Monday, 23 July 2018

የሚበልጥ ፍቅር

'' እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።"  (1ኛ ቆሮ13፥13)

ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ለዘመናት ብዙ ተብሏል ግን ፍቅሩ ሳይበርድ ዛሬም ትኩስ እንደሆነና በሕይወታችንም ሲሰራ እያየነው እንገኛለን። እግዚአብሔር በባህሪው አፍቃሪ አምላክ ነው። ለመፈጠራችን፣ ደግሞት በኋጢአት ወድቀን ሳለ በበደላችን ሙታን በሆን ግዜ ከልጁ ጋር ሕይወት የሰጠን (ለደህንነታችን) መሰረት የእርሱ ፍቅር ነው።

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።
                                                    ዮሐ 3፥16

ከፍቅሩ ብዛት እንዲሁ የወደደን እግዚአብሔር ስሙ ብሩክ ይሁን። ከእኛ ምንም ሳይጠብቅ እንዲሁ የፈለገን አንድ ልጁን በመስጠት ፍቅሩን የገለፀ መልካም የፍቅር አባት ነው። ይህ ፍቅር ነው ታሪካችንን ቀይሮ ወደ ገዛ ፍቅሩ ልጅ መንግስት ያፈለሰን።

በየዘመናቱ ይህ ፍቅር ተሰብኳል፣ ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያ ላለው የሰው ዘር በሙሉ ምስራች ተነግሯል ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር የዘላለም ሀሳቡን እንደ ልቡ ምክር በፍቅር ልንኖር አቅቶናል። እኛ ቤተሰቦቻችንን፣ ወዳጆቻችንና ወገኖችንን የምናፈቅረው ከእግዚአብሔር አምሳል ስተለቀዳን ነው። ግን የእርሱ ፍቅር ፍፁም ሙሉ የእኛ ግን ጎዶሎ ነው። ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በደልና ኋጢአት በመስቀል ላይ ሲሰቀል እኛ ግን የገዛ ጥፋታችንን ማመን ተስኖናል። እርሱ ለሰቃዮቹ ይቅርታና ምህረት ሲለምን እኛ ግን ወዳጆቻችንን እንኳ በቅጡ መውደድ አቅቶናል።

ዓለምን ብንዞር ብንዞር ለበደለ ባሪያ አይደለም ለጨዋ ባሪያ ልጁን የሚሰጥ አናገኝም። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ 5፥6-11 በዝርዝር ያስረዳው።

የሰው ፍቅር እስከ መቃብር ነው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ '' ፍቅር እስከ መቃብር '' የሚለውን መፅሐፍ ያውቀዋል። አዎ የሰው ፍቅር የተገደበ ነው። የእርሱ ፍቅር ግን ወሰን የለውም። እርሱ ፍቅር ነውና። በልጁ የገለጠው ፍቅር የመውደድ ጥግ ነው። የፍቅር ዳርቻ እርሱ እግዚአብሔር ነው።

አቤልና ቃየንን መመልከት እንችላለን። ለሁለቱም መስዋህት የማቅረብ የተሰጠው ጥያቄ አንድ ነው። ነገር ጥያቄውን የመፈፀም ልዩነት ግን አለ። በዘፍጥረት ምዕራፍ አራት ከቁጥር አራት ጀምረን ብናነብ አቤል የቃየን መስዋህት ተቀባይነት እንዳያገኝ ምንም አላደረገም። እርሱ የራሱን ብቻ ነው ያቀረበው። የቃየንን አልተቸም ወይም የወንድሙን ልብ አላሸፈተም። ፍቅር በሚጠይቀው መልኩ አቀረበ እግዚአብሔርም መስዋቱን ተቀበለው።

በአንፃሩ ቃየንን ስናየው ፍቅር ከማጣቱ የተነሳ በወንድሙ ላይ እንዲነሳሳ አደረገው። መስዋቱን ያልተቀበለው እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ ነገር ግን እጁ የሌለበትን ወንድሙን ሲገድል እናነባለን። ከወንድሙ ሊማር ሲገባ የእሱ ድካም ምንጭ ወንድሙ አድርጎ ስለቆጠረ ተበቀለው። ነገር ግን አቤል ባይኖር እንኳ እግዚአብሔር የቃየንን መስዋህት አይቀበልም ነበር። የእግዚአብሔር በር ሁሌም ክፍት ነው። ቃየን ራሱን ለውጦ ዳግም መስዋህት ማቅረብ ይችል ነበር።

የሰዉ በር ቋሚ አይደለም ካሻን እንከፍታለን ካሻን ደግሞ ዘግተን በራሳችን አጥር እንኖራለን። የእግዚአብሔር ቋሚና ዘላቂ ነው የእኛ ግን በሁኔታዎች የተከበበ ነው። በሕይወታችን የብዙ ሰዎች በር ተዘግቶብናል የእርሱ ግን ላይዘጋ የተከፈተ ነው።  በወዳጆቻችን ውንጀላ ተሰላችተናል እርሱ ግን በውድ ደሙ ነጠብጣብ አፈቅራችኋለው የሚል አፍቃሪ ነው ስሙ ይቀደስ።

እግዚአብሔር በምን ያህል የፍቅር መጠን እንደወደደን ነግሮናል

እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል።
                                                        ዮሐ 17፥22-23

 እኛስ ምን ያህል እንወደዋለን? እርስ በራሳችን ምን ያህል እንዋደዳለን?

እኛ ፍቅራችንን ስንገልጥ ምናልባት የዓባይ ወንዝን ርዝመት የሚያህል ወይም የኪሊማንጃሮ ተራራን ከፍታ የሚያህል ልንል እንችላለን እርሱ ግን አንድያ ልጁን የናዝሬቱ ኢየሱስን በወደደበት መጠን ወዶናል። ታዲያ አፍቃሪ ፍቅር ይፈልጋል። የሰጠንን ስንኖረው ማየት ይሻል በወንድማማች መዋደድ  ተመላለሱም ተብሎ እንደተፃፈ አንደ ቃሉ እንድንኖር የጌታ ፀጋ ይርዳን።

ፍቅር የሆነው እርሱ ኢየሱስ በፍቅር ዋጋ ገዝቶናል። አንድ መቶ ብር  የሚያወጣ እቃ ስትገዙ መቼም አንድ ሺህ ብር ቀብድ አትከፍሉበትም። እርሱ ግን ኋጢአት የሚጠይቀውን ሁሉ ቅጣተ ለነበረው ለአሁኑም ወደ ፊትም ለሚደረጉ አመፃዎች ኢየሱስ በፍቅር ከፍሏል። እንደተከፈለልን ዋጋ መኖር ይሁንልን።

ምክር
1) ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ።
                                                    ገላ 5፥13
2) በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ
                                                     ኤፌ 4:፥2
3) ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ
                                                     ኤፌ4፥15

4) ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ።
                                                     ኤፌ 5፥2

5) ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።
                                                     1ኛ ዮሐ4፥18

6) በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን።
                                                   1ኛ ቆሮ 16፥14

7) በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።
                                                 1ኛ ጴጥ 5፥14

No comments:

Post a Comment