Monday, 23 July 2018

ቆራሌው



ከልጅነታችን ጀምሮ የቆራሌን ድምፅ በመስማት አድገናል። ገና ከሩቅ ሆኖ '' ቁራሌው አሮጌ ጫማ ያለው '' እያለ ሲጮህ ሰምተናል። አንዳንዴ ጠብቁት ተብለን አልያም ሲመጣ ጥሩን ተብለን የቆራሌውን ድምፅ ለመስማት ጆሮዎቻችንን አንግበን የጠበቅንበት ጊዜአትም አሉ።

ቆራሌው ሰዎች የተጠቀሙበትን አሮጌ እቃ በየሰፈሩና በየመንደሩ በመግባት እየሰበሰበ በርካሽ ዋጋ የሚገዛ እግረ ቀጭን ሰው ነው። ይጠቅመኛል ያለውን እቃ እየመረጠ የሚስማማውን ዋጋ በመጥራት ይደራደራል። ቆራሌው ከሚደራደርበት መንገድ አንዱ የሚገዛውን እቃ ማጣጣል ነው። የማይጠቅም አድርጎ ወይም በጣም የተጎዳ በማድረግ በሚፈልገው ዋጋ ለመግዛት የሚጠቀምበት ስትራቴጂ ነው።

ሻጭም ስለገዛ እቃው የነበረውን ግምት ወይም ዋጋ በማሳነስ በቀላሉ ለቆራሌው በአነስተኛ ዋጋ ይሸጣል። የሰው ልጅም አእምሮው ትንሽ ያረገውን ነገር ለመተው አይቸገርም።   የማይጠቀምበትን እቃዎች በሙሉ እንደ ቅራቅንቦ በመቁጠር አሳልፎ የባለቤትነት መብት ለቆራለው ይሰጠዋል።

የሰው ልጅ በክርስትና ሕይወቱ የሚፈትኑት ሶስት ነገሮች አሉ። እነዚህ በሕይወቱ ሁሉ ጠላቶቹ የነበሩና አሁንም ድረስ ያሉ የዘላለም ጠላቶቹ ናቸው።
1) ሀሰተኛ የሀሰት አባት ዲያቢሎስ
2) ይህ የምንኖርበት ዓለም
3) ተሸክመን የምንዞረው ስጋችን ወይም የሰጋ ሰሜት ናቸው።

እኛ ሰዎች ከፍተኛ ውጊያ የምናደርገው አእምሮአችን ውስጥ ነው። እነዚህ ከላይ ያየናቸው ደግሞ ሀሳባችንና እንቅስቃሴአችንን በመቆጣጠር ሰው ከተፈጠረበት ዓላማ ውጪ እንድንሆን ያደርጉናል። ከእውነት ይልቅ በምናየውና በአእምሮአችን የእውቀት ደረጃ መጠን ብቻ ነገሮችን እንድናይ ይገፋፉናል። ሶስቱም በጌታ ያለውን ሰላም እንዳንይዝ፣ እረፍት እንዳይሰማን፣ ንስሀ እንዳንገባ በመከላከል የሚያጠቁን የፅድቅ ጠላቶቻችን ናቸው።

እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ።
ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።
                                                   ሮሜ 8፥5-8

ይህ ያልተቤዠው ስጋችን ከቀድሞው ጠላት ዲያብሎስ ምክር በመቀበልና በክፉ ከተያዘው ከዚህ ከአሁኑ ዓለም በሚያየውና በሚሰማው እየተታለለ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እንቅፋት ይሆንብናል። ወደ እግዚአብሔር ፍፁም ሙላት እንዳንደርስ የሚጎትት የሞት ሀሳብ ወደ ልባችን ሹክ የሚል እንቅፋት ነው። የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማን በማድረግ ከእግዚአብሔር ይቅርታ እንዳንጠይቅ በደላችን በደልን ከሚያነፃ ከክርስቶስ ደም የላቀ እንዲመስለን የሚያደርግ የክፉት ሽኩሽክታ ነው።

