ለሰው ልጅ እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሚባሉት ጉዳዮች መካከል ልብስና መጠለያ ናቸው። እኛም እነዚህን ነገሮች ከገሀዱ ዓለም ራሳችንን የምንሸፍንበት ዋንኛ መጠቀሚዎቻችን ናቸው። ሰዎች ሁላችንም ስንባል ሳንሸፈን መኖር አንችልም። በህይወት ዘመናችን በሙሉ በሚያስብል ሁኔታ በሚሸፍነን ውስጥ ተከልለን የምንኖር ጥገኞች ነን።
የመጀመሪያዎቹ ፍጥረታት የሆኑትን አዳምና ሔዋንን ብንመለከት በኋጢአት ከወደቁ በኋላ ክፉንና ደጉን በመለየታቸው ራሳቸውን የሚሸፍን የኮባ ቅጠል እንደለበሱና ነገር ግን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሚያስፈልገውን የሚያውቅ ቸር ነውና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን በጥላነት የሚያሳየውን የበግ ቁርበት አድርጎላቸው በሚበልጠው እንዳለበሳቸውና እንደሸፈናቸው መፅሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
በብሉይ ኪዳን የሰውን በደል መርምሮ በማወቅ የሚታወቀው የዳዊት ልጅ ጠቢቡ ሰለሞን ነው። ስለ ሰለሞን ሁላችንም ከልጅነታችን ጀምሮ የምናውቀው በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተፃፈ አንድ ታሪክ አለ። (1ኛ ነገ 3፥16-28) ሰለሞን እንዴት አድርጎ ሁለቱን ሴቶች እንደመረመረና ሐሰተኛዋን ከእውነተኛይቱ እንደለየና እውነቱን እንዳጋለጠ ብሎም ጉዳዩንም እስራኤል ሁሉ እንደሰሙ ይታወቃል።
አብዛኞቻችን ማጋለጥ ብቻ እውነት የሚመሰለን እንኖር ይሆናል ነገር ግን መሸፈንም እውነት ነው። መፅሐፍ እንዲህ ይላል
የእግዚአብሔር ክብር ነገርን መሰወር ነው፤ የነገሥታት ክብር ግን ነገርን መመርመር ነው።
ምሳ 25፥2
እግዚአብሔር ሸፋኝ አምላክ ነው። የአደባባይ ነውራችንን በመሸፈን በጉዋዳ የሚገስፅ መልካም አባት። እግዚአብሔር የእኛ ነውር በአደባባይ እንዲጋለጥ አይወድም ለዚህም እኛ ከሰዎች ጋር እርስ በእርስ ባለን ግንኙነቶች ችግር እንኳ ቢፈጠር እንደ ማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 18፥15 መሰረት ወንድምህ ቢበድልህ በመጀመሪያ ብቻህን ውቀሰው ይላል። ይህ የሚያሳየው ምን ያህል እግዚአብሔር ነውራችንን ለመሸፈን እንደሚፈልግ ነው። በሌላ በኩል ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ (ገላ 6፥1) ይላል ታዲያ ምን ያህል ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ማሰብ አያዳግትም። መሸፈን ትኩረት የሚያስፈልገው ወሳኝ ጉዳይ ነው።
የሰው ልጅ ህልውና የሚቀጥለው በመሸፈን ውስጥ ነው። መዝሙረኛው ንጉስ ዳዊት ያልተሰራ አካሌን ዐይኖች አዩኝ ብሏል። ያልተሰራ ማንነታችንን እግዚአብሔር ሸፍኖን ነው የሚሰራን። አንድ ህንፃ ሲገነባ በለያዩ ምክንያቶች ዙሪያቸው ተሸፍነው ግንባታቸው ይከናወናል። ግንባታውን የሚቆጣጠረው መሃንዲስ ወይም ኢንጅነር የሚሰራውን ህንፃ መጨረሻ እያወቀው ነው መሰረት ጥሎ እስከ መጨረሻው ግንባታውን የሚያከናውነው። በውጭ የሚያየው ግን ህንፃው አልቆ ካላየው መጨረሻው አያውቀውም። አቤት እግዚአብሔር እጅግ መልካም አባት እኮ ነው። ጋርዶን ይሰራናል ስሙ ይባረክ።
እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ምድሪቱን በከበበው በልጁ ክቡር ደም እንድንሸፈን ይፈልጋል። አዎ እርሱ ዓለምን በፍቅር ካጥለቀለቀው የክርስቶስ ደም ተሸፍነን እኛን ቀጥታ ሳይሆን በጌታ ኢየሱስ በኩል እንድንታይ ይሻል። ብቸኛው አርነት መውጫ ልጁ ነውና። ታዲይ በዚህ በገሀዱ ዓለም እንዴት እንሸፈን ብትሉ መፅሐፍ ቅዱሳችን በተደጋጋሚ የፅድቅ ልብሳችን የሆነውን ኢየሱስን ለብሰን እንድንመላለስ ያሳስባል።
ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት
ሮሜ 13፥14
እግዚአብሔር አምላክ ፍቅር ነው። ፍቅሩም የዓለምን ኋጢአት በልጁ ደም ሸፍኖ የሚያኖር ደግ አባት ነው። እርሱ በራሱ ፍቅር ተመስርቶ የሚኖር አፍቃሪ አምላክ ነው። ፍቅር የሆነው እርሱ ደግሞ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ብሎ በመፅሐፍ ነግሮናል በ1ኛ ጴጥ 4፥8። ከሁሉም ፍርድ እንድንድን የዘላለም ጠላታችን ከሆነው የወንድሞች ከሳሽ እንዲያፍር ያልተሸፈነ ማንነት አለን ብላችሁ የምታስቡ ፍፁም በሆነ መፀፀት ከኋጢአት ሁሉ በሚያድነው በጌታዬ ኢየሱስ ደም ሰውነታችሁን አጥባችሁ አዲሱን ልብሳችሁን ክርስቶስ ኢየሱስን ልበሱት። እግዚአብሔር የትናንት አይደለም የቅድሙን ማንነታችሁን አያይም ይልቁንም የአሁኑን ልባችሁን ነውና የሚያየው ደስ ይበላችሁ።
ምክር
ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።
ኤፌ 4፥22-24