Friday, 8 November 2019

በክርስቶስ ውስጣዊ ራስን መቻል


             እግዚአብሔር በእኛ ላይ ካለው ፍላጎት አንዱ በየትኛውም ስፍራ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ራሳችንን እንድንሆን ነው። እኔ እከሌን መሆን አልችልም በአንፃሩም እከሌ እኔን አይተካም። በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ሆነ በዚህ እንደ እንግዳና መፃተኛ ሆነን በምንኖርበት ኑሮ ራሳችንን ችለን እንድንኖር  እግዚአብሔር ይፈልጋል።

             አንድ ክርስቲያን በሁለት ገፅታ ውስጥ ለአንድ ዓላማ ይኖራል ይህ ማለት ግን ሁለት ማንነት ይኖረዋል ማለት አይደለም። አንደኛው ገፅታው ኑሮው (ስጋዊ) ሲሆን ሁለተኛው ዘላለማዊ ሕይወት (መንፈሳዊ) ነው። ኑሮ ጊዜአዊና አላቂ ሲሆን በዚህ ምድር ላይ በምንቆይባቸው ዘመናት ውስጥ ለሰውነታችንና ለጤናችን እንዲሁም ከሰው ጋር ባለን ግንኙነት ቤተሰብን ጨምሮ የሚያስፈልገንን ለማግኘት የምናደርገው ውጣ ውረድ ነው። ዘላለማዊ ሕይወት ደግሞ ጌታችን መድሃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ የማያልቅና ዘመን የማይሽረው ልዩ መለኮታዊ ስጦታ ነው (ዮሐ 6፥47) (ዮሐ 11፥25/14፥6)። በሚያልፍ ኑሮ ውስጥ የሚገኝ የማያለፍ ዘላለማዊ ሕይወት ያለን ባለ ሁለት ገፅታ ሰዎች ነን።

              ታዲያ በሁለቱም ገፅታዎች ራሳችንን ችለን መቆም ያስፈልገናል። በየትኛውም ነገር በማንም ሰው ላይ መደገፍ የለብንም። ይልቁን ልንደገፍበት የሚገባ በድካማችን የሚራራልን፣ ባስፈለገን ጊዜ የሚደርስልን፣ በእጁ መዳፍ የያዘን ዋስትናችን፣ ልናምነው ዘንድ የተገባ ብቸኛ ማረፊያችን እርሱ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

              እርሱን በማመን የምናገኘው መንፈሳዊ ጥንካሬ ለነገሮች ሁሉ መቻልን ያድለናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች በፃፈው መልእከቱ በምዕራፍ 4 ቁጥር 13 ላይ '' ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። '' እንዳለው ከውጫዊ ሁኔታዎች ነፃ መሆን ባንችልም ልንጎዳ ወይም በተፅህኖ ውስጥ ሊጥለን አይገባም። የቱንም ያህል ፈተና ቢበዛብን፣ በፍፁም ይሆናል ብለን ያልጠበቅነው ፈተና ፊታችን ድንቅር ቢልም፣ ይሆናል ወይም ይሳካል ያልነው ጉዳይ ከመሆን ቢዘገይም በነዚህ ነገሮች ተይዘን ከመፍትኤ ውጪ መሆን የለብንም ምክንያቱም ውጫዊ እርዳታን የማይጠይቅ ውስጣዊ ራስን መቻል በክርስቶስ አለንና።

                 ይህን ስል ተማሪ ሳለው በታሪክ ትምህርት ውስጥ ወቅቱንና በማን ዘመነ መንግስት እንደሆነ ማስታወስ የማልችለው የጦነት ታሪክ ትዝ አለኝ። ጦርነት የተለያዩ  ስትራቴጂዎች አሉት። እናም ይህን ትዝ ያለኝን የጦነት ስልት ከማወራው ጉዳይ ጋራ እያቃጨለብኝ ስለሆነ ለመፃፍ ተገደድኩኝ።

              በአንድ ወቅት ኢትዮጵያዊያን ዘማቾች የተደፈረብንንና የተወሰደብንን ከተማ ለማስመለስ ወደ ቦታው ዘምቶ ነበረ። ታዲያ በወቅቱ የነበረው የዘማቾቹ ፊትአውራሪ ብልህ ስለነበረ ብዙ ድካም ሳያወጣና ደም ሳይፋሰስ እንዴት የጠላትን እጅ መማረክ እንዳለበት አሰበና አንድ ነገር ወሰነ። ጠላት የያዘውን ትንሿን ከተማ ዙሪያውን በመውረር ከተማይቱ የምትጠቀምበትን የውሃ ጉድጉውድ እና ከከተማ ውጪ የምትገኘውን የእህል መጋዘን ተቆጣጠረ። የጠላት የጦር ሰራዊትም በከተማው ውስጥ ያለውን መጠቀም እስኪያስችለው ድረስ መሽጎ ቢቆይም ሰራዊቶቹ ከፊሉ በውሃ ጥም ግማሹ በረሃብ ጠኔ ተመተው በመዳከማቸው ቀስ በቀስ የነበራቸው የመዋጋት ወኔም ደብዛው ጠፋ። በዚህ መሃል እንዳይዋጉ በማጣት ቸነፈር ውስጥ ጉልበታቸውን አጥተዋልና የነበራቸው ብቸኛ ነገር ያለ ውጊያ እጅ መስጠት ነበረና እጅ ሰጥተው ተማረኩ ከተማይቱም በሰላም በአገሬው ልጅ ተጥለቀለቀች።

                በዚህ ታሪክ ውስጥ እንደምንረዳው በውጫዊ እገዛ ወይም ጥገኝነት እስካለን ድረስ የሚመጣብንን የዓለም ፈተና ማለፍ አንችልም። ይህች ከተማ በውስጧ የውሃ ጉድጉዋድ እና የእህል አቅርቦት ቢኖራት ኖሮ ወይም ውጫዊ አቅርቦት ባያስፈልጋት ኖሮ ከውጪ ለሚመጣ ማንኛውም ሰልፍ ራሷን ችላ ትመክት ነበረ፣ ለደረሰባት ከበባ ስጋት የተጋለጠች ባልሆነች ነበር። ስለዚህም እኛም እንዲሁ በኑሮ ከዓለም ለሚመጣ ፈተና ኋይልን በሰጠን በክርስቶስ የተጋረጠብንን ማንኛውንም ፈተና በውስጥዊ ራስን መቻል ልንረታው ያስፈልገናል። ደግሞም በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳን የእግዚአብሔር ፀጋ አለና።

አንድ ሰው በንብ ቢነደፍ ውጫዊ የሰውነት ቆዳን ወይም አካልን እንጂ የውስጡን ማንነት አይነደፍም። ውጫዊ አካሉ በገሃዱ ዓለም ነውና ያለው በውጣ ውረድ ውስጥ ሊጎዳ ይችላል ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች የያዝነውን ይዘናልና በውስጣችን በሚኖረው በእርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ ብርታት የተነሳ ለምንም ነገር ዝግጁ መሆን አለብን። በውስጣችን ኋይልን ባስቀመጠው በእርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ለነገሮች ሁሉ ኋይልን ተላብሰናለና፣ ጥንካሬን አስታጥቆናልና፣ ብቃትን ተጎናፅፈናልና የመጣውን ተቀብለን ለመኖር ዝግጁ ልንሆን ያስፈልጋል። ባልተሳካ ወይም ባልሆነ ጉዳይ ተይዘን መባዘን የለብንም። ለእኛ ያለው መልካም ነገሮች ሁሉ የቱንም ያህል ፈተና ቢበዛበት ከመሆን  የሚከለክለው የለምና ባለመረበሽ እንጠብቀው። መጠበቅ በራሱ በክረስቶስ የሚገኝ ኋይል ነውና።

ለዛሬ አበቃሁ። ለሊታችሁ በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይባረክ። መልካሙን ከእርሱ ብቻ የሆነውን የምታዩበት የያዕቆብ ለሊት ይሁንላችሁ። አሜን

ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ። (ይሁ 1፥2)

No comments:

Post a Comment