ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌ 2፥4-5
Friday, 8 November 2019
ተመልከቱ
እርስ በራሳችን በዘልማድ የምንተያይበት መንገድ ልክ አይደለም ብዬ አስባለው። መተያየት ካለብንም የእግዚአብሔር ቃል በሚያዘው መንገድ እንጂ ከልጅነታችን ጀምሮ በኖርንበትና በለመድነው ሁኔታ መሆን የለበትም እላለው። ከመተያየት ውጪ መሆን አይቻልም ምክንያቱም እየኖርን ያለነው በገሀዱ ዓለም ስለሆነ። ዓይናችን ማየት እስከቻለው ድረስ ያማትራል ነገር ግን የምናየውና የምንመለከተው ነገር የተገደበ ነው። ዓይናችን ማየት ከሚችለው በላይ ማየት ፈፅሞ አይችልም። ልክ እንደዚሁ በመንፈሳዊ እይታም ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ ልንመለከተው የሚገባ ምንም ነገር የለም።
ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ 15፥12 እንደተናገረው
'' እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።''
በዚህ ዓለም በሚኖረን ማንኛውም ዓይነት ግንኙነቶች ውስጥ አንድ ክርስቲያን ከዚህ ትህዛዝ የሚያስወጣው ሌላ ምክንያት ወይም መሰረት የለውም። እርስ በርሳችን ልንሆን የሚገባው ሁሉ ያለ ጉድለት ተፅፏል። እኛ የምንጨምረውም ሆነ የምናካትተው ነገር የለም። በመዋደድ ውስጥ ያሉ መልካምና እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ ግንኙነት ውስጥ ሆነን መኖር ይገባናል።
እርስ በራሳችን ልንተያይ የተገባ መንገድ የሌላው ሰው ስህተት ውስጥ መሆን የእኛን ልክነት አይነግረንም፣ የሌሎች ውድቀት እኛን አያነሳም፣ የሌሎች መክሰር የእኛን ማትረፍ አያረጋግጥም፣ የሌላው መጥፎነት የእኛን መልካምነት አያሳይም፣ የሌላው መራብ የእኛን መጥገብ አያሰኝም፣ የሌላው ሞኝነት የእኛን ብልጥነት አይናገርም፣ የሌላው ንፉግነት የእኛን ለጋስነት አያመጣውም። ይልቁንም አንዱ ከሌላው ሊወስደው የሚገባ ያለውን ጥንካሬና ጥሩ ነገሮችን ብቻ ነው። የሰዎችን ስህተት በማየት የምናጉረመርም ካለን ከእነሱ እኛ በምን ተሻልን?
የራሳችንን ብቻ ልክ አርገን የሌሎችን አብጠልጥለን በግንኙነቶች ውስጥ መዝለቅ ከባድ ነው። እኛ አለን ከምንለው ሀሳብ ወይም ተግባር ሌላ ሰው ካለው ነገር ጋር ማነፃፀር ሳይሆን ልክነቱ የራሳችን ሀሳብና ተግባር የሕይወታችን ቱንቢ ወይም መለኪያ በሆነው፣ ሕያውና በሚሰራው ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ ነፍስንና መንፈስን ጅማትንና ቅልጥምን እስከሚለይ ድረስ በሚወጋው የልብንም ስሜትና ሀሳብ በሚመረምረው በእግዚአብሔር ቃል ነው መመዘን ያለብን(ዕብ 4፥12)። ዳኛችን ቃሉ ነው።
ታዲያ የእግዚአብሔር ፈቃድ ቃሉ እንደነገረንና እንዳሳሰበን እርስ በራሳችን ባለን ግንኝነት ባለፈ ልናየውና ልንመለከተው የሚገባ ትልቁ አጀንዳ አለ። እርሱም
የእስራኤል ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ወጥተው በጉዞ ላይ እያሉ በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ በማጉረምረማቸው እግዚአብሔር ሕዝቡን እባቦችን በመስደድ አስነድፎ ቀጣቸው ብዙዎች ሞቱ። የተቀሩት ግን ከጥፋታቸው በመመለሳቸው እና በመፀፀታቸው እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው። ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ።(ኦሪ ዘኋ 21)
በእባብ ተነድፎ ከሞት የተረፉት ተመልከቱ የባለውን የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ በመስማት ነው። ታዲያ እኛም እንደ እንደ እንግዳና እንደ መፃተኛ በምንኖርበት በዚህ ምድረ በዳ ዓለም ልንመለከተው የሚገባን አለ። ለክርስቶስ ኢየሱስ ምሳሌና ጥላነት ያገለገለው በሕግ ኪዳን ዘመን እንኳ እንዴት በመመልከት ብቻ እንደተረፉ አይተናል። አሁንም ደግሞ አካል የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ በመገለጡ በዘላለም ኪዳን ደም የተገዛን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን በሰማያዊ ጥሪ ተቀብለን እንድንኖር የተከፈለልን ክቡር ዋጋ ያለን እኛ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ልጁን መድህነ ዓለም ክርስቶስን ኢየሱስን መመልከት ብቻ ነው። እግዚአብሔር በቀራኒዮ አደባባይ ስለሰው ልጅ ኋጢአትና አለመታዘዝ ነውራችንን ወስዶ እርቃኑን የሞተልንን ልጁ ብቻውን እንዲታይለት ይፈልጋል።
ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤ ዕብ 3፥1 ተብሎ እንደተፃፈ።
ተወዳጆች ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንኖር ዘንድ በልጁ የመረጠን የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ ነውና ብሎ በደማስቆ እንደ እግዚአብሔር ሀሳብና የልቡ ምክር ይኖር የነበረው ሐናንያ ለሐዋርያው ለቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረው (ሐዋ 22፥14) ሁላችንም በምድር ላይ ያለን ተልእኮ ጌቱችንና መድሃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በመመልከት ምስክሮቹ መሆን ነው።
በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። አሜን
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment