Wednesday, 16 March 2022

በእርግጥ ይቆምልኛል!!!



የክርስትና ብቸኛ ዋስትና ጌታ ኢየሱስ ነው። ከእርሱ ውጪ የተቀበልከው ሕይወት እንደሌለ ሁሉ ከሰጠህም ስፍራ የሚያወርድህ ሰው የለም። ሰዎች በራሳቸው ሚዛን ተምነው ከፍ ዝቅ ሊያደርጉህ ይችሉ ይሆናል ነገር ግን ማንም አንተን ያልሰጠህን ሕይወት አይነጥቅህም። ክርስትናህ ላይ መከራ ወይም ፈተና ያበዙብህ ይሆናል ተጋፍተውህ ግን ሊነጥቅህ የሚችል ሰው የለም። 

ሰዎች በመልካሙ ጊዜ አብረውህ ከነበሩ በተግዳሮትህ ጊዜ ስታጣቸው አይግረምህ። እኛ ሰዎች ደካሞች ነን ይልቅ የማይረሳህን ጌታ ብቻ ተስፋ አድርግ ማንም በሌለህ ጊዜ ከጎንህ ሊቆምልህ የሚችለው እርሱ ብቻ ነው። 

ጳውሎስን የገጠመውን መመልከት በብዙ ያጽናናል። በተከሰሰበት ችሎት ከእርሱ ወገን የሚሆን አንድ ሰው ባለማየቱ ያዘነ ቢሆንም ከሁሉ የሚበልጠው ከእርሱ ጋር በመሆኑ እንደበረታ ይናገራል። 

በፊተኛው ሙግቴ አንድ ስንኳ አልደረሰልኝም፥ ሁሉም ተዉኝ እንጂ፤ ይህንም አይቍጠርባቸው፤ ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ፥ ከአንበሳ አፍም ዳንሁ። ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። (2ኛ ጢሞ 4፥16-18) 

አሁን በብዙ መጨነቅ ውስጥ ሆናችሁ ወገን እንደሌላችሁ ለሚሰማችሁ ጌታ በተጨነቃችሁበት ነገር ከጎናችሁ ይቁምላችሁ። ፍፁም የሆነ መበርታት ያግኛችሁ። ሊውጣችሁ ካለ ክፉ አፍም ያድናችሁ። 

ጌታ ከጎኔ ይቆምልኛል በእርሱ መቆም እበረታለው የሚል እምነት ለሁላችን ይጨምርልን። በማንችለውና ከአቅማችን በላይ በሆነው ነገር ብቻ ሳይሆን አቅም ባገኘንበትም ማከናወን እንደምንችል በምናስበውም ጉዳይ ላይም ከጎናችን ይቁም።

No comments:

Post a Comment