Monday, 23 July 2018

የሚታይ እምነት



በእግዚአብሔር ቅዱስ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት የውስጥን ከሚያውቀው ከእርሱ በቀር ማንም ሊይውቅ አይችልም። እርሱ ዓይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል የሚያበሩ ልብና ኩላሊትን የሚመረምሩ፣ ስለ ሰዎች ሊነገረው የማይገባ ሁሉን የሚያውቅ ከልባችን ይልቅ ታላቅ የሆነ እርሱ ብቻ ነው። ሰው ስራን ወይም ውጫዊ የሆነውን ድርጊት ብቻ ያያል እርሱ ግን የልባችንን ያውቃል። ቃላት ሳንተነፍስ መልስ የሚሰጥ ቸር እረኛ ነው።

እምነት በስራ ይገለጣል ነገር ግን በስራ መገለጡ የሚጠቅመው መልሶ ራሳችንን ወይም በዘንዳችን ያሉትን ሰዎች ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ስለ እኛ ለማወቅ ብሎ የሚፈትነን ነገር የለም። እርሱ አስቀድሞ አውቆናልና። ይልቅስ እምነታችን እንዲታይ የሚፈለግበት ምክንያት ከላይ የጠቀስኩት የራሳችንን እምነት ጥንካሬ እንድንፈትሽ ወይም የእምነታችንን አነሳሳሽ ምክንያት በእኛ እንዲገለጥ እና ለሌሎች ምሳሌ እንድንሆን ነው።

አብርሃም ልጁን ይስሀቅን እንዲሰዋ እግዚአብሔር ሲያዘው እግዚአብሔር አብርሃም በእምነት እንደሚታዘዝ ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም። ኢዮብን ሰይጣን እንዲፈትነው እግዚአብሔር የፈቀደው የኢዮብን መታመን ሳያውቅ ቀርቶም አይደለም። ነገር ግን እነዚህ ሁለቱ የእምነት ሰዎች በእግዚአብሐር ላይ ምን ያህል እንደተደገፉ ራሳቸው አያውቁም ነበረ። ሰይጣን ኢዮብን ስለባረከው ነው እግዚአብሔርን የተከተለው በማለት ከሰሰና ተፈቀደለት። ተፈተነም ብዙ ነገሩን አጣ ነገር ግን ኢዮብ በበረከቶቹ ላይ ሳይሆን በበረከቶቹ አምላክ እምነት እንዳለው እርሱም አወቀ እኛም ይኧው እየተማርንበት እንገኛለን። የሚታይ እምነት አሳየ።

በማርቆሰ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ከቁጥር አንድ እስከ አምስት ድረስ ያለውን ብንመለከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እምነትን በማየት ኋጢአት ሲያስተሰርይ እናነባለን። 

ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ደግሞ ገብቶ በቤት እንደ ሆነ ተሰማ። በደጅ ያለው ስፍራም እስኪጠባቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ይነግራቸው ነበር። አራት ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት። ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፥ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። አንተ ልጅ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው።
                                                    (ማር 2፥1-5 )

የማርቆስ ወንጌል ክርስቶስን እንደ አገልጋይ አድርጎ የሚያሳይ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። በዚህ ምዕራፍ ውስጥም በአንድ ቤት ውስጥ እንዴት ባለ ትህትናና ዝቅታ ጌታ ኢየሱስ ያስተምር እንደነበር ያሳያል። እነዚህ አራት ሰዎች እርሱ ያገለግል ወደ ነበረበት ቤት ሲመጡ መግቢያ መንገድ ባለመኖሩ አልተመለሱም። እርሱን እንጂ እርሱ ከገባበት ቤት ጋር ጉዳያቸውን አላዛመዱም፣ ግድግዳ አልዳበሱም፣ የገባበትን መንገድ የረገጠውን መሬት አላሉም፣ ኋጢአተኛ የሚያስፈልገው መድሃኒት እርሱ ኢየሱስ  ጋር ብቻ ሲደርስ እንደሆነ አምነዋል። ማድረስ የነበረባቸው አካል ጋር አደረሱት ተፈወሰም። የሚከተሉትን ደቀ መዛሙርትን እንኳ ጥሩልኝ አላሉም ምክንያቱም ኋጢአት ሊነፃ የሚችለው በጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው ስሙ ይቀደስ።  የሚታይ እምነት ይሏል ይህ ነው።

ጌታ ኢየሱስ ጋር ለመድረስ ማድረግ ያለባቸውን አደረጉ በሩ ቢጨናነቅም ጣራ አንስተው ከላይ ወደ ታች ሽባውን አስገቡት እርሱም ስራቸውን ሳይሆን እምነታቸውን በማየት የሽባውን ልጁ ኋጢአት ይቅር አለ። አዎ እኛ የአራቱን ሰዎች  ስራ ላይ ትኩረት እናደርግ ይሆናል እርሱ ግን እምነትን ያያል። እኛ ልፋታቸውን አይተን ክንፈረ እንመጥ ይሆናል ነገር ግን እርሱ የመጡበትን ዓላማ ያውቃል።

እነዚህ አራት ሰዎች ተሸክመው በማምጣት ኋጢአተኛውን ከመድሃኒቱ ጋር አገናኙ። ዛሬ ላይ የክርስቶስ ኢየሱስ ነን እያሉ መንገድ የዘጉ ብዙዎች አሉ። በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ባላቸው እምነት ሳይሆን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወይም ስርአት ተመርኩዘው እነሱም ሳይደርሱ ሰውንም ተሸክመው ሳያደርሱ በር ዘግተው የተቀመጡ ብዙዎች አሉ። እኛስ የቱ ጋር ነን? ራሳችንን እንፈትሽ።

አብዛኛው ህዝብ እረፍት ፍለጋ ሲባዝን እያዩት የተስፋውን ቃል ከመንገር ይልቅ በሃይማኖታዊ ካባ ሽፋን በሁከት ድምፅ እያሸበሩ ከመድሃኒቱ ጋር እንዳይገናኝ ታክል የሆኑ ብዙዎች አሉ። እኛስ የቱ ጋር ነን?

እርሱ ሁሉ አዋቂ ነው። አሁን እንኳ ይህን እየፃፍኩ እናንተም እያነበባችሁ በምን ዓይነት ልብ እንዳለን ያውቃል። ተሽክሙ ጣራ አንሰተው ነድለውም በሽተኛን ወደ መድሃኒቱ የሚያመጡበት ባለበት ስፍራ እንኳ ተቃዋሚዎች ነበሩ። ኋጢአትህ ተሰረየችልህ ስላለው ስለምን እንዲህ ያለ ስድብ ይሳደባል ነበር ያሉት። ዛሬም በማያልፍ የሕይወት ኋይል በግርማው ቀኝ የተቀመጠውን ጌታ ጋር ሰዎች እንዲደርሱ ሰዎችን መሸከም አለብን። የሚታይ እምነት ይኑረን እርሱ አሁንም የልባችንን ያያል። አዎ

ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።
                                                       (ዕብ 13፥8)

በእርሱ ዘንድ የሚታይ እምነት ይጨምርልን። የጌታ ኢየሱስ ሰላምና ፍቅር ይብዛላችሁ። አሜን።

1 comment: