Tuesday, 4 August 2020

ምስለ ፍቁር ወልዳ ከመፅሐፍ ቅዱስ አንፃር በትንሹ ሲገመገም



ብዙዎቻችን '' ምስል ፍቅር ወልዳ '' የሚለውን ስዕል ሉቃስ እንደሳለው ሲነገር እንሰማለን። እንደ ሃይማኖቱን ለሚወድና የቤተክርስቲያን አባቶችን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በላይ ለሚወስድ የሚረገረውንም ነገር ያለ ጥያቄ ለሚቀበል ማንኛውም ሰው፤ ማርያም ጌታ ኢየሱስን አቅፋ የሚያሳየው ስዕል ደስ ሊያሰኘው ይችላል። ነገር ግን እንደ ባለአእምሮና አስተዋይ ሁሉን በቃሉ እንደሚመረምር ሰው ግን ለምንና እንዴት ያሉ መሰል ጥያቄዎችን መጠየቅና እውነቱን ለማወቅ መጣር አስፈላጊም ተገቢም ነው። 

እኔ ከጌታ እናት ማርያም አንዱ የምማረው ነገር '' ይህ እንዴት ይሆናል '' የሚለውን ጥያቄ ነው። " ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። " (ሉቃ1፥34) እንኳን ሰው ይቅርና መላእክት እያናገረህ ጥያቄ ጠይቆ እውነቱን መረዳት ከእሷ እማራለው። አዎ ይህ መሰረታዊና ዛሬ ለቆምኩበት እውነት ጠይቆ መረዳትንና ቃሉን መመርመር ወሳኝነት አለው። ዝም ብሎ ስለተባለና በዛ በሚባልበት ስፍራ ረጅም እድሜ ከነገሩ ጋር አብሬ መኖሬ የተባለውን ነገር እውነተኛ አያሰኘውም። 

ድንግል ማርያም ልጇን ይዛ ተስላለች ብሎ ለሚያምን ሰው ቢያንስ መሰረታዊ ጥያቄዎችን መጠየቅና መረዳት አለበት ብዬ አስባለው። በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተቀረፀ ምስልና ስዕል ምን ይላል? የእግዚአብሔር ሀሳብስ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ እጅግ መሰረታዊ ነው በተለይ በአዲስ ኪዳን። የሚገርመው በዛ በአሮጌው ኪዳን እንኳ እግዚአብሔር ይህን ብሏል......

" እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። " (ትንቢተ ኢሳይያስ 42፥8) ልጁን ቤዛ ሊቀካህን አርጎ በሾመበት አዲስ ኪዳን ደግሞ "፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። " (የዮሐንስ ወንጌል 4፥24) ተብሎ ተፅፏል። 

ሲቀጥል ወንጌላዊው ሉቃስን ሰዓሊ አርጎ ማምጣት ስዕሉን መንፈሳዊ ያደርገዋል ወይ? ይህን የምጠይቀው የብዙዎች መከራከሪያ ሉቃስ ስለሳለው ተቀባይነት እንዳለው አድርገው ማመናቸው ነው። አበበም ሳለው ከበደ ስዕሉ ምን ለውጥ አለው? 

ቅዱሳት መፃህፍት በእግዚአብሔር መንፈስ ስለመፃፋቸው ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል ስዕል ግን ፍፁም የለም ??? 

ሌላው ሉቃስ ስሎታል የሚባለው ስዕል ኢየሱስ ህፃን እያለ በእናቱ እቅፍ ውስጥ ሆኖ ነው። ለመሆኑ ሉቃስና ኢየሱስ መች ነው የተገናኙት? የተሳለውስ ህፃን ሆኖ ነው ወይስ ካደገ በኃል በምናብ ነው? በጣም ደግሞ የሚገርመው የስዕሉ የአሳሳል ዘይቤ ድንግል ማርያም በምድራዊ በረከት እጅግ የከበረችና የናጠጠች ሐብታምና የቤተመንግስት ንግስት አስመስሎ መሳሉና ኢየሱስን ደግሞ እንደ ፊልም ማሳመሪያ ውብና ቆንጆ አድርጎ መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ከነገረን ጋር እጅግ የሚጣላና የማይስማማ ያደርገዋል። 

