ብዙ ጊዜ ሰዎች እንዲሁ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንደሚቻል መቀበል ይከብዳቸዋል። እንደው ምንም ሳላደርግ (ስራ ሳልሰራ) የተራበን ሳልመግብ፣ የተጠማን ሳላጠጣ፣ የተራቆተን ሳላለብስ፣ የታመመን ሳላስታምም፣ የተቸገረን ሳልረዳ፣ አስራት ሳላወጣ .....ወዘተ
በመሰረቱ እነዚህን እናድርጋቸው እንኳ ብንል እመኑኝ የተረፈንን ካለ ነው። እናልብስ ብንል የጠበበን ልብስና ጫማ፣ እናብላ ብንል ምግብ ቤት ያስተረፍነውን ቴክአዌይ አስደርገን ነው። እንኳን ተርፎን ከጉድለታችን ብናደርገው እንኳ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ሳይሆን በመቀበል ነው የሚገኘው። የተሰጠንን ብናስተውል የምንሰጠው ባወቅን። የማያልፍ ሕይወት ለመቀበል ዘላለማዊ ስራ ያስፈልጋል።
ጌታ ኢየሱስ መናን ከሰማይ አውርዶ ከመገበ በኃላ እንኳ እነዛ ሰዎች ዳግም ተርበዋል እርሱን ግን ያመኑ ዘላለም ጠግብዋል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰጠን ራሱን ነው እርሱ ደግሞ በማያልፍ የሕይወት ኃይል የሚኖር መጀመሪያ የሌለው አልፋ መደምደሚያ የሌለው ኦሜጋ ነው።
ታዲያ ጌታ ኢየሱስ እንዲሁ ወዶን ራሱን እንዲሁ ከሰጠን ሰዎች ይህንን የዘላለም ሕይወት እንዲሁ መቀበል እንዴት ይከብዳቸዋል። ''እንዲሁ'' የሚለው ቃል እኮ እንደቃሉ የሚቀል አይደለም። ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት ነው ''እንዲሁ'' የመጣው። እግዚአብሔር ከዚህ የበለጠ ሊሰጥ የማይችለውን ትልቁን አንድያ ልጁን ነው የሰጠን።
'' እንዲሁ'' አይቅለልባችሁ በ''እንዲሁ'' ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ የቤዛነት ታላቅ መከራና ሞት የተከፈለበት ዋጋ አለ። ''እንዲሁ'' ማለት እንዴት ያለ ታላቅና የከበረ ዋጋ መሰላችሁ። በእውነት የጌታ ኢየሱስ የማዳኑ ስራ ካወቅነው በላይ ነው።
No comments:
Post a Comment