Friday, 8 November 2019

የትዕግሥት ጥግ



ትዕግሥት :-  ይቅር ባይ፣ ልበሰፊ ፣ ቻይ ፣ትሁት የሆነ የጠባይ መለያ ነው።

ከሰው ጋር ከግንኙነት ነፃ በማንሆንበት በዚህች ዓለም ስንኖር አስፈላጊ ነገር ከሆኑት መካከል አንዱ ትልቁ ትዕግሥት ነው። በዚች ምድር ሰፊውን የሕይወታችንን ክፍልንም የሚይዘው ነገር ደግሞ ግንኙነት ነው። ታዲያ በዚህ ሰፊ ግንኙነት ውስጥ ከሚያስፈልገን  ነገር አንዱ ይህ ትዕግሥት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ትዕግሥታቸው ከሚጠቀስላቸው ሰዎች አንዱ ደግሞ በሁላችንም ህሊና ውስጥ የሚመጣው ኢዩብ ነው።   

''ወንድሞች ሆይ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነብያትን ተመልከቱ። እነሆ፥ በትዕግስት የጸኑት ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዩብ እንደታገሰ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደፈፀመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።''  (ያዕ 5፥10-11)

በዚህ ቃል መሠረት፥ ከላይ እንደገለፅኩትም ኢዩብ በትዕግሥቱ በሁላችንም ህሊና የማይጠፋና ለብዙ ጊዜያትም በምሳሌነት ሲነሳ የምናውቀው ቢሆንም  ኢዩብ በታገሠው ትዕግሥት ከብጹዓን ቢመደብም ድካም ( ስንፍና ) ግን ነበረበት

'' ከዚያም በኋላ ኢዩብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ። ..................'' (ኢዩ 3፥1 ጀምሮ) ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ  ያለውን  ቃል ሲተላለፍ እና የነበረውን ፅናት ስፍራ አስለቅቆታል።

'' ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመስግንሃለሁ፤ሥራህ ድንቅ ነው፣ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።'' (መዝ 138፥14) የሚለውን ዘነጋና ሞቱን ተመኘ መፈጠሩንም ረገመ። በብዙ ችግር ውስጥ ቢሆንም ግን የትዕግሥት ልኩ ታየ።

ትዕግሥት ካደረግን ሊመጣ (ሊፈፀም) የሚችል ታላቅ ኋጢአት ሁሉ በድል የምናልፍበት አቅም እናገኛል። በትዕግሥት ውስጥ በመቆየታችን ለችግራችን የሚሆን የመፍትኤ ሀሳብ ይበዛልናል በመሆኑም ተቻኩለን ከምናደርጋቸው ድርጊቶች ይልቅ በዝግታ አስበን የምናገኘው መፍትሄ የተሻለ ነው።

ማንም እንኳ ኢዮብ ታጋሽ መሆኑን የተመሰከረለት ቢሆንም እንደውም ''ትዕሥት እንደ ኢዮብ ስጠን'' እየተባለ  ሲነገር ብንሰማም በእሱ ላይ መቆም እንደሌለብን እሙን ነው ምክንያቱም ኢዩብ ከታገሠው ትዕግሥት የሚልቅ ወይም ከኢዩብ አልፈን ልናወራለት፣ ልንመሰክርለት፣ ልንመለከተው እንዲሁም ልናስተውለው የሚገባን ሌላ ታጋሽ አለን። ሌላ ልናወራለት የሌለ የትዕግሥት ጥግ አለን። ኋጢያት የማያውቀው ወደር የሌለው የትዕግሥት ምሳሌ አለን። 

'' ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋይ የሆናችሁ ቅዱሳን  ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋሪያና ሊቀ ካህናት  ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤ '' (ዕብ 3፥1) ተብሎ እንደተፃፈ፥ ስለ ትዕግሥት ስናስብ ከኢዩብ  የሚበልጠውን የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕግሥት መርሳት የሌለብን።

