ወ/ሮ ለጥፌ ከእድር እንደተመለሱ ግቢያቸው ውስጥ የዘረጉት የልብስ ማስጫ ገመድ ላይ ጎረቤታቸው እትዬ ልክነሽ ያጠቡትን የልጆቻቸውን ልብሶች አስጥተውበት ያገኛሉ። ለመጣላት ሰበብ ይፈልጉ ስለነበር ጮክ ባለ ድምፅ እየተሳደቡ ከዚች ሴትዮ ጋር ጎረቤት የሆኑበትን ቀን እየረገሙ ባለ በሌለ ኃይላቸው የሴትዮዋን በር ያንኳኳሉ። በር ይከፈትና አቤት ሲባሉ የስድብ መአትና ርግማን በሩን ለከፈተችው በእትዬ ልክነሽ ልጅ ላይ ያወርዱባታል። ልጅቱ በተረጋጋ መንፈስ ስለሰማቻቸው የተናደዱት ወ/ሮ ለጥፌ እናቷን እንድትጠራ ሲጠይቁ እንደሌሉና ቤተክርስቲያን እንደሄዱ ስትነግራቸው የስድብና የእርግማን ጥማታቸው ከትዕግስታቸው በላይ ስለሆነባቸውና እትዬ ልክነሽ እስኪመለሱ የመጠበቅ አቅም ስላልነበራቸው እዛው ቤተክርስቲያን ድረስ በመሄድ ለመሳደብ ይወስኑና ነጠላዬን አቀብሉኝ አሉ።
የተሀድሶን የወንጌል አገልግሎት ለመሳደብና በሕይወታቸው ለደረሰባቸው ኪሳራ ቤተክርስቲያንን ተወቃሽ ለማድረግ ቀን ከሌሊት በሰበብ ባስባቡ ስድብና የጥላቻ ንግግር በመናገርና በመፃፍ እየተጉ ያሉ ሰዎችን ስመለከት ከላይ የነገርኳቹ ታሪክ ትዝ አለኝ። ለምን እንደሆነ ባላውቅም ብቻ ትዝ አለኝ። አንዳች ትችት ቤተክርስቲያን ላይ ለመወርወር ሁሌ ዝግጁ ሆኖ በተጠንቀቅ መኖር እንዴት ይቻላል?
አወኩሽ ናቅሁሽ ነገር ለምን? አንድ የሰፈራችን ልጅ እንግሊዝኛ ማንም አይችለኝም እያለ ሲያቅራራ ''ከመሬት ተነስታ ልክ ልኬን ነገረችን'' ን በእንግሊዝኛ ተርጉም ሲባል ''Stand from the earth talking equal equal '' ብሎ አስቆናል። ከእኔ ወዲያ ላሳር ዓይነት አስተሳሰብ ለማንም እንደማይጠቅም እሙን ነው። በሆነው ባልሆነው ነገር እየተነሱ መዘርጠጥ አግባብ ነው ብዬ አላስብም። የክርስትና ሕይወት ከራስ ባለፈ ለሰዎችም መኖር ይጠይቃልና ሌላው ሁሉ ቢቀር ለመንጋው ማሰብ ተገቢ አይደለምን? በግል ባጋጠማችሁ ችግር ቤተክርስቲያንን ተወቃሽ ለማድረግ ነገር ከመሬት እየፈነቀላችሁ የስድብና የጥላቻ ድንጋይ ለምትወራወሩ ሰዎች እየሄዳችሁ ያላችሁበት መንገድ አይበጃችሁምና አቁሙ። እንደ ወይዘሮዋ ለነገር ነጠላዬን አቀብሉኝ አትበሉ።
ያዋጣናል በምትሉት መንገድ የመሄድ ሰማያዊም ምድራዊም መብታችሁ የተጠበቀ ነው። ነገር ግን ከተሀድሶአዊት ቤተክርስቲያን ራስ ውረዱ። እንዳንመክራችሁ የምትመከሩ ሰዎች ልትሆኑ አልቻላችሁም። ልክ አለመሆናችሁን ቃል ጠቅሰን እንዳናወራ ብዙ ማጣቀሻ የማዋጣት አቅም አላችሁ። አካሄዳችሁ ከእግዚአብሔር ሀሳብና ፈቃድ ውጪ እንደሆነ እያወቃችሁ ከእግዚአብሔር ጋር አትጣሉ የመድቀቅ አላማ ከሌላችሁ።
No comments:
Post a Comment