በመልካም ሁኔታ ውስጥ ሆነን እግዚአብሔርን ማመስገን ተለማምደን ይሆናል ችግር ወይም መከራ ውስጥ ገብተን ግን ብዙ ጊዜ ማመስገን ይከብደናል። ችግር ወይም መከራ የእግዚአብሔርን መልካምነት አያጎድልም። እርሱ ሁልጊዜ ከመልካምነት አይጎድልም ስሙ ብሩክ ይሁን።
እግዚአብሔር በእምነት እንድናድግ በፈተና ውስጥ ያሳልፈናል። እምነት ደግሞ ካልተፈተነ ብርታቱ ወይም ጥንካሬው አይታወቅም። ወርቅ በእሳት ካልተፈተነ እንዲል መፅሐፍ ቅዱሳችን የሰው ልጅም እንዲሁ ነው። እርሱ በትንሹ ሲፈትነን ለትልቁ እያዘጋጀን እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። በፈተና ውስጥ በእምነት እንድናድግ እንጂ እንድንወድቅ ከቶ አይፈልግም። ይልቁንስ በእርሱ አብልጠን እንድንደገፍ ወይም እንድናምን በፈተና ውስጥ ያስተምረናል።
ታዲያ እግዚአብሔር እኛን እየፈተነ ባለበት ሁኔት ውስጥ ሆነን መልካሙነቱ መናገር የምንችልበት እምነት አለን ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ብልህነት ነው። ይህን ካደረግን በእውነት እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ዓላማ እውን ሆኗል ማለት ነው።
ኢዮብ የነበረውን አጥቶ፣ ጤናው ተቃውሶ ሰውነቱ በቁስል ሲወረር ሚስቱ እግዚአብሔርን እርገምና ሙት ባለችው ጊዜ የመለሰው መልስ ለእግዚአብሔር የሚገባው ምስጋና ነበር።
ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።
ኢዮ 2፥10
አዎ ብዙ መልካም ነገሮች ተቀብለን በአንድ ትንሽ ጊዜአዊ ችግር ምክንያት እግዚአብሔርን ከማማረር የሚጠብቅ የእርሱ ጸጋ ሁላችንንም ይርዳ። በተሰጠን በረከት ላይ ሳይሆን በበረከቱ አምላክ ላይ ልበ ሙሉ እምነት ይኑረን። ኢዮብ የነበረውን ሳይሆን ሰጪውን አሻግሮ ተመልክቷል። እምነቱም በእርሱ ላይ ብቻ ነበረ። በነዛ ሁሉ ችግሮች ውስጥ ሆኖ እንኳ እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን ነው ያለው። በችግር ውስጥ ሆኖ ባረከ። ኢዮብ በችግሩ ኋይለኛነት ሳይሆን እምነቱን ባሳረፈበት አምላክ ኋይል ተማርኳል። አንድ ደስ የሚለኝ አባባል አለ:-
'' ለእግዚአብሔር የችግርህን ታላቅነት አትንገር
ለችግርህ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ንገረው ''
እግዚአብሔር ሲሰጥም ሲነፍግም ትክክል ነው መልካምም ነው። የማይጠቅመንን ነገር በመከልከል ይጠብቀናል የሚያስፈልገንን ነገር ሳንነግረው የሚያውቅ እርሱ በራሱ የጊዜ ሰሌዳ ያከናውንልናል ይሰጠንማል። አዎ እግዚአብሔር መልካም ነው።
ችግርን ለጥቅማችን ያመጣዋል ከችግር መውጫንም እርሱ ያዘጋል እግዚአብሔር እጅግ መልካም ነው።
No comments:
Post a Comment