ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌ 2፥4-5
Monday, 23 July 2018
ያ ሰው
ያ ሰው እኔ ነኝ የበደልኩትኝ
ያ ሰው ኢየሱስ ነው እኔን ያዳነኝ
እኔ:-
ንጉስ ዳዊት ኣሪዮንን ካስገደለ በኋላ እግዚአብሔር በናታን በኩል ተናገረው ላደረገውም ኋጢአትን የመሸፈን ስራ ለራስህ ብዙ ሰጥቼ ሳለ አንተ ግን አልበቃህ ብሎ የሰውን ወሰድክ። ላደረከውም ክፉ ስራ ሌላ የበደል ካባ ደረብክ፣ የሰጠውህ አንሶም ከሆነ እጨምርልህ ነበር ነገር ግን አልጠየከኝም ብሎ ዳዊትን ወቀሰው። ሁለተኛ ሳሙኤል ምዕራፍ አስራ ሁለት ከቁጥር 1-7 እንዲህ ይላል:-
እግዚአብሔርም ናታንን ወደ ዳዊት ላከ ወደ እርሱም መጥቶ አለው። በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ አንዱም ድሀ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ባለጠጋውም እጅግ ብዙ በግና ላም ነበረው። ለድሀው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፤ አሳደጋትም ከልጆቹም ጋር በእርሱ ዘንድ አደገች፤ እንጀራውንም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበር፥ እንደ ልጁም ነበረች። ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፤ የዚያንም የድሀውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን። ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው። ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት ይመልስ አለው። ናታንም ዳዊትን አለው። #ያ_ሰው_አንተ_ነህ።
አዎ ያ ሰው አንተ ነህ አለው። በራሱ ላይ የፈረደ በሰው ሲሆን በደሉ የገባው ራሱን በጉዳዩ ውስጥ ሳይመለከት በሰው ውስጥ ሲሆን የነገሩን ታላቅነት ተረዳ ፈረደም። እግዚአብሔር በምሳሌ ንጉስ ዳዊትን ገሰፀው። እኔም በዚህ የታሪክ ክፍል ብዙ ተማርኩ ጉዳዩን ወደ ራሴ አመጣሁት። እኔስ ብሆን ብዬ ራሴን በዚህ ታሪክ ውስጥ አገኘው።
ያ ሰው እኔ ነኝ። ሁሉ ተሰጥቶኝ፣ የጎደለብኝ ሳይኖር በክቡር የክርስቶስ ደም ተገዝቼ፣ ውድ ዋጋ ወጥቶብኝ ሳለ ነገር ግን እኔ በበደሌና በኋጢአቴ ሙታን ነበርኩኝ፣ የሥጋዬንና የልቡናዬን ፈቃድ እያደረኩ በሥጋ ምኞት በፊት እኖር ነበር፣ ከፍጥረቴ ጀምሮ የቁጣ ልጅም ነበርኩ። በአለመታዘዝ ጠንቅ የጠፋው፣ በዓለም ተወስጄ ከእግዚአብሔርም ክብር ጎድዬ ከመንፈሱ እርቄ የምኖር ተቅበዥባዥ ነበርኩ። መንፈሳዊ ካባ ደርቤ፣ ለሚያየኝ አማኝ መስዬ፣ የራሴን የመዳን መንገድ ፈፅሜ ቤዛዬ ላይ ደርቤ፣ ከበደልና ከኩነኔ የሚያነፃውን ክቡር ደሙን አክፋፍቼ የነበረ፣ አዎ ያ ሰው እኔ ነኝ። ነገር ግን.........
ኢየሱስ:-
በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ። ልትድን ትወዳለህን? አለው። ድውዩም። ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ። ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ።
ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው። ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት።
እርሱ ግን። #ያዳነኝ_ያ_ሰው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው።
ዮሐ 5፥2-11
አዎ ጌታ ኢየሱስ በድካሜ የሚራራ መልካሙ እረኛዬ፣ የዓለምን ኋጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፣ ክብሩን እንደመነጠቅ ሳይቆጥር ከዙፋኑ ወርዶ እንደ እኔ ሰው ሆኖ፣ ከባዱን ሸክሜን ሊሸከም፣ ስለ ኋጢአቴ ልከፍለው የሚገባውን የመስቀል ሞት ስለእኔ ሊሞት፣ የእኔን መራራ ፅዋ ሊጠጣ ራሱን አሳልፎ የሰጠው የእኔ አዳኝ፣ የዓለም ቤዛ ያዳነኝ ያ ሰው ኢየሱስ ነው።
ሰው የለኝም ብሎ የነበረው ድውዩም እውነተኛውን ኋጢአት የሌለበት፣ ነውር የማያውቀው፣ ስለ እኛ የመጣውን ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ አገኘው ዳነም። ዛሬም እኔ ከዘመናት በፊት በከፈለልኝ ውድ ዋጋ ድኛለው። በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ቤዛነት በኩል በፀጋው ሕያው ሆኛለው። እረ እኔስ ሰው አለኝ። የዘላለም ሊቀካህኔ ኢየሱስ፣ በእኔና በእግዚአብሔር መካከል ያለ መካከለኛዬ፣ እረ እኔስ ሰው አለኝ።
ማሳሰቢያ:-
ይህን ፅሁፍ ላነበባችሁ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑን ሳትዘነጉ መሆን ይኖርበታል።
የጌታ ፀጋና ሰላም ለሁላችን ይብዛልን አሜን።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment