ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌ 2፥4-5
Monday, 23 July 2018
ቅዱሱ መስዋዕት
እስራኤልን ከአራት መቶ ሰላሳ ዓመት በኋላ እግዚአብሔር ከግብፅ ባርነት እንዲያወጣቸው ያቀረበው መስዋት አንድ ነው (ዘፀ 12፥40 ጀምሮ)። ከነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ሌላ አርባ ዓመት የበረሀ ጉዞ ከፊታቸው አለ። ለዛውም እጅግ አስቸጋሪ መንገድ። በረሀው የሚወክለው ይህን ዲያቢሎስ የሚገዛውን ዓለም ሲሆን የቀረበው መስዋት ደግሞ ጥላነቱ ጌታ ኢየሱስን ነው።
ሙሴና አሮን እንደታዘዙት መስዋቱን ካቀረቡ በኋላ በዚያው ቀን እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ከነሰራዊቶቻቸው ከግብፅ ምድር አወጣ። ከግብፅ ባርነት ቀንበር ነፃ አወጣ። ከፈታኝ የአርባ ዓመታት ጉዞ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር ገቡ።
የሰው ልጅ ከነበረበት የኋጢአት ግዞት ወይም ከሞት ባርነት ግን ነፃ የሚያወጣው አንድ እውነተኛ ቅዱስ መስዋት ያስፈልገዋል። ከአዳምና ሔዋን መተላለፍ ጀምሮ የሰው ልጅ በዚህ እስራት ውስጥ ነበረ። ነገር ግን እስራኤልን ከግብፅ ባርነት እንዳወጣው የሰው ልጅንም ከዚህ የሚያወጣ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የተወደደ የመአዛ ሽታ ቅዱስ መስዋት መታረድ አለበት። ይህም መስዋት የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ከኋጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን የመሰለው የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው።
ኢየሱስ ለዓለም የተሰዋ ሕዝቡንም ከሞት ባርነት ነጻ ያወጣ የነበረብንን ኩንኔ ያስቀረ። በደሙ ማስተሰርያ ይሰማን የነበረውን በደለኝነት ከላያችን ያነሳ ቅዱስ መስዋት ነው። እግዚአብሔር እስራኤልን መና ከሰማይ እያወረደ ሲራቡ እያበላ፣ ሲጠሙ ከዓለት ላይ ውሃ እያፈለቀ ጥማቸውን ቆረጠ። እኛ ግን ዛሬ በነገሮች ሁሉ በድካማችን የሚራራልን ሊቀካህናታችን፣ ተበልቶ ዳግም የሚያስርበውን ሳይሆን፣ የበረከት መና ሳይሆን የሕይወት እንጀራችን፣ ከአለቱ ፈልቆ እስራኤላዊያን ዳግም እንደተጠሙት ሳይሆን የሕይወት ውሃ የናዝሬቱ ጌታ ለእኛ ሰጠን።
እስራኤልም (የብሉይ ኪዳን ሕዝብ) እኛም (የአዲሱ ኪዳን ሕዝብ) የተሰጠን ከሰማይ ነው ልዩነቱ እነሱ የተሰጣቸው ከሰጪው የታዘዘላቸውን በረከት ሲሆን እኛ ግን ሰጪውን ነው፣ ምንጩን ነው ስሙ ይቀደስ። የበረከቱ እንጀራ ጊዜአዊ ነው የእኛ ግን ዘላለማዊ ነው።
የእስራኤል ህዝብ ተስፋይቱን ምድር ወርሰውም ለኋጢአት በየጊዜው ለእግዚአብሔር መስዋታቸውን ይሰዋሉ እኛ ግን በአንዱ መድሃኒት የዛሬ 2010 ዓመት የፈሰሰው ደም አሁንም ትኩስ ነው። አንዴ ለዘላለም ባፈሰሰው ደም ዘላለም ይቅር እያስባለ የሚኖር ቅዱስ መስዋት ነው። መፅሐፍም እንደሚል የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኋጢአት ሁሉ ያነጻል (1ኛ ዮሐ 1፥7)። ከዚህ ላይ ሌላ ለኋጢአት የሚቀርብ መስዋት የለም። ይህ ደም ለዘላለም በቂ ነው። እግዚአብሔር በኋጢአት ምክንያት እኛን ይቀጣ የነበረውን ፍርድ ሁሉ ጌታ መስቀል ከፍሎታል። ምንም ዓይነት ጌታ ለኋጢአት ያልከፈለው ዋጋ የለም።
ከምንም በላይ እጅግ ደስ ሊለን የሚገባው እግዚአብሔርን ያመኑ እስራኤላዊያን ተስፋ ያደረጉትን ምድር ከነአንን አገኙ እኛ ግን " በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤(የዮሐንስ ወንጌል 3: 36) ነው የተባለነው። እዳችንን ከፍሎ ወሰደን። ኢየሱስ ለኋጢአታችን ሞቶ ለጽድቃችን ከሙታን መካከል ተነሳ እኛንም በእርሱ የምናምን ሕያዋን አደረገን። አሁን በማያልፍ የሕይወት ኋይል በግርማው ቀኝ ባለበት በዚያ ስፍራችን ሆነ። በዚህም እጅግ ደስ ይበለን።
ዛሬም የኢየሱስ ደም ከኋጢአት ያነጻል።
ዛሬም የናዝሬቱ ጌታ ያድናል።
ዛሬም ሊቀካህናታችን በድካማችን ይራራል።
ዛሬም ኢየሱስ አልተወንም።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment