Thursday, 7 November 2019

አጥንት የሌለው ሥጋ


የሰው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ በተለየ መልኩ የተበጀ የለም ሁላችንም በአንድ መንገድ ወደዚች ምድር የመጣን ነን። መፅሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል (ሐዋ 17፥26) እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ። ስለዚህ አንድ ብሔር ከየትኞቹም ዘሮች የተውጣጣ ቢሆንም ሁሉም የአዳም ዘር ናቸው።

ታዲያ ከዚህ ድርግም ያለ እውነት የወጣ የትኛውም አስተሳሰብ ልክ አይደለም ሆኖም አያውቅም። ልዩነት የለምና የእከሌስ ዘር ብልጫው ምንድነው? የሚለውን የሚመልስ እንድስኳ የለም አይኖርምም። ሰው ከሰውነቱ የሚወድቀው በስጋ ሲያስብ ነው። ለዚህም መፅሐፍ ቅዱሳችን ይመሰክርልናል

ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል (ሮሜ 8፥6-7)።

የእግዚአብሔር ቃል በወተትና በአጥንት ይመሰላል። ህፃን ልጅ ወተት የሚጠጣው አጥንቱ እንዲያድግ ነው። አጥንት ደግሞ ለሰው ልጅ ቆሞ ለመሄድ ዋናውን ሚና እንደሚጫወት እንዲሁ የእግዚአብሔር ቃልም በዘላለም ሕይወት ለመኖር ምርጫ የሌለበት ብቸኛ ምርጫ ነው። ከላይ ያነበብነው ቃል እንደሚነግረን ስለ መንፈስ ማሰብ ነው አጥንት የሚሆነን።

እንደው በአጭሩ ንገረኝ ካላችሁኝ ........

በስጋ ስለ ስጋ የሚያስቡ ሰዎች በዝተዋልና እያየን ያለነው አጥንት የሌላቸው ሰዎችን ነው። ሰው በዘር ሲያስብ አጥንት የሌለው በኪሎ እንደሚመዘን ጥሬ ስጋ ነው። እንደው ክምር ያለ መቆም የማይችል የተዘረገፈ ጥሬ ስጋ። የሰው ልጅ አጥንት ስላለው ነው ሰጋ የለበሰው።

ልብ በሉ እግዚአብሔር ሔዋንን ሲያበጅ አጥንትን እንጂ ስጋን ከአዳም አልወሰደም። " እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። " (ዘፍ 2፥21) እናም በዘር የምታስቡ የአጥንታችሁ ዘር ምንድነው? ከየትኛው የአጥንት ዘር ናችሁ? መልሱልኝ?

ለካ ሰው ቆሞ የሚሄደው አጥንት ስላለው ነው እንጂ በደምና ስጋው አይደለም።

ኢትዮጵያዬ ልጆችሽን በዘር የለየ ክፋ፤ ኃይልና ስልጣን ባለው በጌታችን በመድሃኒታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ስም የተመታ ይሁን። ዙሪያሽን የከበበው በአራቱም አቅጣጫ ያለ በየማዕዘኖችሽ ላይ ቆሞ ያደባብሽ የአባቴ የእግዚአብሔር የቁጣ እሳት ይብላው።

ልዩነቱ ጠፍቶ አንድነት በዝቶ ዓለም ሳይሆን ከሰላም ባለቤት ከሰላም አለቃ ከዓለሙ ቤዛ ሰላምሽ  እንዲበዛ ለምወዳድሽ ሀገር ለእምዬ ኢትዮጵያ ይሁን !!!

No comments:

Post a Comment