Monday, 8 November 2021

ተሀድሶአዊ የወንጌል እንቅስቃሴን በወንጌል የማዳን ጥሪ

 


የተሀድሶ ቤተክርስቲያን የተነሳባትን ነፋስ ንጹዉን ወንጌል ሰባኪነቷን ጥላሸት የሚቀቡባት ላይ እንደ ቃሉ የሆነ አጸፋዊ መልስ ልትሰጥ ይገባል። በእርግጥ በየአጥቢያው የተደረጉ እንቅስቃሴዎችና የማጽኛ ፕሮግራሞች እንደነበሩ ባውቅም በቂ ነው ብዬ አላስብም። ስለሆነም በሰሞኑ የወንጌል እንቅሳቃሴን የመረበሽ ተግባርን በተመለከተ በጉባኤያት ብቻ ሳይሆን በዚህ ስሟንና ተግባሯን እያቀለሉ በሚያሰራጩቧት በማህበራዊ ሚዲያ ምዕመኗቿም ጭምር ተሀድሶአዊውን የወንጌል እንቅስቃሴን የተከበረውን ስሟንና ስራዋን ኢየሱስን በመስበክና በስሙ የሚመጣውን ማንኛውንም ተግዳሮት ተጋፍጣ በወንጌል እንቅስቃሴ ፊታውራሪ ልንሆን ይገባል።

የዳንበትን ቅዱስን ወንጌል ያለ ሽቀጣ የሰማንበትን ብዙ የሕይወት መስዋህትነት የተከፈለበትን የከበረው የወንጌል እንቅስቃሴ ዛሬ ላይ በተወሰኑ በአገልግሎቱ ውስጥ በነበሩ ሰዎች በግል ባላቸው ፍላጎትና ችግር የተነሳ ወዳልተገባ ስም ማጥፋትና አገልግሎቱን ወደ ማርከስ እንዲሁም ወደ ማቃለል እንቅስቃሴ ውስጥ እንደገቡ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ለእነዚህ ሰዎች ምህረትን እየለመንን ለአገልግሎቱ ደግሞ ብርታት እንዲጨምር መትጋት ይኖርብናል። ስደትና ወታወክ(መበታተን) ሲፈጥር የምናውቀው ወደ ተሻለ አገልግሎት ነውና (ሐዋ 8) አንፍራ።

እናም ይህ መጥፎና አደገኛ ወደ እያንዳንዱ ማህበረ ምዕመናን ቤት እየገባ በተለይም ከቅርብ ጊዜአት ወዲህ ለወንጌል ልባቸውን ከፍተው መሰራት ለጀመሩ ወንድምና እህቶች ልባቸው በብዙ ስለተጎዳና ስለተከፈለ ቤተክርስቲያናትም ሆነ ልጆችዋ እንዲሁም በዚህ የወንጌል እንቅስቃሴ ቃሉን በመስማት ያተረፋችሁ በሙሉ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ከፍ ብሎ የተነሳውን የሰውን ሀሳብ በማፍረስና ለክርስቶስ ኢየሱስ መታዘዝም አእምሮን ሁሉ ወደሚማርክ ዘመቻ ከሁላችሁ እጅግ የማንስ እኔ እንድትገቡ  ላነቃ እወዳለው። 

ወንጌልን ከየትኛው ጊዜ በበለጠ ሊሰበክ ይገባዋል እግዚአብሔርም በነገር ሁሉ በእርግጥ ይረዳናል። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። (ዕብራውያን 4፥16)

ለአገልግሎት ነውን?

