Monday, 20 September 2021

ብልጫ ያለው ሕይወት


ወርደህ አትዋረድ!!! 

የንስር ተፎጥሮ እጅግ የሚገርም ነው። ብዙ ነገሩ ለአማኝ ምሳሌ ሆኖ ሲነገር ይስተዋላል። ከብዙ በጥቂቱ ለመናገር ያህል ንስር ስፍራውን ጠባቂ ነው። ይህንንም ብርቱ ጽናቱን በሁለት ሁኔታዎች ብንመለከት 


1) ክረምት ሲቃረብ አብዛኛው አእዋፋት ከዝናቡ ሽሽት ወደ ሌላ ስፍራ ይሄዳሉ አንዳንዱም ብዙ ሀገራት እስከማቋረጥ ይደርሳሉ። ንስር ግን ክረምት አልፎ በጋ እንደሚመጣ ያውቃልና ቤቱን ሳይለቅ ስፍራም ሳይቀይር በትዕግስት ክረምቱን ያሳልፋል። 


2) የንስር ከፍተኛ ጠላቱ እንደሆነ የሚነገርለት እንስሳ እባብ ነው። እባብን ማጥቃት ወይም ራሱን መከላከል ሲፈልግ የሚጠቀመው ስልት ስፍራውን አያስለቅቀውም። ወደ ሰማይ በመውጣት እባቡን ትፈልጋለች እንዳየችውም ወደ ምድር በፍጥነት ተምዘግዝጋ በአፍና በእግር ጥፍሮቿ በመያዝ ወደ ሰማይ ትወስደዋለች መልሳ ወደ ምድር ትፈጠፍጠዋለች። ንስር ይህን የምታደርገው ሰማይ ስፍራዋ ስለሆነ ነው። ምድር ላይ ከእባብ ጋር ግብግብ አትገጥምም። ምክንያቱም ምድር ላይ ምቹ ለእባብ ነውና ትሸነፋለች ለንስር የመጫወቻ ሜዳዋ ደግሞ ሰማይ ነው። በእባብ ሜዳ ሳይሆን በራሷ ሜዳ ወስዳ ታሸንፋለች። ወርዳ አትገጥምም በማይመጥናት ስፍራ ውርርድ ውስጥ አትገባም። 


ልክ እንዲሁ አማኝ በማይመች አካሄድ አትጠመድ እንደሚል ቃሉ በማያሸንፍበት ሜዳ ለመጫወት መጣጣር አያስፈልገውም። ስፍራውን ጠብቆ መኖር ይኖርበታል። በኑሮ በውጣ ውረዱ ብዙ ተግዳሮት ይመጣልና ብልጫ ያለው ሕይወት ስለተሰጠን ወርደን አንዋረድ። ያለ ስፍራ መጠበቅ ከባለጋራችን ጋር መጋደልም ሆነ ራሳችንን መጠበቅ ወይም መቃወም አንችልም። የሚገጥሙን ፈተናዎች ስፍራችንን ሊያስለቅቁ የሚችሉበትን ምክንያት አለመፍቀድ ያስፈልገናል። 


የሕይወታችን ቤዛና አዳኝ ኢየሱስ የገጠሙትን ሁሉንም ፈተናዎች በጽናት ያለፈ ጀግናችን ነው። እኛም አንዳች ፈተና ሲመጣብን ኢየሱስን ለማሳየት ያገኘነው እድል አድርገን ልንጠቀምበት ይገባናል። በብዙ ጥላቻ ውስጥ መውደድን፣ በብዙ ክፉት ውስጥ ደግነትን፣ በብዙ በቀል ውስጥ ይቅርታን ልንኖረው የተጠራን ነንና የትኛውንም ተግዳሮት ስፍራ ለመልቀቅ ምክንያት አናድርግ። ማንኛውም ነገር በእኛ ህይወት ሲከሰት ከተሰጠን ሕይወት አንፃር እየመለስን ስንኖር ነው ብልጫ ያለው ሕይወት ኖርን የሚባለው። ካልድኑ ሰዎች ያነሰ ሕይወት አይደለም ልክ ወይም የተስተካከለ ሕይወት እንኳ ብንኖር ብልጫችን ምንድነው? አንዳንድ ሰዎች ለንትርክና ለግጭት እድል እየሰጡ ሜዳቸው ውስጥ የጥል ኳስ እንድንመታ ይጋብዙናል ታዲያ በስፍራችን ወይስ በነሱ ስፍራ ሆነን ነው ኳሷን መምታት ያለብን? 


መልሱን ከፈለግን ጌታ ያደረገውን መመልከት ይበጃል። እርሱ ለገጠመው ተግዳሮቶች ፈታኞቹ በሚፈልጉት መንገድ የሆነ ምላሽ ፍፁም አልሰጠም። ተመጣጣኝ ምላሽ እንኳ እርሱ ጋር አልነበረም። '' ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ '' ( 1ኛ ጴጥ 2፥23) ብልጫ ያለው ሕይወት ከኢየሱስ እንማር። 


ይህ ሕይወት ከንግግር ባለፈ በመሆን የምናሳየው ውድ ሕይወት ነው። ክርስትና ደግሞ ንግግር ብቻ ሳይሆን ተግባርም ነው። ደግሞስ ተግባር ከንግግር ይበልጣል ይባል የለ። ምናልባትም ኢየሱስን በመስበክ የኖርን መስሎን እንዳይሰማን! ስንኖረው ነው የስብከታችን ጉልበትና አቅም የሚታየው። ስብከቶች ከጎግል ወይም ከዩቲዩብ ይገኛሉ ኑሮ ግን በተግባር ብቻ ነው የሚታየው። ስለዚህ ኢየሱስን በጣም ስለሰበክነው ሳይሆን ስንኖረው ነው አገልግሎታችን ጉልበት የሚኖረው። ፍቅር የሆነውን ኢየሱስ እየሰበክ ፍቅር አልባ፣ መዳን የሆነልንን የእርሱን ትዕግስት እየሰበክን ትዕግስት አልባ  ይቅር ባዩን እያወራን በይቅርታ የማናምን ግብዞች አንሁን።


የአማኝ ምልልስ ምላስ ላይ ያለ ሳይሆን እግር ላይ የሚመጣ ብርቱ የሕይወት ሰልፍ ነው። ይህ የምልልስ ሕይወት ደግሞ የተያያዘው ከጌታና ከጌታ ጋር ብቻ ነው። የሆነውን ለመሆን፣ ያደገውን ለማድረግ ያሳለፈውን ለማሳለፍ በመከራ/በፈተና ውስጥ ልናልፍ  ተጠርተናል። በዝናብ እየሄድን ውሃ አይንካኝ አይባልም። እየጠሉን ልንወድ፣ እየጎዱን ልንጠቅም፣ እየሰደቡን ልንመርቅ፣ ሲመቱን ላንመታ፣ ሲያዋርዱን ልናከብር፣ ሲዋሹብን (ያላደረግነውን አደረጉ ቢሉ) በጽድቅ ለሚፈርደው ጌታ አሳልፈን በመስጠት ከብደን ብልጫ ባለው ሕይወት እንድንጨርስ ኢየሱስ የኖረውን ሕይወት እንመልከት። ለወጉን ፍቅርን ለሰደቡን ምህረትን እንድንኖረው የጌታ ጸጋ ይርዳን። 


ኢየሱስ የህይወታችን እና የፀበያችን ደግሞም የባህሪያችን መለኪያ ነው። በሰፈሩት ቁና ይሰፈራሉና በኢየሱስ መስፈሪያ መሰፈር ይሁንልን።

No comments:

Post a Comment