ድንግል ማርያም ጌታን እንዴት እንደወለደችውና በምን ያህል ዋጋ በመክፈል እንዳሳደገችው ለሚያውቅ ሰው በተዋበ አልባስ፣ የወርቅ ፈርጥ ያለበት የሐር ልብስና የወርቅ አክሊል ሲያይ መጠየቅ ያለበት ጉዳይ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር መስዋዕት ሲያቀርብ ጠቦት ለማምጣት ገንዘብ ላልበቃው ሰው የሰጠው አማራጭ ርግብ አንዱ ነው (ዘሌ 5፥7)። ድንግል ማርያምን ስሏታል የተባለው ሉቃስ የፃፈው ወንጌል ላይ ግን ያቀረበችውን ስንመለከት ግጭት ይፈጥርብናል። 

"፤ እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ። የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ። ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። " (የሉቃስ ወንጌል 2: 22-24)

ኢየሱስን ደግሞ ይወደድ ዘንድ ደምግባት እንዳልነበረው (ኢሳ 53) እና የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ (ፊልጵ 2፥7) ተብሎ እንጂ እንደ HOME ALONE ሆሊውድ ፊልም ቆንጅዬ ሲያዩት የሚያሳሳ ድንቡሽቡሽ ልጅ እንዳልሆነ መረዳት እንችላለን። ይህስ ጥያቄ መመለስ የለበትም? 

ይህ ጉዳይ ሲነሳ እጅግ የሚደንቀኝ ነገር ደግሞ ሳለው የተባለው ሉቃስ ራሱ በፃፈው በሐዋርያት ስራ ላይ የፃፈው ትዝ ሲለኝ ነው። በነገራችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሉቃስ ባለመድሂት እንጂ ሰዓሊ እንደሆነ ምንም አልተናገረም። " የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ " (ወደ ቆላስይስ ሰዎች 4፥14)። ምን እንዳለ ታውቃላችሁ? 

" እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም። " (የሐዋርያት ሥራ 17፥29)

እንዲህ ያለ ወንጌላዊ ከተናገረው ቃል በተቃራኒ ጊዜውን በእርድና በበርበሬ ቀለም ያጠፋል ብላችሁ ታምናላችሁ? አይመሰለኝም እንደው ነገሩን ለጥጣችሁ አላሰባችሁበት እንጂ ማሰቡንስ አታስቡም ነበር። 

አንድ የቤተክርስቲያን አባት በንግስ ጊዜ ይህን ምስለ ፍቁር ወልዳ ስዕል የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ይዘው ሲዘምሩ ያዩና ይህ ህፃን እስካሁን በእናቱ እቅፍ ውስጥ ነው እንዴ ያለው? መች ነው የሚወርደው? ብለው ጠየቁ ይባላል። እናንተስ መቼ ከእናቱ እቅፍ ወርዶ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት በቁመትና በሞገስ ካደገ በኃላ ስለ በደልና ኃጢአት ራሱን አሳልፎ በመስቀል ላይ ሞቶ ደግሞም እኔኑን ስለማጽደቅ በሶስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ በመነሳት ለዘላለም እኖርበት ዘንድ ስፍራ ሊያዘጋጅል ወደ አባቱ በመሄድ በማያልፍ የሕይወት ኃይል በግርማ ቀኝ አልተቀመጠምን?  ብላችሁ የማትጠይቁት? 

ማስተዋል ይብዛላችሁ ከተፃፈው እንዳናልፍ ጸጋው ይርዳን አሜን።

Monday, 3 August 2020

መሻርና መፈጸም



“እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፣  ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፣(ማቴ. 5፡17)። (ክፍል አንድ)

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ፦ ብዙ ወንድሞቻችን እና አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትና መምህራን “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፣ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፣” (ማቴ. 5፡17)፣ የሚለውን ኀይለ ቃል የሚረዱበት መንገድ የብሉይ ኪዳኑ ሕግ (የሙሴ ሕግ) አሁንም እንደሚሠራና በሐዲስ ኪዳንም ልንጠብቀው እንደሚገባን፣ ትእዛዝም እንደ ሆነ፣ ካልፈጸምናቸው ደግሞ እንደምንኮነንና የገሃነመ እሳት ፍርድ እንደሚጠብቀን ቆጥረው ሲጽፉና በፌስ ቡክ ላይ ሲለጥፉ ስላየሁ ነው። ምናልባት ለጸሐፊዎቹም ሆነ ለአንባቢዎች ይጠቅማል ብዬ ስላሰብሁ ይህን ጽፌአለሁና በትዕግሥት አንብቡት።   