ይህ የስጋ ስሜት የሚሰማው ድምፅ አለ የወቃሽ ድምፅ። እንደ ቆራሌው አሮጌውን ማንነት የሚያስታውስና ወደ ኋላ የሚጎትት ድምፅ። ልክ እንደ ቆራሌው የመግዣ ስትራቴጂ ያጣጥልሃል፣ ለራስህ ያለህን ዋጋ እንዳታስተውል የኋጢአትህን መአት ያዥጎደጉድልሃል፣ ራስህን በመውቀስ የኩነኔ ስሜት እንዲሰማህ ያደርግሃል፣ ስለአንተ የፈሰሰ ደም እንዳለ ያስረሳሃል፣ ኋጢአትህ የማይነፃ እስኪመስልህ ድረስ ዋጋ ቢስ ያደርግሃል፣ በሕይወትህ ተስፋ በማስቆረጥ የፅድቅ ወጋገንን ይሸፍንብሃል፣ የኢየሱስ ክብር ደም ከኋጢአት ሁሉ እንደሚያነፃ ከህሊናህ ውስጥ ይሰውራል።
'' አንተ እኮ እንዲ አድርገሃል እንዴት ንስሀ ትገባለህ ''
'' የአንተ በደልማ ይቅርታ አያሰጥም ''
'' አሁን አንተ ነህ ክርስቲያን የምትሆነው '' በማለት ይወቅሳል። ነገር ግን መፅሐፍ እንደሚል

ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?
                                                              ዕብ 9፥14
ከምን ያህል የሞተ ስራ ህሊንችንን የሚያነፃ የኢየሱስ ደም ብቃት እንዳለው ይናገራል። ከየትኛውም በደልና ኋጢአት የሚያነፃ ውድ ደም አለ። ለዚህም ነው የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኋጢአት ሁሉ ያነፃል ተብሎ የተፃፈው።

ስለዚህ ተወዳጆች ኢየሱስ የሞተው ስለኋጢአታችን ነው። እርሱ ህሊናን ከሞተ ስራ ያነፃል። መንፈሳዊ ቆራሌው የሚለውን አትስሙ። እርሱ ሊሰርቅ ሊያርድ እንጂ ስለሌላ አልመጣምና ''  ቆራሌው በደለኛ ስሜት ያለው '' ሲላችሁ በኢየሱስ ስም ተቃወሙት። ክፉውን ተቃወሙት እርሱም ከእናንተ ዘንድ ይሸሻል ተብሎ ተፅፏልና።

የቱንም ያህል በደል ቢኖርብን ሁሌ ለጥቅማችን የሚጠራን ድምፅ አለ። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ ይከተሉኝማል እንዳለ ጌታ ይህን ድምፅ ብቻ መስማት ይሁንልን። እናንተ ደካሞች ሸከማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለው የሚል ብርቱ ድምፅ አለ።

አሮጌ እቃ የሚገዛው እግረ ቀጭኑ ቆራሌው አሮጌዎቹን ሰብስቦ ጥቂትም ቢሆን ብር ከፍሎ ይሄዳል ይሄኛው መንፈሳዊ ቆራሌ ግን ያለመታከት የሚሰራ ኩነኔ ወይም የባሰ የበደለኝነት ስሜት ጨምሮ  የሚሄድ አፍዝ አደንግዝ የዘላለም ጠላታችን ነው። ራሳችንን በማርከስ አእምሮችንን አንስጥ፣ አንገዛለት አላለው። ይህን እንድናደርግ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ የሚረዳን የእግዚአብሔር ፀጋ ሁላችንንም ይርዳን አሜን።

የማንቂያ ደውል (wake up call)

የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።         
                                                           ሮሜ 6፥23
ኩነኔ የለበት በክርስቶስ ላለ
እዳው በአንዱ ጌታ ስለተከፈለ
በፅድቅ ልንኖር ለኋጢአት ሞተናል
ማህተሙን ይዘን ማንስ ይከሰናል
የበጉ ደም ነክቶን ማን ይቋቋመናል።

No comments:

Post a Comment