Monday, 23 July 2018

አጽናኑ



'' አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል አምላካችሁ። ''
                                                 ኢሳ 4፥1

በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደምናነበው እስራኤል በባቢሎን ለሰባ ዓመታት በምርኮ ስትወድቅ ከፍተኛ መንፈሳዊ ክስረት ደርሶባታል። በዚህም ምክንያት በንጉስ ሰለሞን በከበሩ ድንጋዮች የተሰራው ቤተመቅደስ በባቢሎናዊያን በመቃጠሉ መቅደስ አልባ  ለመሆን ችለዋል። የእግዚአብሔር ታቦትም ተማረከ፣ ብዙ መጻህፍትም በእሳቱ ተቃጠሉ። ሌሎችም ክስረቶች ደርሶባቸው ነበር እናም የደረሰባቸውን መከራና የነፃነት እጦት ምክንያት ተስፋ ወደ መቁረጥ በመድረስ

'' መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ''
 (ትንቢተ ኢሳይያስ 40: 27)  በማለት አጉረመረሙ።

ነገር ግን እግዚአብሔር ሰሚ ነው ታምፆበትም ይሰማል። እርሱ ታማኝ እረኛ ነው ሕዝቡን አልተወም አጽናኝ ነብያትን በመላክ ሕዝቡን ያጽናና ነበር። ከላይ ከጠቀስነው ከኢሳያስ ምዕራፍ አርባ በኋላ የነበሩት ትንቢቶች ስለ ነፃ አውጪው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መሲህነት ነው። እስራኤልም መሲሁን በተስፋ ይጠብቁት ነበር። ነገር ግን መፅሐፍ እንደሚል

'' የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። '' (የዮሐንስ ወንጌል 1: 11)

ዛሬ በዘመናችን የሰው ልጅ በልዩ ልዩ ምርኮ ውስጥ ወድቋል መሲሁ ክርስቶስ ኢየሱስ ለኋጢአት ሞቶ ደግሞም እኛኑን ስለማፅደቅ በመነሳት የምስራች እየተነገረ ባለበት በዚህ ዘመንም የሰው ልጅ በሌሎች ነገሮች ተማርኳል። ዘመኑ በቴክኖሎጂ የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰበት በመሆኑ ሰዎች በቀላሉ መረጃ የሚያገኙበት ዘመን ላይ እንገኛለን።

ከዚህም የተነሳ ራሱንና አጠገቡ ያለውን በመዘንጋት የሩቁን የመረጃ ዜናዎች በመስማትና በማንበብ ተጠምዶአል። አብዛኞቹ የመረጃ መገናኛ አውታሮች ትኩረት የሚስብ ትኩስ ዜና ካጡ ስራ የሰሩ አይመስላቸውም። መልካሙን እየተዉ የጭንቀት ወሬ ለማግኘት የሚያነፈንፉ ብዙዎች ናቸው። አንድ አደጋ ወይም ጦርነት ወይም አንዳች እልቂት ያለበት መረጃ ካገኙ ሁሉም ያንኑ ክፉ ወሬ እንደ በግ ሲያመነዥጉት ይሰነብታሉ። የሚያጽናናም ሆነ የሚያንጽ ወሬ የሚነገርበት ወይም የሚነበብበት የመረጃ አውታሮች እጅግ ጥቂት ናቸው።

አሁን ሁላችንም ማለት በሚቻል ሁኔት በሞባይል ስልካችን ኢንተርኔትን በመጠቀም ለመረጃ ቅርብ ነን። በተለይ በFacebook። ወደዚህ መንደር የገባን እንደሆን ብዙ አሉባልታ ያለበት ዜና እንደአሸን የፈላ ነው። ድሮ ሐሜት አለ ተብሎ የምንሰማው ቡና ሲጠጣ ነበር አሁን ግን በፈረደበት በFacebook ሆኗል። በግለሰቦች ደረጃ የነበረው ሐሜትና ውሸት አድጎ ብሔራዊ ብሎም ኢንተርናሽናል አድርገነዋል።  በጣም የሚገርመው በፊት ብና እየተጠጣ ያለ ክፍያ የሚወራው ወሬ ዛሬ ላይ ኢንተርኔት ለመጠቀም ገንዘብ አውጥተን ካርድ በመግዛት በጀተኛ ሐሜተኞች ሆነናል።

ስለ ሰዎች ክፋትና በደል ብዙ የሚፃፍበት ነገር ግን ስለ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ጥቂት መፃፍ የሚያሰተችበት ዘመን ላይ ነን። ስለ ሰዎች ማንነት ለሰዓታት እናወራለን ነገር ግን መፅሐፍ ቅዱስ ይዘን አንድ ምዕራፍ ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ መነጋገር አቅቶናል።

የአንድን የእግር ኳስ ብድን ተጫዋቾች በሙሉ ከነመለያ ቁጥራቸው ሸምድደን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የተነገሩበትን የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ግን አንብበን የማናውቅ እንኖራለን።

እግዚአብሔር ፈቅዶለት ጸጋውም አስችሎት ጥቂት የሚፅፈውን ወይም የሚመሰክር ሲመጣ የሀሰት ስም በመለጠፍ የተፃፈው አጀንዳ ተረስቶ ወደ ሰውዬው ማንነት Divert ያደርጋል። የጉብዝናዬ ወራት ሳያልፍ ፈጣሪዬን ላስብ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ቃል ያዘነበለን ሰው በመከፋፈልና በማሳት ወደ ፀብና ትችት እንዲያደላ የምናደርገው ለምንድነው?

በጣም የሚገርመኝ ነገር ቢኖር አንድ ጊዜ አንድ የራሴን ፎቶ በዚሁ የFacebook Wall ላይ ለጠፍኩኝ እናም የሚያውቁኝ ሁሉ የተለመደውን Like አልፎ አለፎም Comment አደረጉ በሚቀጥለው ቀን ግን አንድ የእግዚአብሔር ቃል ከነጥቅሱ ለጠፍኩኝ እነዛ Likeዎች ድራሻቸው ጠፋ ምክንያቱም ከእኔ ባሻገር ያለውን መልእክት መመልከት ስላልቻሉ። ከላይ የጠቀስኩት መከፋፈል ያመጣው መዘዝ መሆኑ ነው።

መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ አራት ቁጥር ስድስት ላይ በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙዎች ናቸው ይላል። ብዙዎች ለዚህ ለሚያልፈው ዓለም ሳይሆን ከጌታ ጋር ዘላለም የምንኖርበትን መንገድ ማወቅ ይሻሉ። እርስ በእርሳችን በፍቅር እንደ እግዚአብሔር ቃል ካልተገሳጸጽን፣ ተስፋ የቆረጠውን ካላጽናናን እንዴት የጌታ ፍቅር ገባን ልንል እንችላለን?

በዚህ ቃል ተጽናኑ (1ኛ ተሰ 4፥18)

እግዚአብሔር በልጁ በክርሰቶሰ ኢየሱስ ያመንን ሁላችን እርስ በራሳችን እንድንጽናና ይፈልጋል። እንድንደጋገፍ አንዱ ለሌላው አበርታች እንድንሆን ይሻል። ታዲይ ምንድነው የምንጠብቀው? ጥፋት ያለበት አንድ ሰው ቢገኝ ቃሉ እንደሚያዘው በየዋሃት መንገድ ማቅናት አንድም እሱን ለመጥቀም አንድም እኛም እንዳንሰናከል ለምን እንደ ቃሉ አንሆንም?

አጽናኙ ለዘላለም ከእኛ ጋር ነው።
(ዮሐ 14፥15-16፣ ዮሐ 14፥26፣ ዮሐ 15፥26)

የሚያጽናናን የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ተልኮልን ለእርሱ እንዳንገዛ አዚም ያደረገብን ማን ነው? መሲሁ ክርስቶስ ስለእኛ መስዋህት ሆኖልን የእኛ መዘናጋት ጤነኝነት አይደለም። ለእስራኤል የተላኩት የምርኮ ዘመን ነብያትን ነው ለእኛ ግን ታላቅ አጽናኝ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። እጅግ እድለኞች ነን። መጽናናት ይሁንልን።

ይህንን ፅሁፍ ላነበባችሁ በሙሉ አንዳችን ለአንዳችን መኖር ይገባልና በሰው ልብ ውስጥ ጥላሸት ከምንቀባ አንድ የእግዚአብሔር  ቃል ተናግረን ሰውን አጽናንተን በብሩኩ ተስፋችን በጌታ ኢየሱስ ላይ ባለ እምነት እንዲኖር የሁልጊዜ ኑሮአችን እናድርግ እላለው። የማንችል ነን ብላችሁ ለመሞከር በፍርሃት ያላችሁ አዎ ሁላችን አንችልም ነገር ግን የሚያስችል ፀጋ በሚያስፈልገን ጊዜ ይሰጠናልና። የእግዚአብሔር ቃል እንደሚል '' ሰው በኋይሉ አይበረታምና '' በራሳችን ሳይሆን በፀጋው ላይ በመውደቅ የሚገኝ አገልግሎት ይኖረን ዘንድ ሰዓቱ አሁን ነው። አረፈደም ዘመኑ ካመጣው መንፈሳዊ ክስረት እንውጣ።

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ የእግዚአብሐር አብ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ህብረት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።
ሼር

No comments:

Post a Comment