰረተ እምነት የነበረው ለእግዚአብሔር መንግስት የመግዛት አቅም እንዲኖረው አደረገ። እምነት ያሰላል!!!
ኖህንም ብንመለከት
ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ስዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥ በዚህም ዓለምን ኰነነ፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።
ዕብ 11፥7
እግዚአብሔር መርከብ እንዲሰራ ሲያዘው ኖህ አንድም የዝናብ ጠብታ ሳያይ ነው መርከብ የሰራው። በጠራራ ፀሐይ መርከብ ሲሰራ ያዩት ሁሉ እንደ እብድ ሳይቆጥሩትም አልቀሩ። እንኳን መርከብ ይቅርና ዝናብ ይዘንባል ብለህ ተማምነህ ዣንጥላ ይዘህ ሲያዩህ እንደታመምክ ሊቆጥሩህ ይችላሉ። ኖህ እነሱ የማያውቁትን እሱ በእርግጠኝነት አውቋል። ምክንያቱም እምነቱ ተስፋ የሚያደርገውን እውነት በእምነት ስሌት አስልቶ ገዝቶት ነበረና። እምነት ያሰላል።
በብዙ ችግር ውስጥ ያላችሁ፣ ተስፋ የምታደርጉት የማይመስል ለሆነባችሁ፣ በይሆናልና አይሆንም መካከል ውስጥ ለተቀመጣችሁ፣ አሁን በዓለም በምታዩት ነገር ተወስዳችሁ ብሩኩ ተስፋችንን የዘነጋችሁ እምነት ያሰላል። በማስላት ወደሚገኝ ክብር የሚያመጣ በእምነት መገበያያ ገንዘብ እንያዝ አላለው። በድጋሚ እምነት ያሰላል።
ደግሞም በኑሮአችሁ ሰልፍ በዝቶባችሁ ላላችሁ፣ አንዳች ነገር እንዲሰጣችሁ እግዚአብሔርን ጠይቃችሁ መልስ በመጠበቅ ላይ ላላችሁ፣ በእግዚአብሔር በረከት ላይ ሳይሆን በበረከቱ አምላክ፣ በበረከቱ ሰጭ፣ ወይም በበረከቱ ምንጭ እግዚአበሔር ላይ ባለ እምነት ላላችሁ ይህ የመንግስቱ መገበያያ ገንዘብ እንዳይባክን ፀንታችሁ እንድትቆዩ እያሳሰብኩ በእምነት የገዛችሁት ይሆናል፣ በእርግጥ እግዚአብሔር ታማኝ ነውና ያደርገዋል። በእምነት አስልታችሁ በያዛችሁት ተስፋ እንድትፀኑም ምክሬ ነው። በእምነት ማስላት መኖራችሁን ቀጥሉበት አላለው።
እምነት ያሰላል!!!
ይህን መልእክተ እኔ ፃፍኩት እናንተም አንብባችሁ ሼር በማድረግ ሌሎች እንዲማሩበት እንድታደርጉ በጌታ ፍቅር እጠይቃለው። ቪዲዮውን መመልከት አይርሱ። እኔ ተባርኬበታለው እናንተንም ይጠቅም ዘንድ እነሆ ጋበዝኳችሁ። ለመጠቀምም ለመጥቀምም ሆናችሁ ትመለከቱት ደግሞም የእግዚአብሔር ቃል ሊነግረን በፈለገው መጠን መረዳት ይሆንላችሁም ዘንድ ፀሎቴ ነው።
No comments:
Post a Comment