የኢየሱስ የክብሩ ወንጌል የሚሰበከው ወንጌሉ ራሱ በሚሰጠው አቅምና ጸጋ ነው። አሁን አሁን እያየን ያለነው ከጸጋው ውጪ በውሸትና በማስመሰል ወንጌል እንሰራለን የሚሉ መበራከታቸው ነው። ወንጌል ቀጥተኛ መንገድ ይፈልጋል ይህም ኢየሱስን ብቻውን በመግለጥ በጨለማ ላሉት ብርሃን እንዲበራላቸው ወንጌሉ ራሱ የሚጠይቀውን መንገድ መከተል። ሐዋርያት በእጃቸው የተቀበሉትን ይህን ቅዱስ ወንጌል ያበዙት በቀጥተኛ መንገድ እስከ ሕይወት መስዋህትነት በመክፈል ነው። በዚህ ሁሉ ግን ወንጌልን ለጥቅማቸውና በግል ፍላጎታቸው ተነድተው እንዳላገለገሉ ለማንም ግልፅ ነው። ለዛም ነው የሕይወት መስዋህተንት ያስከፈላቸው። 

እንደዘመኑ አገልጋዬች ቢሆኑ በአይሁድ መቅደስ ገብተው ራሱን በመሰዋት ለዓለም ያበረከተውን ቅዱሱን ደም በማክፋፋት የኮርማና የበግ ጠቦት መስዋህት እያቀረቡ፣ አይሁድ እንዳይከፋው ኢየሱስ በበረት የተወለደ የዮሴፍ ልጅ ነው እያሉ ወንጌልን እንሰብካለን ቢሉ ዛሬ ላይ ንጹህ ወንጌል  ባላየን ነበር። 

ሰሞኑን በዚህ '' ለአገልግሎት ነው '' በሚል ካባ የተሸፈኑ የተወሰኑ አገልጋዬች የኢየሱስን ብቸኛ የአዲስ ኪዳን መካከለኝነትንና ሊቀካህንነት ዝቅ በማድረግ ፍጡራንን በእርሱ ቦታ በመተካት ወደ ሚነገርበት አገልግሎት ፈቀቅ የማለታቸው  ሚስጢር ይህ ስጋና ደም የፈጠረው የማምለጫና ማታለያ መንገዳቸው '' ለአገልግሎት ነው '' የሚል ከባድ የዓለም መንገድ ነው። 

ኢየሱስ በእነሱ አባባል ለጊዜው ብቸኛ መድኃኒት አይደለም።  ሌሎች ፍጡራንና መላእክት በእርሱ ቦታ ተተክተው ወንጌል ተሸቃቅጦ ይሰበካል፣ የሚያገለግሉት ሕዝብም እንዳይከፋው መዝሙርና ምስጋና ይቀርብላቸውል ለምን? መልሳቸው '' ለአገልግሎት ሲባል ነው ''። 

ሁላችት የተዋጀነበትን ቅዱስ ደም ወደ ጎን በመተው መጽሐፍ ቅዱሳችንም በግልፅና በብቸኝነት የነገረንን (የኢሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻል) የሚለውን ችላ በማለት እልፍ መንገድ እንዳለ ወደሚነገርበት ምኩራብ መግባት ይህም የፈረደበት '' ለአገልግሎት ነው '' የሚል ታፔላ ነው። 

ቦታና ጊዜ የማይወሰንለት በእውነትና በመንፈስ የሚመለከው ጌታ እግዚአብሔርን በሁሉም ስፍራ ሆኖ ፀሎትንና ምስጋናን የሚቀበል ሆኖ ሳለ ከሞቱ በኃላ ወደ ሚዘምርላቸው እንዲሁም እንዲማልዱ ወደ ሚፀለይላቸውና ለእግዚአብሔር የሚደረገውን አምልኮታዊ ስርአት አንዳች ነገር ሳይቀነስባቸው ተጋርተው ወደሚሰጣቸው ድንኳን መግባት ብልሃት የተፈጠረው ይህ '' ለአገልግሎት ነው '' የሚል አመክንዬ ነው።  

ኢየሱስ የሚለውን ስም ብቻውን መጠራት የለበትም ድስት እንኳ ሁለት ጆሮ አለው ብለው ከሚያስቡ ጋር ገብተው ''ኢየሱስ'' ላለማለት ወልድ ብለው መናገር መጀመራቸውን ሳይ ለአገልግሎት ነው? ብዬ ለማሰብ ሞከርኩ በረገጡት ጫማ ራሴን ከትቼ ለማየት ተጣጣርኩ ግን ሊዋጥልኝ አልቻለም። ወልድ ማለት በራሱ ችግር አለው እያልኩ አይደለም ግን ወልድ ያሉት ኢየሱስ ላለማለት እንደሆነ በግልፅ ሳላየው ነው። 

