Wednesday, 16 March 2022

በአገለግሎት ሰበብ የግል ፍላጎት ለምትከተሉ ሁሉ

 

በተለይ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ አገልግሎት ደሞዝተኛና ጥቅም ሱስ ለሆነባችሁ 

በመጽሐፈ መሳፍንት ከተመዘገቡ አስነዋሪ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ አንዱ በዘመኑ የነበረውን ሃይማኖታዊና የሥነ ምግባራዊ ጉድለት የሚያንጸባርቅ ክስተቶችን በግልፅ በመከሰቱ ነው። ይህ ታሪካዊ ስህተት የሰው ልጅ ልብ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር እስካልሆነ ድረስ ሊፈጠር እንደሚችል ግልፅ የሆነ ማሳያ ነው።

በዚያ ዘመን የሕዝብ መሪ ባልነበረበት ጊዜ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን (በራሱ ብልሀት የፈጠረውን መሳ. 21፥25) ያደርግ ነበር። ይሄ ደግሞ ሕዝብ ቀጪና ተው ባይ እንደሌለው ሲያውቅ ነውርና ኃጢአት እንዲፈፅም ድፍረት ይሆነዋል። 

ሕግ አስፈጻሚ አካል አለመኖር ለሕገወጥነት መከሰትና መስፋፋት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ሕግና ሕግ አስፈፃሚዎች መኖራቸው የሰው ገደብ የለሽ ነውረኛነትና መረን መውጣት በተወሰነ ቁጥጥር ሥር እንዲሆንና እንዲገደብ ያደርጋሉ። ይህ ለየትኛውም ዘመን መርህ አድርገን እንወስደዋለን። 

ይህ የምነግራችሁ ታሪክ በዘመነ መሳፍንት የነበረውን አጠቃላይ የሥነ ምግባር መመሪያ መጥፋቱን ያሳያል። እንደሚታወቀው እግዚአብሔር ለሌዊ ወገን ቃሉን እንዲያውቁና ሌሎችን ማስተማር እንደሚገባቸው በልዩ ትኩረት ተናግሯል። ከአስራ ሁለቱ ነገደ እስራኤላውያን ሁሉ የበላይ ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝ እንዲኖሩ የሚጠበቅባቸው እነዚህ ሌዋውያን ነበሩ። ነገር ግን ስለ አይሁድ ሃይማኖት መበላሸት ከታሪኩ መረዳት እንችላለን። 

ሌዋዊያን ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ከሚያወጡት አስራት ኑሮአቸውን መምራት ነበረባቸው ነገር ይህ በሙሴ በኩል የተጀመረው የአይሁድ ስርአት በመበላሸቱ የተነሳ አንድ ሌዋዊው ሥራ ፍለጋ ወደ ሰሜን ይጓዝና ወደ ሚካ ቤት መምጣቱን መጽሐፉ ይናገራል። ሚካም እናቱ አስቀርፃ ላሰራችው ጣዖት ካህን ሆኖ እንዲያገለግል ቤቱንም የአምልኮ ስፍራ ለማድረግ ፈልጎ ስለነበር ለእውነተኛው የእግዚአብሔር አምልኮ በኃላፊነት ማገልገል የነበረበትን ይህን ሌዋዊ ካህን ከእኔ ዘንድ ተቀመጥ፥ አባትና ካህንም ሁነኝ፤ እኔም ልብሶችንና ምግብህን፥ በእየዓመቱም አሥር ብር እሰጥሃለሁ፡ አለው። ሌዋዊውም ገባ። (መሳ 17፥10) 

ይህ ሌዋዊ ስለ ግል ሕይወቱ እንጂ ለእግዚአብሔር ስለሚደረግ አምልኮ ግድ ስላልነበረው የተሳሳተውን አምልኮ ለመምራት ፈቃደኛ ሆነለትና በሚካ ቤት ገባ። እውነተኛ ለእግዚአብሔር ብቻ ይገባው የነበረውን አምልኮ ትቶ ገንዘብን ፍለጋ ብቻ ወደ ጣኦት አምልኮ አገልግሎት በፍቃዱ ሊገባ ችሏል። ልብ ማለት ያለብን ሚካ እንደ አይሁድ ልማድና ለካህን ባላቸው ስፍራ መጠን ሌዋዊውን ለጣኦት አገልግሎት እንደጠየቀ ነው። ካህኑ ግን ፍፁም አገልግሎቱን ወደሚያረክስ እሱም ወደሚያምፅበት መንገድ እንደገባ ማስተዋል አለብን። ይህ ሌዋዊ ያደረገው በእስራኤል ታሪክ ትልቁ ውድቀት ተብለው ከሚነሱት ውስጥ አንዱ ነው። ለግል ፍላጎቱና ምቾቱ ሲል ክህነቱን የሸጠ ሰው እንደሆነ ከድርጊቱ መረዳት እንችላለን። 

በአዲስ ኪዳን የክህነት አገልግሎት የተሰጠው ለአማኞች በሙሉ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በተለየ መንገድ ከሌላ ሕዝብ በልዩነት የተሰጠ የክህነት አገልግሎት በአዲስ ኪዳን ዘመን የለም። በአይሁድና በግሪክ ሰው፣ በወንድና በሴት ልጆች መካከል ልዩነት የለም።

እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ (1 ጴጥ 2፥9)

ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን። (ራዕ 1፥5-6) 

የክህነት አገልግሎት ለአማኞች በሙሉ የተሰጠ ስለመሆኑ በትንሹ ከላይ በተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መረዳት እንችላለን። ነገር ግን ራሳቸውን የተለየ አገልጋይ አድርገው በተለያዩ የእምነት ተቋም ውስጥ ድብቅ ተልእኮ (underground mission) አለን ብለው ሰበብ በመፍጠር ለግል ፍላጎት መሸፈኛ አድርገው ወንጌልን በብዙ መንገድ የሚሸቃቅጡ ብዙ ሰዎች አሉ። (በተለይ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ) ቢነገራቸውም ከአፋቸው ውጪ የማይሰሙ የሌላውን አገልግሎት የሚያጥላሉና ለአማኞች እንቅፋት የሆኑ እውነትን በጓዳ ደብቀው በውሸት የተሞላ የሳሎን አገልግሎት ውስጥ ያሉ የዘመኑ አንዳንድ አገልጋዮች ንጹውን ወንጌል ከአሮጊቶች ተረት ጋር የሚቀላቅሉና የሚሸቃቅጡትን ሳስብ ከላይ የነገርኳችሁ ታሪክ ነው ትዝ ያለኝ። እነዚህን ሰዎች ከዛ ሌዋዊ ካህን ለይቼ የማይበት ዐይን የለኝም። 

ካህናት የተባልንበትን የተለየንበትን ቅዱስ አገልግሎት ለግል ፍላጎትና ምቾት ለደሞዝና ለጥቅማ ጥቅም ሲባል የክርስቶስ ኢየሱስ መካከለኝነትና አማላጅነት የሚሻርበት፣ ያለ ክቡር ደሙ ኃጢአት ሊስተሰረይ እንደሚቻል ወደሚነገርበት፣ ኢየሱስ ብቸኛ መድኃኒትና አዳኝ (መዳን በሌላ በማንም የለም) ብሎ መናገር ምንፍቅና ተብሎ ወደሚያስፈርጅበት፣ በሕይወት ወደሌሉ ሰዎች ልመናና ፀሎት ወደሚደረግበት፣ ለእግዚአብሔር ብቻ ይደረግ የሚገባውን የአምልኮ ስርአት ከፍጡራን ጋር በመቀላቀል ወደሚፈፀምበት፣ አገልግሎት ውስጥ የገቡ ብዙ ሰዎች አሉ። 

በግል ሕይወታቸው ይቸገሩ ይሆናል። ሁሉ ነገር ወድ በሆነበት ዘመን ኑሮአቸውን ያከበደ ብዙ ጉዳዮች ይኖሩ ይሆናል። አንዳንዶችም ያልጎደለባቸው ነገር ግን ምኞት ያሰከራቸውም አይጠፉም። ይህ አገልግሎት ግን በምንም የሚነካ ከየትኛውም ችግሮች መውጫ መንገድ ተደርጎ እንደ አማራጭ የሚቀርብ የስራ መስክ መሆን የለበትም። ቅዱስ አገልግሎት ነው ብለን ካሰብን ቅድስናውን ጠብቀን መሆን አለበት። በእኛ የማሰቢያ ሚዛን መልካም የመሰለን ሁሉ መልካም አይደለም። የአገልግሎታችን መስፈሪያና መለኪያ ቱንቢው ቃሉ እንጂ የእኛ የአመዛዛኝነት እውቀትና ችሎታ አይደለም። 

ስለዚህ የቱንም ያህል የግል ችግር ውስጥ ብንሆን የሚያጽናና የሚያበረታ ቃል ያለን ሰዎች ነንና በዚህ ደስ ይበለን። የሚሸጥም ሆነ የሚለወጥ አገልግሎት የለንም። እጅግ የከበረውን አገልግሎታችንን በሚያልፍና በሚጠፋ ቢበዛ ሆድ ለሚሞላ ደሞዝ አሳለፈን አንስጥ እላለው። 

ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። (ዕንባቆም 3፣17-18) ክህነቴንም አልሸጥም አለውጥም የሚል ይህን መልእክት ሼር ያድርግ።

No comments:

Post a Comment