(የመልእክቴም ዋና ሀሳብ ይህ ነው) ስለ ሁላችን ኃጢአት ሳይገባው መከራን ሲቀበል፣ በሌለበት በደል ሲከሰስ በሸላቾች እንደሚታረድ በግ ዝም ሲል፣ በቁስሉ ቁስላችንን ሲያክም፣ በቀራኒዮ በደሙ ሲዋጀን፣ በእርጥብ እንጨት ላይ በችንካር ሲሰቃይ፣ በተጠማው አንጀቱ ሆምጣጤ ሲጠጣ፣ እንደ ወንበዴ በመስቀል ሲሰቀል፣ በበደልና በኋጢአታችን ሙታን የነበርነውን ጽድቃችንም የመርገም ጨርቅ የሆነብን ስለእያንዳንዳችን ሞታችንን በሞቱ በትዕግሥት ሲሽር ከእግዚአብሔር ያጣነውን ልጅነት አስገኘን። ይህም የኢየሱስ ፍቅር ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ያሳየናል እንድም አፀፋ ሳይመልስ ሁሉ ታግሶ መዳናችንን ፈፅሞልናል።

'' የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቁጠሩ '' (2ኛ ጴጥ 3፥15)

ሰለዚህም ዩሐንስ በፍጥሞ ደሴት ሳለ '' መከራውንና መንግስቱን የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕግሥት የምካፈል''  እንዳለው ልንካፈለው የሚገባን የትዕግሥት ጥግ ከኢዩብ የላቀውን፣ አልፈን የማናወራለትን የኢየሱስን ትዕግሥት  ሊሆን ይገባል።
                               ደዊት 2008 የምህረት ዓመት  የተፃፈ

ተመልከቱ


            እርስ በራሳችን በዘልማድ የምንተያይበት መንገድ ልክ አይደለም ብዬ አስባለው። መተያየት ካለብንም የእግዚአብሔር ቃል በሚያዘው መንገድ እንጂ ከልጅነታችን ጀምሮ በኖርንበትና በለመድነው ሁኔታ መሆን የለበትም እላለው። ከመተያየት ውጪ መሆን አይቻልም ምክንያቱም እየኖርን ያለነው በገሀዱ ዓለም ስለሆነ። ዓይናችን ማየት እስከቻለው ድረስ ያማትራል ነገር ግን የምናየውና የምንመለከተው ነገር የተገደበ ነው። ዓይናችን ማየት ከሚችለው በላይ ማየት ፈፅሞ አይችልም። ልክ እንደዚሁ በመንፈሳዊ እይታም  ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ ልንመለከተው የሚገባ ምንም ነገር የለም።
          ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ 15፥12 እንደተናገረው

'' እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።''

        በዚህ ዓለም በሚኖረን ማንኛውም ዓይነት ግንኙነቶች ውስጥ አንድ ክርስቲያን ከዚህ ትህዛዝ የሚያስወጣው ሌላ ምክንያት ወይም  መሰረት የለውም። እርስ በርሳችን ልንሆን የሚገባው ሁሉ ያለ ጉድለት ተፅፏል። እኛ የምንጨምረውም ሆነ የምናካትተው ነገር የለም። በመዋደድ ውስጥ ያሉ መልካምና እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ ግንኙነት ውስጥ ሆነን መኖር ይገባናል።
        እርስ በራሳችን ልንተያይ የተገባ  መንገድ የሌላው ሰው ስህተት ውስጥ መሆን የእኛን ልክነት አይነግረንም፣ የሌሎች ውድቀት እኛን አያነሳም፣ የሌሎች መክሰር የእኛን ማትረፍ አያረጋግጥም፣ የሌላው መጥፎነት የእኛን መልካምነት አያሳይም፣ የሌላው መራብ የእኛን መጥገብ አያሰኝም፣ የሌላው ሞኝነት የእኛን ብልጥነት አይናገርም፣ የሌላው ንፉግነት የእኛን ለጋስነት አያመጣውም። ይልቁንም አንዱ ከሌላው ሊወስደው የሚገባ ያለውን ጥንካሬና ጥሩ ነገሮችን ብቻ ነው። የሰዎችን ስህተት በማየት የምናጉረመርም ካለን ከእነሱ እኛ በምን ተሻልን?
        የራሳችንን ብቻ ልክ አርገን የሌሎችን አብጠልጥለን በግንኙነቶች ውስጥ መዝለቅ ከባድ ነው። እኛ አለን  ከምንለው ሀሳብ ወይም ተግባር ሌላ ሰው ካለው ነገር ጋር ማነፃፀር ሳይሆን ልክነቱ የራሳችን ሀሳብና ተግባር የሕይወታችን ቱንቢ ወይም መለኪያ በሆነው፣ ሕያውና በሚሰራው ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ ነፍስንና መንፈስን ጅማትንና ቅልጥምን እስከሚለይ ድረስ በሚወጋው የልብንም ስሜትና ሀሳብ በሚመረምረው በእግዚአብሔር ቃል ነው መመዘን ያለብን(ዕብ 4፥12)። ዳኛችን ቃሉ ነው።
        ታዲያ የእግዚአብሔር ፈቃድ ቃሉ እንደነገረንና እንዳሳሰበን እርስ በራሳችን ባለን ግንኝነት ባለፈ ልናየውና ልንመለከተው የሚገባ ትልቁ አጀንዳ አለ። እርሱም
      የእስራኤል ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ወጥተው በጉዞ ላይ እያሉ በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ  በማጉረምረማቸው እግዚአብሔር ሕዝቡን እባቦችን በመስደድ አስነድፎ ቀጣቸው ብዙዎች ሞቱ። የተቀሩት ግን ከጥፋታቸው በመመለሳቸው እና በመፀፀታቸው እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው። ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ።(ኦሪ ዘኋ 21)
       በእባብ ተነድፎ ከሞት የተረፉት ተመልከቱ የባለውን የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ በመስማት ነው። ታዲያ እኛም እንደ እንደ እንግዳና እንደ መፃተኛ በምንኖርበት በዚህ ምድረ በዳ ዓለም ልንመለከተው የሚገባን አለ። ለክርስቶስ ኢየሱስ ምሳሌና ጥላነት ያገለገለው በሕግ ኪዳን ዘመን እንኳ እንዴት በመመልከት ብቻ  እንደተረፉ አይተናል። አሁንም ደግሞ አካል የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ በመገለጡ በዘላለም ኪዳን ደም የተገዛን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን በሰማያዊ  ጥሪ ተቀብለን እንድንኖር የተከፈለልን ክቡር ዋጋ ያለን እኛ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ልጁን መድህነ ዓለም ክርስቶስን ኢየሱስን  መመልከት ብቻ ነው። እግዚአብሔር በቀራኒዮ አደባባይ ስለሰው ልጅ ኋጢአትና አለመታዘዝ ነውራችንን ወስዶ እርቃኑን የሞተልንን ልጁ ብቻውን እንዲታይለት ይፈልጋል።

 ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤ ዕብ 3፥1 ተብሎ እንደተፃፈ።

ተወዳጆች ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንኖር ዘንድ በልጁ የመረጠን የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ ነውና ብሎ በደማስቆ እንደ እግዚአብሔር ሀሳብና የልቡ ምክር ይኖር የነበረው ሐናንያ ለሐዋርያው ለቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረው (ሐዋ 22፥14) ሁላችንም በምድር ላይ ያለን ተልእኮ ጌቱችንና መድሃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በመመልከት ምስክሮቹ መሆን ነው።

 በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። አሜን

በክርስቶስ ውስጣዊ ራስን መቻል


             እግዚአብሔር በእኛ ላይ ካለው ፍላጎት አንዱ በየትኛውም ስፍራ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ራሳችንን እንድንሆን ነው። እኔ እከሌን መሆን አልችልም በአንፃሩም እከሌ እኔን አይተካም። በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ሆነ በዚህ እንደ እንግዳና መፃተኛ ሆነን በምንኖርበት ኑሮ ራሳችንን ችለን እንድንኖር  እግዚአብሔር ይፈልጋል።

             አንድ ክርስቲያን በሁለት ገፅታ ውስጥ ለአንድ ዓላማ ይኖራል ይህ ማለት ግን ሁለት ማንነት ይኖረዋል ማለት አይደለም። አንደኛው ገፅታው ኑሮው (ስጋዊ) ሲሆን ሁለተኛው ዘላለማዊ ሕይወት (መንፈሳዊ) ነው። ኑሮ ጊዜአዊና አላቂ ሲሆን በዚህ ምድር ላይ በምንቆይባቸው ዘመናት ውስጥ ለሰውነታችንና ለጤናችን እንዲሁም ከሰው ጋር ባለን ግንኙነት ቤተሰብን ጨምሮ የሚያስፈልገንን ለማግኘት የምናደርገው ውጣ ውረድ ነው። ዘላለማዊ ሕይወት ደግሞ ጌታችን መድሃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ የማያልቅና ዘመን የማይሽረው ልዩ መለኮታዊ ስጦታ ነው (ዮሐ 6፥47) (ዮሐ 11፥25/14፥6)። በሚያልፍ ኑሮ ውስጥ የሚገኝ የማያለፍ ዘላለማዊ ሕይወት ያለን ባለ ሁለት ገፅታ ሰዎች ነን።

              ታዲያ በሁለቱም ገፅታዎች ራሳችንን ችለን መቆም ያስፈልገናል። በየትኛውም ነገር በማንም ሰው ላይ መደገፍ የለብንም። ይልቁን ልንደገፍበት የሚገባ በድካማችን የሚራራልን፣ ባስፈለገን ጊዜ የሚደርስልን፣ በእጁ መዳፍ የያዘን ዋስትናችን፣ ልናምነው ዘንድ የተገባ ብቸኛ ማረፊያችን እርሱ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

              እርሱን በማመን የምናገኘው መንፈሳዊ ጥንካሬ ለነገሮች ሁሉ መቻልን ያድለናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች በፃፈው መልእከቱ በምዕራፍ 4 ቁጥር 13 ላይ '' ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። '' እንዳለው ከውጫዊ ሁኔታዎች ነፃ መሆን ባንችልም ልንጎዳ ወይም በተፅህኖ ውስጥ ሊጥለን አይገባም። የቱንም ያህል ፈተና ቢበዛብን፣ በፍፁም ይሆናል ብለን ያልጠበቅነው ፈተና ፊታችን ድንቅር ቢልም፣ ይሆናል ወይም ይሳካል ያልነው ጉዳይ ከመሆን ቢዘገይም በነዚህ ነገሮች ተይዘን ከመፍትኤ ውጪ መሆን የለብንም ምክንያቱም ውጫዊ እርዳታን የማይጠይቅ ውስጣዊ ራስን መቻል በክርስቶስ አለንና።

                 ይህን ስል ተማሪ ሳለው በታሪክ ትምህርት ውስጥ ወቅቱንና በማን ዘመነ መንግስት እንደሆነ ማስታወስ የማልችለው የጦነት ታሪክ ትዝ አለኝ። ጦርነት የተለያዩ  ስትራቴጂዎች አሉት። እናም ይህን ትዝ ያለኝን የጦነት ስልት ከማወራው ጉዳይ ጋራ እያቃጨለብኝ ስለሆነ ለመፃፍ ተገደድኩኝ።

              በአንድ ወቅት ኢትዮጵያዊያን ዘማቾች የተደፈረብንንና የተወሰደብንን ከተማ ለማስመለስ ወደ ቦታው ዘምቶ ነበረ። ታዲያ በወቅቱ የነበረው የዘማቾቹ ፊትአውራሪ ብልህ ስለነበረ ብዙ ድካም ሳያወጣና ደም ሳይፋሰስ እንዴት የጠላትን እጅ መማረክ እንዳለበት አሰበና አንድ ነገር ወሰነ። ጠላት የያዘውን ትንሿን ከተማ ዙሪያውን በመውረር ከተማይቱ የምትጠቀምበትን የውሃ ጉድጉውድ እና ከከተማ ውጪ የምትገኘውን የእህል መጋዘን ተቆጣጠረ። የጠላት የጦር ሰራዊትም በከተማው ውስጥ ያለውን መጠቀም እስኪያስችለው ድረስ መሽጎ ቢቆይም ሰራዊቶቹ ከፊሉ በውሃ ጥም ግማሹ በረሃብ ጠኔ ተመተው በመዳከማቸው ቀስ በቀስ የነበራቸው የመዋጋት ወኔም ደብዛው ጠፋ። በዚህ መሃል እንዳይዋጉ በማጣት ቸነፈር ውስጥ ጉልበታቸውን አጥተዋልና የነበራቸው ብቸኛ ነገር ያለ ውጊያ እጅ መስጠት ነበረና እጅ ሰጥተው ተማረኩ ከተማይቱም በሰላም በአገሬው ልጅ ተጥለቀለቀች።

                በዚህ ታሪክ ውስጥ እንደምንረዳው በውጫዊ እገዛ ወይም ጥገኝነት እስካለን ድረስ የሚመጣብንን የዓለም ፈተና ማለፍ አንችልም። ይህች ከተማ በውስጧ የውሃ ጉድጉዋድ እና የእህል አቅርቦት ቢኖራት ኖሮ ወይም ውጫዊ አቅርቦት ባያስፈልጋት ኖሮ ከውጪ ለሚመጣ ማንኛውም ሰልፍ ራሷን ችላ ትመክት ነበረ፣ ለደረሰባት ከበባ ስጋት የተጋለጠች ባልሆነች ነበር። ስለዚህም እኛም እንዲሁ በኑሮ ከዓለም ለሚመጣ ፈተና ኋይልን በሰጠን በክርስቶስ የተጋረጠብንን ማንኛውንም ፈተና በውስጥዊ ራስን መቻል ልንረታው ያስፈልገናል። ደግሞም በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳን የእግዚአብሔር ፀጋ አለና።

አንድ ሰው በንብ ቢነደፍ ውጫዊ የሰውነት ቆዳን ወይም አካልን እንጂ የውስጡን ማንነት አይነደፍም። ውጫዊ አካሉ በገሃዱ ዓለም ነውና ያለው በውጣ ውረድ ውስጥ ሊጎዳ ይችላል ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች የያዝነውን ይዘናልና በውስጣችን በሚኖረው በእርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ ብርታት የተነሳ ለምንም ነገር ዝግጁ መሆን አለብን። በውስጣችን ኋይልን ባስቀመጠው በእርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ለነገሮች ሁሉ ኋይልን ተላብሰናለና፣ ጥንካሬን አስታጥቆናልና፣ ብቃትን ተጎናፅፈናልና የመጣውን ተቀብለን ለመኖር ዝግጁ ልንሆን ያስፈልጋል። ባልተሳካ ወይም ባልሆነ ጉዳይ ተይዘን መባዘን የለብንም። ለእኛ ያለው መልካም ነገሮች ሁሉ የቱንም ያህል ፈተና ቢበዛበት ከመሆን  የሚከለክለው የለምና ባለመረበሽ እንጠብቀው። መጠበቅ በራሱ በክረስቶስ የሚገኝ ኋይል ነውና።

ለዛሬ አበቃሁ። ለሊታችሁ በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይባረክ። መልካሙን ከእርሱ ብቻ የሆነውን የምታዩበት የያዕቆብ ለሊት ይሁንላችሁ። አሜን

ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ። (ይሁ 1፥2)

ባህድ ፍም


እንደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነታ እግዚአብሔር የሚመለከውና የሚሰገድለት በመንፈስና በእውነት ነው እርሱም እንደነዚህ ያለውና ይሻልና ተብሎ እንደተፃፈ (ዮሐ 4፥23-24)። እርሱን የሚያመልክ ቢኖር  ከዚህ እውነት ውጪ መሆን አይችልም። መንፈሰ ነውና ያለ ገደብና መወሰን ይመለካል፣ እውነት ነውና ከልብ በሆነ እምነትና መታዘዝ በተግባር ይመለካል። አምልኮ ለአንድ ጌታ ብቻ የተገዛ ባሪያ ሊያቀርበው የሚገባ ፍጹምና ሁለንተናዊ መገዛት ነው። አምልኮ፣ ስግደትን፣ ውዳሴን፣ አክብሮትን ዝማሬን፣ ፀሎትን፣ መስዋዕትን፣ መልካም ስራን፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርን፣ ፍቅርን፣ ሕይወትን አጠቃሎ ለእግዚአብሔር አምላክ ብቻ መስጠት ማለት ነው። ስለዚህ አምልኮ ለአምላክህ ብቻ የሚገባና የሚሰጥ መገዛት ወይም ሁለንተናዊ ራስን መስጠት ማለት ነው።

እግዚአብሔርን እንደምንፈልገው ማምለክ አንችልም። እርሱ በሰጠን የአምልኮ መስፈርት ልናመልከው ነው ቃሉ የሚያዘው። አምልኮ ማለት አምላክ ለሆነ ብቻ መገዛት ማለት ነውና ከምናቀርበው የምስጋና መስዋህት ጀምሮ ለእግዚአብሔር መገዛት ፣ እርሱ እንደሚፈልገው ማምለክ ማለት ነው።

እግዚአብሔርን ስናመልክ እውነተኛነቱን መመዘን ያለብን የሁለንተናችን መለኪያ ወይም ቱንቢ በሆነው በሕያው ቃሉ መሰረት ነው። አምልኮ በብዙ መንገድ ይገለፃል በቃላት ሊሆን ይችላል ወይም በድርጊት ነገር ግን ዋናው ልናስተውለው የሚገባው ነገር ቢኖር የምናቀርበው አምልኮ ተመላኪው አምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ ላያና ደስ መሰኘቱ ላይ ነው። እኛን ያሰደሰተን ሁሉ እግዚአብሔርን አያስደስተውም። የደስታችን ምንጭ እርሱ ነውና። የእኛ ደስታ የሚመጣው የእርሱን ደስታ ተከትሎ  ነው። እኛን ደስ ብሎን እርሱ እውቅና ያልሰጠው አምልኮ ከንቱ ነው።  የራሳችንን ደስታ ፍለጋ የሚደረግ አምልኮ ሊኖረን አይገባም። ካላላበን እና ሞቅ ያለ ዝማሬ ተዘምሮ እንጀታችን ካልራሰ፣ አዋራው ካልጨሰ፣ ጅማታችን እስኪታጠፍና አመዳም እስክንመስል ድረስ ካልተራብን ያልፆምን የሚመስለን፣ የሚያምርብንን ልብስ ካለበስን የማንሰማ ከመሰለን፣ ዘማሪያንና ሰባኪያን ወይም ሌሎች ካልተገኙ በእግዚአብሔር ዘንድ እውቅና የማናገኝ መስሎን ከተሰማን አምልኳችንን መፈተሽ/መመርመር  ይኖርብናል።

የሰው ነገር አንጨምር:-

እግዚአብሔር በቃሉ በኩል ከነገረን የአምልኮ ስርዓት ውጪ አንዳች ነገር መጨመር እርሱን አያስደስትም። አምልኮ ላይ ያለው ትልቁ ችግር እግዚአብሔር ደስ እንዲለው የምንፈልገው የእኛን ደስ መሰኘት ተከትሎ ነው። እንዲህ ካለ ደስ መሰኘት ኋያሉ አምላክ በቸርነቱ ያውጣን።

እንኳን አይደለም በዚህ በክርስቶስ የፀጋ ዘመን/አዲስ ኪዳን በአሮጌው ብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ካዘዘው ውጪ ያለ አምልኮ በእርሱ ዘንድ ከንቱ ከመሆኑ ባሻገር ቁጣን ያመጣል።

<< የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ። እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ። >>
                                                  ዘሌዋ 10፥1-2

እሳቱን በተመለከተ ለእግዚአብሔር መሥዋት ከሚቀርብበት መሰዊያ አይደለም የአሮን ልጆች ያመጡት። ቅዱሱ መጽሐፍ የአሮን ልጆች እሳቱን ማምጣት የነበረባቸውን ሲነግረን

<< እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል፥ አይጠፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ እንጨት ያቃጥልበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ በዚያም የደኅንነትን መሥዋዕት ስብ ያቃጥላል። >>
                                                 ዘሌዋ 6፥12

<< በእግዚአብሔርም ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል፥ >>
                                                ዘሌዋ 16፥12

እርሱ ካዘዘው ዘወትር በፊቱ ከሚነደው ለክርስቶስ ኢየሱስ አምሳል ከሆነው ከመሰዊያው እሳት ውጪ ሌላ እሳት ከመንደር (ከሰፈር) ሰው ሲበርደው ወይም ምግብ ሊያበስልበት ካቀጣጠለው ከመንደር አምጥተው ጨመሩ። ይህ የሚያሳየው በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር መንደድ የነበረበት እሳት እንደጠፋ ነው። ይህ ደግሞ በአጭር ቃል እግዚአብሔርን ደስ አላሰኘም። በፊቱ ያልነበረ እሳት በመጨመራቸው የእግዚአብሔር የቁጣ እሳት ናዳብንና አብዮድን በላቸው። 

የኣሪት ዘሌዋውያን መጽሐፍ የሚያተኩረው ወይም በተደጋጋሚ የሚያወራው ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የተወደደ የመሓዛ ሽታ ያለው የሚቃጠል መሥዋት ነው። (ዘሌዋ 1፥13/17)  ይህም ጣፋጭ ሽታ ለክርስቶስ ምሳሌ  እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ በምዕራፍ 5 በቁጥር 2 ላይ እንዲህ ይገልፀዋል።

<< ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ >>

ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ እግዚአብሔርን ማምለክ እግዚአብሔር ራሱ በፈቀደልን መንገድ እንጂ እንደ እኛ የስጋ   ምኞትና መሻት አይደለም። የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ ተብሎ እንደተፃፈ (ገላ 5፥24) ከዚህ እውነት ራሳችንን ከሰቀልንበት ከጌታ መስቀል ያወረደና ለሰጋዊ ምኞትና ፍላጎት ራሱን ያመቻቸ አምላኪ አሁን እንደ አሮን ልጆች እንደ ናዳብና አብዮድ እሳት አይበላቸው ይሆናል ምክንያቱም ያለንበት ዘመን በጌታ ኢየሱስ የፀጋ ዘመን ነውና ነገር ግን ከፊት የሚጠብቀው የዘላለም እሳት አለ።

ለክርስቶስ አምሳሉና ጥላ ለሆነ አግልግሎት የመጣው ቁጣ በእሳት መበላት ከሆነ ለአካሉ እግዚአብሔር ደስ የተሰኘበት የመለኮትን ቁጣ ያበረደ እንደ አቤል ያላይደለ ዘወትር የሚያስምር ክቡር ደሙን ያፈሰሰው የተወደደ የዘላለም የመሓዛ ሽታ ኢየሱስ ላይ የሚረግ ጭማሪም ሆነ እግዚአብሔር ካዘዘው ሌላ አምልኮ መፈፀም ምን ያህል ቁጣው የበረታ ይሆን???

አብ እንደዚህ ያለውን ይሻል ካለ መፅሐፉ አለ ነው ከዚህ ውጪ የሚሻው የለምና። ከመሰዊያውም ሆነ ከመንደር ፍም አምጥቶ ቢቀላቀል ውጤቱ ያው ነው ምክንያቱም ከታዘዘው ውጪ ሆኗልና። በተቀደሰና ባልተቀደሰ ነገር በሚገኝ ውህደት እግዚአብሔር አይመለክም። ከተፃፈው ውጪ ያለ አምልኮ በእግዚአብሔር ፊት ቁጣን ያመጣል። ክርስቶስ ደግሞ ከእግዚአብሔር ሊመጣብን የነበረውና ቁጣንና ፍርድ ስለ ኋጢአት መክፈል ያለበትን ዋጋ ሁሉ ከፍሏልና በእያንዳንዳችን ፈንታ ሆኖ ሊመጣ የነበረውን ቁጣ ሁሉ በእርሱ ላይ አኑሯል። ከዚህ በላይ ለእግዚአብሔር የተወደደ የመሓዛ ሽታ የለም። እግዚአብሔርን ስናመልክ ቃሉን በመጠንቀቅና በማስተዋል እንደ ቃሉ መሆን ግድ ይሏል

<< እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። >>
                                                        ቆላ 3፥17
በጣም የሚገርመኝ የእግዚአብሔር ቃል እንኳ በሕይወት እያለን አይደለም ማንቀላፋታችን እንኳ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ 1ኛ ቆሮ 15፥20 ይናገራል። ታዲያ በሕይወት እያለን እስክናቀላፋ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ፍላጎትና ዓላማ ዋጋ አውጥቶ በገዛንና የራሱ ባደረገን በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እርሱን ማምለክ ነው። አሜን።

Thursday, 7 November 2019

አጥንት የሌለው ሥጋ


የሰው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ በተለየ መልኩ የተበጀ የለም ሁላችንም በአንድ መንገድ ወደዚች ምድር የመጣን ነን። መፅሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል (ሐዋ 17፥26) እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ። ስለዚህ አንድ ብሔር ከየትኞቹም ዘሮች የተውጣጣ ቢሆንም ሁሉም የአዳም ዘር ናቸው።

ታዲያ ከዚህ ድርግም ያለ እውነት የወጣ የትኛውም አስተሳሰብ ልክ አይደለም ሆኖም አያውቅም። ልዩነት የለምና የእከሌስ ዘር ብልጫው ምንድነው? የሚለውን የሚመልስ እንድስኳ የለም አይኖርምም። ሰው ከሰውነቱ የሚወድቀው በስጋ ሲያስብ ነው። ለዚህም መፅሐፍ ቅዱሳችን ይመሰክርልናል

ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል (ሮሜ 8፥6-7)።

የእግዚአብሔር ቃል በወተትና በአጥንት ይመሰላል። ህፃን ልጅ ወተት የሚጠጣው አጥንቱ እንዲያድግ ነው። አጥንት ደግሞ ለሰው ልጅ ቆሞ ለመሄድ ዋናውን ሚና እንደሚጫወት እንዲሁ የእግዚአብሔር ቃልም በዘላለም ሕይወት ለመኖር ምርጫ የሌለበት ብቸኛ ምርጫ ነው። ከላይ ያነበብነው ቃል እንደሚነግረን ስለ መንፈስ ማሰብ ነው አጥንት የሚሆነን።

እንደው በአጭሩ ንገረኝ ካላችሁኝ ........

በስጋ ስለ ስጋ የሚያስቡ ሰዎች በዝተዋልና እያየን ያለነው አጥንት የሌላቸው ሰዎችን ነው። ሰው በዘር ሲያስብ አጥንት የሌለው በኪሎ እንደሚመዘን ጥሬ ስጋ ነው። እንደው ክምር ያለ መቆም የማይችል የተዘረገፈ ጥሬ ስጋ። የሰው ልጅ አጥንት ስላለው ነው ሰጋ የለበሰው።

ልብ በሉ እግዚአብሔር ሔዋንን ሲያበጅ አጥንትን እንጂ ስጋን ከአዳም አልወሰደም። " እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። " (ዘፍ 2፥21) እናም በዘር የምታስቡ የአጥንታችሁ ዘር ምንድነው? ከየትኛው የአጥንት ዘር ናችሁ? መልሱልኝ?

ለካ ሰው ቆሞ የሚሄደው አጥንት ስላለው ነው እንጂ በደምና ስጋው አይደለም።

ኢትዮጵያዬ ልጆችሽን በዘር የለየ ክፋ፤ ኃይልና ስልጣን ባለው በጌታችን በመድሃኒታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ስም የተመታ ይሁን። ዙሪያሽን የከበበው በአራቱም አቅጣጫ ያለ በየማዕዘኖችሽ ላይ ቆሞ ያደባብሽ የአባቴ የእግዚአብሔር የቁጣ እሳት ይብላው።

ልዩነቱ ጠፍቶ አንድነት በዝቶ ዓለም ሳይሆን ከሰላም ባለቤት ከሰላም አለቃ ከዓለሙ ቤዛ ሰላምሽ  እንዲበዛ ለምወዳድሽ ሀገር ለእምዬ ኢትዮጵያ ይሁን !!!

ሥጋ የለበሰ ሁሉ


ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና። አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል (ሮሜ 3፥20-21)

በዚህ ቃል '' ሁሉ '' የሚለውን ቃል ከሰው ልጅ ፍጥረት ጀምሮ እስከ አሁን የምንኖረውን እንዲሁም ወደ ፊት የሚኖሩትንም የሰው ልጅን በሙሉ ያካተተ ነው። ታዲያ ይህ '' ሁሉ '' የሚለው ቃል ምንም እንኳን ሁለት ፊደል ቢሆንም ይህን ያህል ሰው በመወከሉ ከባድ ሀይለ ቃል ነው ማለት ማጋነን አይደለም።

ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሉቃ 3፥3-6) ይህ በ''ሁሉ'' የተጠቀለለው ሥጋ ለባሽ ያለው ብቸኛ መዳኛ እግዚአብሔር ያዘጋጀው መንገድ ነው። ለዚህም መፅሐፍ ቅዱሳችን ሲናገር

" ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። " (ገላ 2፥16) ይላል።

በመሆኑም ሥጋ ለባሽ ሆኖ በሕግ ሥራ (በሥራ) እጸድቃለው ብሎ ደፋ ቀና ቁጭ ብድግ የሚል ካለ ራሱን እንደ ሰው ማየት የተሳነው ብቻ ነው። እናም

ወገን ስማ
ባትሰማኝም ስማ
ባትወደውም ስማ
ባትፈልግም ስማ
ላልሰማም አሰማ
ዝም ብለህ አታቅማማ
በሆነው ባልሆነው ትግል አትግጠማ
በሥራ አትድንማ
እኮ በምን ሥራህ እረ ዘርዝርማ
ተው...ተው... ተው እንዳትሞክረው
ጭራሽ አታስበው
ላያድንህ ከሞት
ላያስጥልህ ከእሳት
ላያስገኝ ልጅነት
ላይኖርህ ነፃነት
ላያወጣ አርነት
ላይሆንልህ ሕይወት
ላይሰማህ እረፍት
የድንግዝግዝ ልፋት
የማትመካበት
አንተ የምታፍርበት
አንቺ የምታፍሪበት
አያድንም ከሞት
.
.
.
እኔም ዛሬ ፃፍኩት
" ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። " (1ኛ ቆሮ  1፥29)