የግድ ለመመሳሰል ዮሐንስ አፈወርቅ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እያሉ ጥሩ ጥሩ የሚመስሉ አባባሎችን እየተጠቀሙ ተሀድሶአዊያንን ላለማስከፋት፣ ተቀባይነት ለማግኘት ኦርቶዶክሳዊያንን ማስደሰት ደግሞም እግዚአብሔርንም ላለመበደል በሚደረግ ፍልሚያ ውስጥ እንዳሉ የተረዱት አልመሰለኝም። 

ከእግዚአብሔር በላይ ይራራሉ ከሚባሉት ከሰው አልፈው ሰይጣንን ከሚያሞነኩስና ከእግዚአበሔር ጋር ሊያስታርቁ ከሚወዱት ጋር ኢየሱስን እንዴት ባለ መንገድ ሊሰብኩት እንደፈለጉ አልገባኝም። ሰው የጎረቤቱን ቤት ሰርቶ ነው እንዴ የራሱን የሚሰራው? ምናለ ብትተዋቸው? የተሀድሶ አገልግሎት በሁለት እግሮቹ እንዳይቆምና ያስተማረቻቸውን አቅፋ ረዥም ርቀት እንዳትጓዝ ካደረጉት አንዱ ምክንያት ሌላ ቤት ላይ ተታኮ የሚደረገው እንቅስቃሴ ነው። እስከ መቼ ነው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ጫንቃ ተላቆ ይህን አገልግሎት ለማስፋት አንድነት የማይፈጠው? 

እረ ስንቱን ልናገር በጌታ.......... በጣም ከገረመኝ ነገር አንዳንዶች በዚህ መንገድ ብዙ ዓመት ያስቆጠሩና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለረዥም ዓመት ተቀጥረው ያሉ ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነ የሚናገሩት ነገር። በዚህ መንገድ የሚከፈል ዋጋ እኔ ሊታየኝ አልቻለም ቅዱሱ መጽሐፍም ይህንን አካሄድ ሲደግፍም ሆነ ሲያበረታታ አላየሁም አልሰማሁም። ዋጋ አለን ካሉም እንደኔ እንደኔ ደሞዛቸውን ይቁጠሩ ደግሞስ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብቻ ለምን ታያቸው? ይህ አካሄድ ለምን መስጂድ አይሰራም? ጂሆቫ ጋርና ካቶሊክ ቤተ እምነት ውስጥስ ለምን አይሞክሩትም? 

ነገ የምናፍርበትንና የማያዋጣንን መንገድ ዛሬ አንጠቀም!

Monday, 20 September 2021

ብልጫ ያለው ሕይወት


ወርደህ አትዋረድ!!! 

የንስር ተፎጥሮ እጅግ የሚገርም ነው። ብዙ ነገሩ ለአማኝ ምሳሌ ሆኖ ሲነገር ይስተዋላል። ከብዙ በጥቂቱ ለመናገር ያህል ንስር ስፍራውን ጠባቂ ነው። ይህንንም ብርቱ ጽናቱን በሁለት ሁኔታዎች ብንመለከት 


1) ክረምት ሲቃረብ አብዛኛው አእዋፋት ከዝናቡ ሽሽት ወደ ሌላ ስፍራ ይሄዳሉ አንዳንዱም ብዙ ሀገራት እስከማቋረጥ ይደርሳሉ። ንስር ግን ክረምት አልፎ በጋ እንደሚመጣ ያውቃልና ቤቱን ሳይለቅ ስፍራም ሳይቀይር በትዕግስት ክረምቱን ያሳልፋል። 


2) የንስር ከፍተኛ ጠላቱ እንደሆነ የሚነገርለት እንስሳ እባብ ነው። እባብን ማጥቃት ወይም ራሱን መከላከል ሲፈልግ የሚጠቀመው ስልት ስፍራውን አያስለቅቀውም። ወደ ሰማይ በመውጣት እባቡን ትፈልጋለች እንዳየችውም ወደ ምድር በፍጥነት ተምዘግዝጋ በአፍና በእግር ጥፍሮቿ በመያዝ ወደ ሰማይ ትወስደዋለች መልሳ ወደ ምድር ትፈጠፍጠዋለች። ንስር ይህን የምታደርገው ሰማይ ስፍራዋ ስለሆነ ነው። ምድር ላይ ከእባብ ጋር ግብግብ አትገጥምም። ምክንያቱም ምድር ላይ ምቹ ለእባብ ነውና ትሸነፋለች ለንስር የመጫወቻ ሜዳዋ ደግሞ ሰማይ ነው። በእባብ ሜዳ ሳይሆን በራሷ ሜዳ ወስዳ ታሸንፋለች። ወርዳ አትገጥምም በማይመጥናት ስፍራ ውርርድ ውስጥ አትገባም። 


ልክ እንዲሁ አማኝ በማይመች አካሄድ አትጠመድ እንደሚል ቃሉ በማያሸንፍበት ሜዳ ለመጫወት መጣጣር አያስፈልገውም። ስፍራውን ጠብቆ መኖር ይኖርበታል። በኑሮ በውጣ ውረዱ ብዙ ተግዳሮት ይመጣልና ብልጫ ያለው ሕይወት ስለተሰጠን ወርደን አንዋረድ። ያለ ስፍራ መጠበቅ ከባለጋራችን ጋር መጋደልም ሆነ ራሳችንን መጠበቅ ወይም መቃወም አንችልም። የሚገጥሙን ፈተናዎች ስፍራችንን ሊያስለቅቁ የሚችሉበትን ምክንያት አለመፍቀድ ያስፈልገናል። 


የሕይወታችን ቤዛና አዳኝ ኢየሱስ የገጠሙትን ሁሉንም ፈተናዎች በጽናት ያለፈ ጀግናችን ነው። እኛም አንዳች ፈተና ሲመጣብን ኢየሱስን ለማሳየት ያገኘነው እድል አድርገን ልንጠቀምበት ይገባናል። በብዙ ጥላቻ ውስጥ መውደድን፣ በብዙ ክፉት ውስጥ ደግነትን፣ በብዙ በቀል ውስጥ ይቅርታን ልንኖረው የተጠራን ነንና የትኛውንም ተግዳሮት ስፍራ ለመልቀቅ ምክንያት አናድርግ። ማንኛውም ነገር በእኛ ህይወት ሲከሰት ከተሰጠን ሕይወት አንፃር እየመለስን ስንኖር ነው ብልጫ ያለው ሕይወት ኖርን የሚባለው። ካልድኑ ሰዎች ያነሰ ሕይወት አይደለም ልክ ወይም የተስተካከለ ሕይወት እንኳ ብንኖር ብልጫችን ምንድነው? አንዳንድ ሰዎች ለንትርክና ለግጭት እድል እየሰጡ ሜዳቸው ውስጥ የጥል ኳስ እንድንመታ ይጋብዙናል ታዲያ በስፍራችን ወይስ በነሱ ስፍራ ሆነን ነው ኳሷን መምታት ያለብን? 


መልሱን ከፈለግን ጌታ ያደረገውን መመልከት ይበጃል። እርሱ ለገጠመው ተግዳሮቶች ፈታኞቹ በሚፈልጉት መንገድ የሆነ ምላሽ ፍፁም አልሰጠም። ተመጣጣኝ ምላሽ እንኳ እርሱ ጋር አልነበረም። '' ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ '' ( 1ኛ ጴጥ 2፥23) ብልጫ ያለው ሕይወት ከኢየሱስ እንማር። 


ይህ ሕይወት ከንግግር ባለፈ በመሆን የምናሳየው ውድ ሕይወት ነው። ክርስትና ደግሞ ንግግር ብቻ ሳይሆን ተግባርም ነው። ደግሞስ ተግባር ከንግግር ይበልጣል ይባል የለ። ምናልባትም ኢየሱስን በመስበክ የኖርን መስሎን እንዳይሰማን! ስንኖረው ነው የስብከታችን ጉልበትና አቅም የሚታየው። ስብከቶች ከጎግል ወይም ከዩቲዩብ ይገኛሉ ኑሮ ግን በተግባር ብቻ ነው የሚታየው። ስለዚህ ኢየሱስን በጣም ስለሰበክነው ሳይሆን ስንኖረው ነው አገልግሎታችን ጉልበት የሚኖረው። ፍቅር የሆነውን ኢየሱስ እየሰበክ ፍቅር አልባ፣ መዳን የሆነልንን የእርሱን ትዕግስት እየሰበክን ትዕግስት አልባ  ይቅር ባዩን እያወራን በይቅርታ የማናምን ግብዞች አንሁን።


የአማኝ ምልልስ ምላስ ላይ ያለ ሳይሆን እግር ላይ የሚመጣ ብርቱ የሕይወት ሰልፍ ነው። ይህ የምልልስ ሕይወት ደግሞ የተያያዘው ከጌታና ከጌታ ጋር ብቻ ነው። የሆነውን ለመሆን፣ ያደገውን ለማድረግ ያሳለፈውን ለማሳለፍ በመከራ/በፈተና ውስጥ ልናልፍ  ተጠርተናል። በዝናብ እየሄድን ውሃ አይንካኝ አይባልም። እየጠሉን ልንወድ፣ እየጎዱን ልንጠቅም፣ እየሰደቡን ልንመርቅ፣ ሲመቱን ላንመታ፣ ሲያዋርዱን ልናከብር፣ ሲዋሹብን (ያላደረግነውን አደረጉ ቢሉ) በጽድቅ ለሚፈርደው ጌታ አሳልፈን በመስጠት ከብደን ብልጫ ባለው ሕይወት እንድንጨርስ ኢየሱስ የኖረውን ሕይወት እንመልከት። ለወጉን ፍቅርን ለሰደቡን ምህረትን እንድንኖረው የጌታ ጸጋ ይርዳን። 


ኢየሱስ የህይወታችን እና የፀበያችን ደግሞም የባህሪያችን መለኪያ ነው። በሰፈሩት ቁና ይሰፈራሉና በኢየሱስ መስፈሪያ መሰፈር ይሁንልን።

Saturday, 29 May 2021

በፍጹም ልብህ

 

አንዳንድ ጊዜ ብዙ ከመጠንቀቅ እና ሕይወታችንን በማስተዋል ከመምራታችን የተነሳ ስኬታማ ወይም ውጤታማ ኑሮ እንዳለን የምንቆጥር ልንኖር እንችላለን። በእርግጥ መጠንቀቅም ሆነ ማስተዋል አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። '' ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል '' (ምሳሌ 2፥11) እንደሚል መፅሐፍ። ነገር ግን ለደረስንበት ደረጃ ራሳችንን ድጋፍ የምናደርግ ከሆነ ተሳስተናል። 

እኔ እንደገባኝ በራስ መደገፍን የሚያክል አደገኛና ከንቱ ነገር ያለ አይመስለኝም። የቱንም ያህል ብዙ ነገሮችን ያወቅንና አስተዋዮች ብንመስልም የእኛ ማስተዋል ለመደገፍ የሚያበቃ አይደለም። የእኛ ማስተዋል ከሸንበቆነት አይበልጥም ቆመናል ስንል ወድቀን እንገኛለን። 

እስኪ ስንቶቻችን ነን ገና ያልተፈጠን ነገር ሊፈጠር ይችላል ብለን ፍርሃት በፈጠረው በገዛ ፈቃዳችን ተመስርተን ነገሮችን እንዳይሆኑ ያደረግን/የተከላከልን የሚመስለን? ለራሳችን ልክ የሆንባቸው ጉዳዮች ላይ ሰው አለማሳዘናችን እርግጠኞች ነን ወይ? ደግሞም ማስተዋል አለኝ ተብሎ ክርስቲያን ብልጣብልጥ እንዲሆን ተፈቅዶለታል ወይ? ራሳችንን እንጠይቅ

እውነት እውነት እላችኃለው የእኛ ማስተዋል ከእግዚአብሔር ሞኝነት አይበልጥም። '' ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። '' (1ኛ ቆሮ 1፥25)

እኛ ችሎታችንና አቅማችን እጅግ ውሱን ስለሆነ ያለ እግዚአብሔር እርዳታ በማስተዋልና በጥንቃቄ እንኳ ቢሆን አንዳች ልናደርግ አንችልምና ለደረስንበት ማንኛውም ደረጃ ክብሩን ለእርሱ እንስጥ። እግዚአብሔር አደረገልን ማለትን እናብዛ በማንኛውም ሰበብ ክብሩን ለሌላ አንስጥ። 

እንዴት እንደሚሠራና ነገሮችን እንደሚያቀናጅ ዝርዝሩንና ስሌቱን ወይም ቀመሩን አናውቅምና ለአሠራሩ ፍፁም እንድንመች ፍፁም እንመነው ፍፁም ይሰራብናል።

ሁሉን ቻይነቱና ሀሳቡም ይከለከል ዘንድ በማይቻል በእርሱ እንደገፍ ባይዋጥልንም የራሳችንን አካሄድ ትተን ፍለጋውን እንከተል! እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና '' የነፋስ መንገድ እንዴት እንደ ሆነች፣አጥንትም በእርጉዝ ሆድ እንዴት እንድትዋደድ እንደማታውቅ፣ እንዲሁም ሁሉን የሚሠራውን ሥራ አታውቅም '' (መክብብ 11፡4-5) 

በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ፤ ይህም ለሥጋህ ፈውስ ይሆንልሃል፥ ለአጥንትህም ጠገን። እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር፥ ከፍሬህም ሁሉ በኵራት፤ (ምሳ 3፥5-9)

ቸር እንሰንብት !

Tuesday, 4 May 2021

የእኛ ዶሮስ?

መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ሁሉም ነገሮች ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ይጠቅመን ዘንድ ተፅፎልናል የቅዱሳን የሕይወት ታሪክ ጭምር (2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3: 16-17)። ነገር ግን ቃሉ ሊነግረን በፈለገው መጠን አንረዳውም። በሕይወት እስካላዋሃድነው ድረስ የቃሉ ጉልበት አይታወቀንም። አንዳንዴ ከታሪክ ባልዘለለ መልኩ እናየዋለን። በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተፃፈው ሁሉ በዓላማና እኛም ልንማርበት ታቅዶ ነው። በዘፈቀደ ያለ ምንም ቃል የለም። 

የጴጥሮስን ዶሮ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው በፋሲካ ሰሞን ነው ነገር ግን ዛሬም በየአንዳንዱ ዛሬ ዶሮ ይጮሃል። ብዙዎቻችን በጴጥሮስ ላይ ብቻ የጮኧች አርገን እናስባለን። ዶሮዋ ጴጥሮስ ላይ  መጮዋ እኛ ሕይወት ላይ ምን ፋይዳ አመጣ ብለን ካልጠየቅን ስለምን ለትምህርት ተፃፈ ማለት እንችላለን? 

እርግጥ ነው ጴጥሮስ በጊዜው በራሱ ተማምኖ ሌሎች ቢሸሹ እንኳ እኔ ግን አልተውህም ብሎ ቢናገርም ያች ዶሮ እንዳትጮው ማድረግ አልቻለው። ዶሮዋ እስክትጮው ድረስ ጴጥሮስ በራስ ተማምኖ ነበር። አንዴ ካዴ ደግሞም ሁለቴ ያን እንኳ ከነበረበት የራስ መተማመን ሊባንን አልቻለም የሶስተኝው ግን የጌታ ቃል ነውና በእርግጥ ባነነ። ዛሬስ እኛ ከዚህ የምንማረው ምንድነው? 

ያች ዶሮ ጴጥሮስን ወደ ንስሀ አስገሰገሰችው እናም ወዲያው በመፀፀቱና በማንባቱ በደሉ ይቅር ተባለችለት። እኛ ስንት ዓመት በየማለዳው ዶሮ ሲጮው ከነበርንበት በደልና እግዚአብሔር እንደቃሉ አለመታዘዝ ቀስቅሶን ይሆን? ይህን የራሳችን ጉድ የምናውቀው ራሳችን ነን። ስንት ዓመት የዶሮዋን ጪወት ለጴጥሮስ ብቻ አርገን አሰበነው? ዛሬም በበደል ላለ ሰው የዶሮ ጩወት ለጴጥሮስ እንደጮኧችው አይደለምን? ጪወቷን ስንሰማ ለንስሀ ማንቂያ ወይስ ከእንቅልፍ ማንቂያ? 

መስማት ይሁንልን። በራሳችን ወይም በዚህ ዓለም ማስተዋል ሳይሆን በእግዚአብሔር ማስተዋል  እንመላለስ ዘንድ የእርሱ መሉም ፈቃድ ይሁን። አሜን

Monday, 11 January 2021

እንዲያው በጸጋው

 


ብዙ ጊዜ ሰዎች እንዲሁ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንደሚቻል መቀበል ይከብዳቸዋል። እንደው ምንም ሳላደርግ (ስራ ሳልሰራ) የተራበን ሳልመግብ፣ የተጠማን ሳላጠጣ፣ የተራቆተን ሳላለብስ፣ የታመመን ሳላስታምም፣ የተቸገረን ሳልረዳ፣ አስራት ሳላወጣ .....ወዘተ


በመሰረቱ እነዚህን እናድርጋቸው እንኳ ብንል እመኑኝ የተረፈንን ካለ ነው። እናልብስ ብንል የጠበበን ልብስና ጫማ፣ እናብላ ብንል ምግብ ቤት ያስተረፍነውን ቴክአዌይ አስደርገን ነው። እንኳን ተርፎን ከጉድለታችን ብናደርገው እንኳ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ሳይሆን በመቀበል ነው የሚገኘው። የተሰጠንን ብናስተውል የምንሰጠው ባወቅን። የማያልፍ ሕይወት ለመቀበል ዘላለማዊ ስራ ያስፈልጋል። 


ጌታ ኢየሱስ መናን ከሰማይ አውርዶ ከመገበ በኃላ እንኳ እነዛ ሰዎች ዳግም ተርበዋል እርሱን ግን ያመኑ ዘላለም ጠግብዋል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰጠን ራሱን ነው እርሱ ደግሞ በማያልፍ የሕይወት ኃይል የሚኖር መጀመሪያ የሌለው አልፋ መደምደሚያ የሌለው ኦሜጋ ነው። 


ታዲያ ጌታ ኢየሱስ እንዲሁ ወዶን ራሱን እንዲሁ ከሰጠን ሰዎች ይህንን የዘላለም ሕይወት እንዲሁ መቀበል እንዴት ይከብዳቸዋል። ''እንዲሁ'' የሚለው ቃል እኮ እንደቃሉ የሚቀል አይደለም። ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት ነው ''እንዲሁ'' የመጣው። እግዚአብሔር ከዚህ የበለጠ ሊሰጥ የማይችለውን ትልቁን አንድያ ልጁን ነው የሰጠን። 


'' እንዲሁ'' አይቅለልባችሁ በ''እንዲሁ'' ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ የቤዛነት ታላቅ መከራና ሞት የተከፈለበት ዋጋ አለ። ''እንዲሁ'' ማለት እንዴት ያለ ታላቅና የከበረ ዋጋ መሰላችሁ። በእውነት የጌታ ኢየሱስ የማዳኑ ስራ ካወቅነው በላይ ነው።