Monday, 23 July 2018

ሌላ አንድ የለም


ዶሮ ታርዳ በብልት በብልት አስራ ሁለታ ቦታ ከመገነጣጠሏ በፊት አንድ ዶሮ ተብላ እንደምትጠራ ሁሉ የዚህ ፅሁፍ ርዕስም  አንድ ራሱን የቻለ መልእክት ያለው ሲሆን እንደ ዶሮ ብልት ስንገነጣጥለው ሶስት ራሳቸውን የቻሉ ወሳኝና ቆራጥ መልእክት አዘል ያነገቡ ርዕሶች ይወጡታል።  እነሱም
ሌላ     \
አንድ     }   አትኩሮት የሚሹ ወሳኝ ጉዳዮች
የለም   /

ሌላ

ሌላ የሚለው ቃል በአብዛኛው የሚያተኩረው አማራጭ ስለሆነ ጉዳይ ነው። '' ሌላ '' ያለበት ዐረፍተ ነገር የአንድን ድርጊት ውስንነት ወይም ገደብ የለሽነት በጉልህ የሚያሳይ ቁርጥ ያለ ውሳኔን ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል ሰይጣን ''ሌላ'' በሚለው ቃል መፅሐፍ ቅዱስ ሲገልፀው  እንዲህ ይላል

ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤
                                                            ዮሐ 10:፥10

በዚህ ቃል ውስጥ የሰይጣን ዓላም በግልጽ ተቀምጧል። ሰይጣን በእኛ ላይ ከዚህ ውጪ ምንም ዓይነት ተልዕኮ የለውም። ሊያጫውትህ፣ ሊያዝናናህ፣ ሊያዳብርህ፣ ወይም በሕይወትህ የምትፈልገውን ሊሰጥህ አይመጣም። እሱ ሌባ ነው ይሰርቃል፣ ያርዳል፣ ያጠፋል ሌላ ተግባርም ሆነ ምግባር የለውም። ስለ ሰይጣን ከዚህ ውጪ የተረዳ ሰው ካለ '' ሌላ '' የሚለው ወሳኝ ቃል አመለካከቱን ቆርጦ ይጥለዋል ምክንያቱም የጌታ ቃል እጅግ ግልፅ በሆነ መልኩ ተናግሯልና።

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ '' ሌላ '' በሚለው ቃል ጋር አያይዞ ከብዙ በጥቂቱ በእንዲህ ይገልፀዋል።

መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።
                                                                 ሐዋ 4፥12
እዚህ ጋር መፅሐፍ ቅዱሳችን በአፅንዎት እንደገለፀው የመዳን ብቸኛ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ ሌላን ሁለት ጊዜ ተጠቅሞበታል፣ አንድም ከኢየሱስ ውጪ የመዳን ጉዳይ ታሳቢ እንዳላይደለና በማንም ሊሆን እንደማይችል፣ አንድም ሌላ ከእርሱ ውጪ እኛ ልንጠቀምበት የሚገባ ስም እንደሌለ። በአጭሩ ከእርሱ ውጪ አዳኝ እንደሌለ '' ሌላ '' የሚለው ቃል ይገልፅልናል። ኢየሱስ ክርስቶስ አማራጭ የሌለው ብቸኛ ምርጫ ነው። አዎ ኢየሱስ ብቸኛ አዳኝ፣ ኢየሱስ ብቸኛ ቤዛ ነው።

ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
                                                              1ኛ ቆሮ 3:፥11
ማብራራት በማይጠይቅ ሁኔታ እዚህ ጋርም መፅሐፍ ቅዱሳችን '' ሌላ '' በሚል ቃል አዘል ኢየሱስን ምርጫ የለሽ ብቸኛ ጉዳያችን እንደሆነ ዳግም በአትኩሮት ገልፆታል።

ታዲያ ከእኛ ምን ይጠበቃል? መፅሐፉ ስለእኛም '' ሌላን '' ተጠቅሞ እንዲህ ይለናል

እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤
                                                                   ዮሐ 10፥1
ኢየሱስ ራሱን ብቸኛ ከሰማይ የመጣ እውነተኛ መንገድ መሆኑን በተለያየ ምሳሌዎች ነግሮናል። ለዚህም እርሱን ብቻ መንገድ አርገን ሕይወታችንን ማቅናት አለብን። በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ብሎናል። ከእርሱ ውጪ መንገድ አደላድለን ከሆነ መንገዳችንን ማቅናት ይኖርብናል። ወንበዴነታችንን ወደነው ካልሆነ በቀር ብቸኛ መንገዳችን የቃሉ ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