ብዙ የቤተ ክርስቲያናችን መምህራን የብሉይ ኪዳኑና የሐዲስ ኪዳኑ አገልግሎትና ትምህርት ሲምታታባቸውና ምእመናንንም ግራ ሲያጋቡ ይስተዋላል። ለዚህ ለተምታታና ግራ ለተጋባ ትምህርት ምክንያት የሆናቸው የዕውቀትና የትምህርት ማነስ አይመስለኝም። ችግሩ የመጣው ኢትዮጵያ የብሉይ ኪዳኑን ሕግና አዲስ ኪዳንንም ተቀብላለች ከሚል አስተሳሰብና በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ለሚታዩ አንዳንድ አይሁዳዊ ባህልና መንፈሳዊ ለሚመስሉ ሰው ሠራሽ ልምምዶች ሽፋን ለመስጠት የታሰበ አካሄድ ይመስላል። ሕጉን ተቀብላለች ወይም አልተቀበለችም የሚለውን ጉዳይ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አሁን ማንሣት አስፈላጊም ጠቃሚም ባለመሆኑ እንተወዋለን (1 ጢሞ. 1፡7)። 

በቅድሚያ በማቴዎስ 5፡17 ላይ የተጠቀሰውን ኃይለ ቃል ትርጉም በሚገባ ለመረዳት፣ የሕጉን (የኦሪትን) ምንነት፣ ለማን እንደ ተሰጠና የተሰጠበትን ዓላማ መረዳት አስፈላጊ ነው። 

1ኛ. ሕጉ የተሰጠው በሲና ተራራ ለእስራኤላውያን ብቻ ነው፣ ሕጉ ለነ አብርሐም ይስሐቅና ያዕቆብ፡ ወይም ለአሕዛብ አልተሰጠም (ዘጸ. 19᎑1-6, ዘዳ. 7:6-11) ፣ አብርሐም የጸደቀው ሕገ ኦሪትን በመጠበቁ አልነበረም፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ ቃል በማመኑ ነው እንጂ (ዘፍ. 15፡6)። 

2ኛ. የሙሴ ሕግ ሰውን ለማጽደቅ አልተሰጠም። ሕጉ የተሰጠው ከፈርዖን ባርነት ነጻ ለወጣ፣ በበጉ ደም ለተዋጀና ለእግዚአብሔር ለሆነ ሕዝብ (ለዳነ ሕዝብ) መተዳደሪያ እንዲሆን (ዘጸ. 19፡1-25) ተሰጠ እንጂ፣ ከባርነት ነጻ ለመውጣትና ከነዐንን እንዲወርሱ በቅድመ ሁኔታነት አልተሰጠም (ዘዳ. 7፡6-8)።  

3ኛ. ሕጉ ቅዱስ ነው፣ መንፈሳዊም ነው (ሮሜ 7፡ 12-14)፣ ሕጉ የተሰጣቸው ሰዎች (እስራኤላውያን) ሥጋውያን ስለሆኑ ሕጉን መፈጸም ስለማይችሉ እርግማንን ያመጣል (ገላ. 3፡10-11)፤ 

4ኛ. የሕጉ ፍጻሜ ክርስቶስ ስለሆነ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ በሞግዚትነት እንዲያገለግል በሙሴ በኩል በጊዜያዊነት የተሰጠ ነው (ገላ. 3፡23-25)፣ 

5ኛ. ሕጉ (ኦሪት) የሰዎችን ኃጢአተኛነት፣ የእግዚአብሔርን ቅዱስነት ይገልጣል (ሮሜ 3፡20፣ 7፡7፤ ገላ. 3፡21᎑22)፣ እንጂ ሰዎችን ፍጹማን (ንጹሐን) ማድረግ አይችልም፣ (ገላ. 2፡16፤ ገላ. 3፡11)፤ 

