Friday, 8 November 2019

ባህድ ፍም


እንደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነታ እግዚአብሔር የሚመለከውና የሚሰገድለት በመንፈስና በእውነት ነው እርሱም እንደነዚህ ያለውና ይሻልና ተብሎ እንደተፃፈ (ዮሐ 4፥23-24)። እርሱን የሚያመልክ ቢኖር  ከዚህ እውነት ውጪ መሆን አይችልም። መንፈሰ ነውና ያለ ገደብና መወሰን ይመለካል፣ እውነት ነውና ከልብ በሆነ እምነትና መታዘዝ በተግባር ይመለካል። አምልኮ ለአንድ ጌታ ብቻ የተገዛ ባሪያ ሊያቀርበው የሚገባ ፍጹምና ሁለንተናዊ መገዛት ነው። አምልኮ፣ ስግደትን፣ ውዳሴን፣ አክብሮትን ዝማሬን፣ ፀሎትን፣ መስዋዕትን፣ መልካም ስራን፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርን፣ ፍቅርን፣ ሕይወትን አጠቃሎ ለእግዚአብሔር አምላክ ብቻ መስጠት ማለት ነው። ስለዚህ አምልኮ ለአምላክህ ብቻ የሚገባና የሚሰጥ መገዛት ወይም ሁለንተናዊ ራስን መስጠት ማለት ነው።

እግዚአብሔርን እንደምንፈልገው ማምለክ አንችልም። እርሱ በሰጠን የአምልኮ መስፈርት ልናመልከው ነው ቃሉ የሚያዘው። አምልኮ ማለት አምላክ ለሆነ ብቻ መገዛት ማለት ነውና ከምናቀርበው የምስጋና መስዋህት ጀምሮ ለእግዚአብሔር መገዛት ፣ እርሱ እንደሚፈልገው ማምለክ ማለት ነው።

እግዚአብሔርን ስናመልክ እውነተኛነቱን መመዘን ያለብን የሁለንተናችን መለኪያ ወይም ቱንቢ በሆነው በሕያው ቃሉ መሰረት ነው። አምልኮ በብዙ መንገድ ይገለፃል በቃላት ሊሆን ይችላል ወይም በድርጊት ነገር ግን ዋናው ልናስተውለው የሚገባው ነገር ቢኖር የምናቀርበው አምልኮ ተመላኪው አምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ ላያና ደስ መሰኘቱ ላይ ነው። እኛን ያሰደሰተን ሁሉ እግዚአብሔርን አያስደስተውም። የደስታችን ምንጭ እርሱ ነውና። የእኛ ደስታ የሚመጣው የእርሱን ደስታ ተከትሎ  ነው። እኛን ደስ ብሎን እርሱ እውቅና ያልሰጠው አምልኮ ከንቱ ነው።  የራሳችንን ደስታ ፍለጋ የሚደረግ አምልኮ ሊኖረን አይገባም። ካላላበን እና ሞቅ ያለ ዝማሬ ተዘምሮ እንጀታችን ካልራሰ፣ አዋራው ካልጨሰ፣ ጅማታችን እስኪታጠፍና አመዳም እስክንመስል ድረስ ካልተራብን ያልፆምን የሚመስለን፣ የሚያምርብንን ልብስ ካለበስን የማንሰማ ከመሰለን፣ ዘማሪያንና ሰባኪያን ወይም ሌሎች ካልተገኙ በእግዚአብሔር ዘንድ እውቅና የማናገኝ መስሎን ከተሰማን አምልኳችንን መፈተሽ/መመርመር  ይኖርብናል።

የሰው ነገር አንጨምር:-

እግዚአብሔር በቃሉ በኩል ከነገረን የአምልኮ ስርዓት ውጪ አንዳች ነገር መጨመር እርሱን አያስደስትም። አምልኮ ላይ ያለው ትልቁ ችግር እግዚአብሔር ደስ እንዲለው የምንፈልገው የእኛን ደስ መሰኘት ተከትሎ ነው። እንዲህ ካለ ደስ መሰኘት ኋያሉ አምላክ በቸርነቱ ያውጣን።

እንኳን አይደለም በዚህ በክርስቶስ የፀጋ ዘመን/አዲስ ኪዳን በአሮጌው ብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ካዘዘው ውጪ ያለ አምልኮ በእርሱ ዘንድ ከንቱ ከመሆኑ ባሻገር ቁጣን ያመጣል።

<< የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ። እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ። >>
                                                  ዘሌዋ 10፥1-2

እሳቱን በተመለከተ ለእግዚአብሔር መሥዋት ከሚቀርብበት መሰዊያ አይደለም የአሮን ልጆች ያመጡት። ቅዱሱ መጽሐፍ የአሮን ልጆች እሳቱን ማምጣት የነበረባቸውን ሲነግረን

<< እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል፥ አይጠፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ እንጨት ያቃጥልበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ በዚያም የደኅንነትን መሥዋዕት ስብ ያቃጥላል። >>
                                                 ዘሌዋ 6፥12

<< በእግዚአብሔርም ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል፥ >>
                                                ዘሌዋ 16፥12

እርሱ ካዘዘው ዘወትር በፊቱ ከሚነደው ለክርስቶስ ኢየሱስ አምሳል ከሆነው ከመሰዊያው እሳት ውጪ ሌላ እሳት ከመንደር (ከሰፈር) ሰው ሲበርደው ወይም ምግብ ሊያበስልበት ካቀጣጠለው ከመንደር አምጥተው ጨመሩ። ይህ የሚያሳየው በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር መንደድ የነበረበት እሳት እንደጠፋ ነው። ይህ ደግሞ በአጭር ቃል እግዚአብሔርን ደስ አላሰኘም። በፊቱ ያልነበረ እሳት በመጨመራቸው የእግዚአብሔር የቁጣ እሳት ናዳብንና አብዮድን በላቸው። 

የኣሪት ዘሌዋውያን መጽሐፍ የሚያተኩረው ወይም በተደጋጋሚ የሚያወራው ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የተወደደ የመሓዛ ሽታ ያለው የሚቃጠል መሥዋት ነው። (ዘሌዋ 1፥13/17)  ይህም ጣፋጭ ሽታ ለክርስቶስ ምሳሌ  እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ በምዕራፍ 5 በቁጥር 2 ላይ እንዲህ ይገልፀዋል።

<< ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ >>

ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ እግዚአብሔርን ማምለክ እግዚአብሔር ራሱ በፈቀደልን መንገድ እንጂ እንደ እኛ የስጋ   ምኞትና መሻት አይደለም። የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ ተብሎ እንደተፃፈ (ገላ 5፥24) ከዚህ እውነት ራሳችንን ከሰቀልንበት ከጌታ መስቀል ያወረደና ለሰጋዊ ምኞትና ፍላጎት ራሱን ያመቻቸ አምላኪ አሁን እንደ አሮን ልጆች እንደ ናዳብና አብዮድ እሳት አይበላቸው ይሆናል ምክንያቱም ያለንበት ዘመን በጌታ ኢየሱስ የፀጋ ዘመን ነውና ነገር ግን ከፊት የሚጠብቀው የዘላለም እሳት አለ።

ለክርስቶስ አምሳሉና ጥላ ለሆነ አግልግሎት የመጣው ቁጣ በእሳት መበላት ከሆነ ለአካሉ እግዚአብሔር ደስ የተሰኘበት የመለኮትን ቁጣ ያበረደ እንደ አቤል ያላይደለ ዘወትር የሚያስምር ክቡር ደሙን ያፈሰሰው የተወደደ የዘላለም የመሓዛ ሽታ ኢየሱስ ላይ የሚረግ ጭማሪም ሆነ እግዚአብሔር ካዘዘው ሌላ አምልኮ መፈፀም ምን ያህል ቁጣው የበረታ ይሆን???

አብ እንደዚህ ያለውን ይሻል ካለ መፅሐፉ አለ ነው ከዚህ ውጪ የሚሻው የለምና። ከመሰዊያውም ሆነ ከመንደር ፍም አምጥቶ ቢቀላቀል ውጤቱ ያው ነው ምክንያቱም ከታዘዘው ውጪ ሆኗልና። በተቀደሰና ባልተቀደሰ ነገር በሚገኝ ውህደት እግዚአብሔር አይመለክም። ከተፃፈው ውጪ ያለ አምልኮ በእግዚአብሔር ፊት ቁጣን ያመጣል። ክርስቶስ ደግሞ ከእግዚአብሔር ሊመጣብን የነበረውና ቁጣንና ፍርድ ስለ ኋጢአት መክፈል ያለበትን ዋጋ ሁሉ ከፍሏልና በእያንዳንዳችን ፈንታ ሆኖ ሊመጣ የነበረውን ቁጣ ሁሉ በእርሱ ላይ አኑሯል። ከዚህ በላይ ለእግዚአብሔር የተወደደ የመሓዛ ሽታ የለም። እግዚአብሔርን ስናመልክ ቃሉን በመጠንቀቅና በማስተዋል እንደ ቃሉ መሆን ግድ ይሏል

<< እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። >>
                                                        ቆላ 3፥17
በጣም የሚገርመኝ የእግዚአብሔር ቃል እንኳ በሕይወት እያለን አይደለም ማንቀላፋታችን እንኳ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ 1ኛ ቆሮ 15፥20 ይናገራል። ታዲያ በሕይወት እያለን እስክናቀላፋ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ፍላጎትና ዓላማ ዋጋ አውጥቶ በገዛንና የራሱ ባደረገን በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እርሱን ማምለክ ነው። አሜን።

No comments:

Post a Comment