'' ሌላ '' የሚለው ቃል ከኢየሱስ ውጪ እንዳናይ፣ እንዳናስብ፣ እንዳንመለከት፣ እንዳንሻም ያሳስባል።

አንድ
በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቁጥርን ወይም ብዛት ለማመልከት ከተጠቀሰበት ዓላማ ውጪ መንገድን፣ ሁኔታን፣ ትዕዛዝን፣ ፍቃድን ወይም የእግዚአብሔር ሀሳብ በግልፅ ከማስቀመጥ አንፃር '' አንድ '' ተብሎ በተነገረባቸው ቦታዎች ሁሉ እግዚአብሔር በቃሉ ምን ያህል ሊያሳስበን እንደፈለገ በቀላሉ መረዳት እንችላለን። አንድ የሚለው ቃል የሚያሳየው ከምርጫ ውጪ የሆነን ነገር በብቸኛነት የሚያጠቁም ወይም የሚያሳይ ወሳኝ ቃል ነው።

ይህ ''አንድ'' የሚለው ቃል በሕይወታችን ውስጥ ትርጉም የሚሰጥና ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር የሚያግባባን መሰረታዊ ቃል ነው። መፅሐፍ እንደሚል በአንዱ መተላለፍ ኋጢአት በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ነገሰ ሞትንም አስከተለ ነገር ግን በአንዱ በኢየሱስ መታዘዝ ሕይወት ሆነልን (ሮሜ 5፥12-17)።

ሰው ከኋጢአትና ከዘላለም ሞት እንዲድን እግዚአብሔር ያዘጋጀው የመዳን መንገድ አንድ ልጁ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው እንደ ዮሐንስ ወንጌል 14፥6 መሰረት። በሌላ በኩል

ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤
                                                       1ኛ ጢሞ 1፥15

ከዚህ የምንረዳው ማንም ከኢየሱስ በቀር የእኛን ኋጢአት ሊያስቀር ወደዚህ ዓለም የመጣ እንደሌለ ነው። የዓለምን ኋጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ተገለጠ የተባለለት እርሱ ብቻ ነው። ለዚህም በተደጋጋሚ ክርስቶስን በብቸኛነት '' አንድ '' በማለት ይገልፀዋል። ለምሳሌ ያህል:-

=}} አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ (2ኛቆሮ 5፥14)
=}} ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሰጠ (ማር 10፥45/1ኛ ጢሞ 2፥6)

መፅሐፍ ቅዱሳችን '' አንድ '' ሲል ሌላ እንደሌለ ልንረዳ ይገባል። እኛን በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል

ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥
                                                             ሮሜ 3:፥11

 ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤
                                                              ሮሜ 3፥23

ሁሉ የሚለው ቃል ውስጥ አንድ እንኳ መምዘዝ አንችልም መፅሐፉ በድግግሞሽ በማሳሰብ ዘግቶታል። ሁሉም የሰው ዘር በሙሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ክቡር ደም መቤዥት አስፈልጎታል። ከእግዚአብሔር ክብር ጎድለን የነበርነውን እርሱ መልሶልናል። ከኋጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን የመሰለው ጌታችን ኢየሱስ በመካል የነበረውን የጥል ግድግዳ ያፈረሰ እርሱ ብቻ ነው። ይህንንም መፅሐፍ ሲናገር

አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤
                                                           1ኛ ጢሞ 2፥5
ቃሉ በአፅንሆት እንደገለፀው በመካከል ያለው አንድ ብቻ ነው እዚህ መካከለኛ ላይ መጨመርም ሆነ ከተጠቀሰው መካከለኛ ሌላ መፈለግ አይቻልም። ሰው ያሻውን ይጨምር ይሆናል በእግዚብሔር ዘንድ ግን ተቀባይነት የለውም።

አንድ ጌታ ኢየሱስ አለኝ ክርስቶስ አለኝ
ነፍሴን ነፍሱ ያደረገልኝ የሚዋጋልኝ
ማይፈታ ምይተሜ ነው ደሙ
ከፍ ላርገው አርማዬ ነው ስሙ

የለም
ይህ ቃል በአጭሩ የሚያስረዳው ከላይ ካየናቸው ሁለት ወሳኝ ጉዳዮች ውጪ ሌላ እንደሌለ ነው። አዎ ሌላ አንድ የለም። መፅሐፉ ካስቀመጠልን መዳኛ ውጪ ሌላ አንድስ እንኳ የለም። ትርፉ ጉንጭ ማልፋት እንጂ ።

መዳን ከኢየሱስ ውጪ በሌላ በአንድስ እንኳ የለም (ሐዋ 4፥12)። እርሱ ብቸኛ መዳኛ ነው። ከእርሱ ሌላ አምባ የለም ማንም የለም ማንንም አላውቅም ይላል እግዚአብሔር እኛስ?

እኔ በበኩላ
የለም ሌላ ስም ሌላ መዳኝ
ከሰማይ በታች መተማመኛ

ከቤዛዬ፣ በድካሜ ከሚራራልኝ ሊቀካህኔ፣ ደሙ ዘላለም ከሚያነፃ ከኢየሱስ ውጪ ሌላ አንድ የለም ብያለው። እናንተስ?

No comments:

Post a Comment