6ኛ. ሕጉ በመሥዋዕቱ፣ በክህነቱ፣ በመቅደሱና በሥርዐቱ፣ ወዘተ. የጥላ አገልግሎት በመሆን የኢየሱስን ቤዛነት በእምነት ለማየት እንዲችሉ ለእስራኤል የተሰጠ ስለሆነ፣ አማናዊው መሥዋዕት፣ መቅደስና ሊቀ ካህናት የሆነው ክርስቶስ ሲመጣ ይሟላል ማለት ነው፣ (ዕብ. 10፡1᎑2)። 

7ኛ. በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከጨለማ ሥልጣን እጅ ነጻ ለወጣ የሐዲስ ኪዳን ሕዝብ (ለቤተ ክርስቲያን) መተዳደሪያ እንዲሆን የብሉይ ኪዳኑ ሕግ (ኦሪት) አልተሰጠም፣ ሊሆንም አይችልም። የሐዲስ ኪዳን ሕዝብ በእጅ ሳይሆን በመንፈስ፣ በሥጋው ሳይሆን በልቡ  የተገረዘ ሕዝብ ነው (ሮሜ 2፡29፤ ቆላ. 2: 11) ። ሕጉ በድንጋይ ጽላት ሳይሆን በልብ ጽላት የተጻፈ (2 ቆሮ. 3-3)፣ መሥዋዕቱ የእንስሳት ሳይሆን የክርስቶስ ሥጋና ደም የሆነለት አዲስ ሕዝብ ነው። አምልኮው ምድራዊ ሳይሆን፣ ሰማያዊ፣ ውጫዊ ሳይሆን፣ ውስጣዊ፣ ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ፡ ከሕግ በታች ሳይሆን ከፀጋ በታች (ዮሐ 1:16-17፤ ሮሜ 6:14) የሆነ ሕዝብ ነው። 

አሁን በሐዲስ ኪዳን የኦሪትን ሕግ እንፈጽማለን፣ እናስፈጽማለንም እያሉ ማስተማር በክርስቶስ የተፈጸመውን ሥራ ያለመረዳት፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መምረጥ (ዕብ. 6፡4-6)፤ ከነጻነት ወደ ባርነት መምጣት ነው (ገላ. 4፡30-31)።  

በማቴዎስ 5፡17 ላይ የተጠቀሰው በአማርኛ “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፣ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፣” የሚለውን ኃይለ ቃል ለመረዳት  “ለመሻር” እና “ልፈጽም” የሚሉትን ሁለት ቃላት (ግሶች) በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። በግእዝ “ኢይምሰልክሙ ዘመጻእኩ እስዐር ኦሪተ ወነቢያተ። ኢመጻእኩ እስዐሮሙ አላ እፈጽሞሙ።” በሚል ይነበባል። “ለመሻር” ና “ልፈጸም” የሚባሉት ሁለት ግሶች ከግእዙ “እሰዐር” እና “እፈጽሞሙ” ከሚለው ፍች ጋር ተስማሚ ናቸው። 

እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ (አዲስ ኪዳን) በተጻፈበት እናት ቋንቋ በግሪክኛው “ለመሻር” የሚለው ቃል (ግስ) kataluso “ካታሉሶ” (katalusai) to abolish, to destroy፣ “ማጥፋት” “መደምሰስ” ማለት ሲሆን፤ እንዲሁም “ልፈጽም” የሚለው ቃል (ግስ)  በግሪክኛው plero “ፕሌሮ” (plerusai) to fulfill፣ ከሚል ቃል የተገኘ ነው። plero “ፕሌሮ” የሚለው ቃል ትርጉምም  “ማሟላት” “ሙሉ ማድረግ” ማለት ነው። 

በዚህ መሠረት የማቴዎስ 5፡17 ን ንባብ ስንተረጉመው “እኔ ሕግንና  ነቢያትን “ላጠፋ” (“ልደመስስ”) የመጣሁ አይምሰላችሁ፣ “ላሟላ” (“ሙሉ ላደርግ”) እንጂ “ልደመስስ” (“ላጠፋ”) አልመጣሁም። የሚል ይሆናል። ስለሆነም፦

አንደኛ፣ ጌታችን ሕግን “ላሟላ” እንጂ “ልደመስስ”፣ (ላጠፋ) አልመጣሁም በማለቱ፤ ሕጉ እንዲሁ በከንቱ እንዳልተሰጠ፣ እንደማይደመሰስ ነገር ግን “እንደሚሟላ”  ያመለክታል። በዚህም ሕጉ ቅዱስ ቢሆንም ኃጢአተኛውን ሰው መቀደስ፣ ማጽደቅና ፍጹም ማድረግ ባለመቻሉ በክርስቶስ መሟላት የሚያስፈልገው መሆኑን ያሳያል (ዕብ. 7፡18᎐19፤ )።

ሁለተኛ፣ “እኔ ሕግንና  ነቢያትን “ላጠፋ” (“ልደመስስ”) የመጣሁ አይምሰላችሁ፣ “ላሟላ” (“ሙሉ ላደርግ”) እንጂ “ልደመስስ” (“ላጠፋ”) አልመጣሁም፣ በሚለው ኃይለ ቃል ውስጥ “ላጠፋ” እና “ላሟላ” የተባሉት ግሶች የተነገሩት፤ በአንደኛ መደብ ነጠላ ቁጥር ዐቢይ አንቀጽነት ሲሆን፣ “እኔ” በሚል ተውላጠ ስም የተጎላበቱ በመሆናቸው የድርጊቶቹ ፈጻሚ ራሱ ጌታ ኢየሱስ መሆኑን ያሳያል። በዚህም ሕጉን “የማያጠፋውና የማይደመስሰው” ነገር ግን “የሚያሟላው” ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያመለክታል። ስለዚህ እኛ እንድናሟላው የተሰጠን ትእዛዝ ያለመኖሩን ያሳያል። 

ሦስተኛ፣ ሕጉ (የብሉይ ኪዳኑ ሕግ) የሚያመለክተውና የሚናገርለት መሢሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመጣ የሕጉ አገልግሎት ፍጻሜ አግኝቷል (ተሟልቷል) ማለት ነው። ስለዚህ ሕጉ ጌታ ኢየሱስ እስኪመጣ ድረስ የሚያገለግል ሞግዚት (ማቆያ) ከሆነና፣ ሕጉ የሚናገርለት ኢየሱስ ከመጣ፤ አሁን በአዲስ ኪዳን የሕጉ አገልግሎት ፍጻሜ ስላገኘ አይቀጥልም ማለት ነው። 

አራተኛ፣ ሰው ከኃጢአቱ የሚነጻው፣ የሚጸድቀውና የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሠራው የማዳን ሥራ በማመኑ እንጂ ሕግን በመፈጸሙ አይደለም (ሮሜ 3፡24-28፤ ዮሐ. 1፡12᎐13)። ጳውሎስ እንዳስተማረው “ሰው ያለ ሕግ ሥራ፣ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለን” (ሮሜ 3፡28)፤ “በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ፣ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን (ሐዋ. 13፡39)ብሎአል። 

5ኛ. በሐዲስ ኪዳን ምእመናን ከሕግ በታች ሁነው ሕግን የሚፈጽሙት ሳይሆን፣ ከጸጋ በታች ሆነው ሕጉ የሚጠይቀውን ብቻ ሳይሆን በአዲስ ሕይወት፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል  አብልጠው የሚፈጽሙት የፍቅር ሕግ ነው (ማቴ. 5፡22፤ 28፤ 34፣ 39፤ 44)። 

የሙሴ ሕግ የማያድንና ጊዜያዊ መሆኑን፡የዳንነውና የምንኖረውም በወንጌል ሕግ በፀጋ እንደሆነ፦የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ጎርጎርዮስ “የፍቅርን ሕግ ወንጌልን ሠራልን ፡ የላም ሥጋ፡ የፍየል ደም ሳንሻ ኃጢአታችንን ማስተስረይ ተቻለን፡ ያች ቀዋሚት ያልነበረች ሕግ ነበረች፡ ድኅነት የማይገኝባት ትእዛዝም ነበረች“ በማለት አስተምሮአል (ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ)።

ውድ አንባቢ ሆይ! ሕጉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከተሟላ በኋላ በብሉይ ኪዳኑ ሕግ ለመኖር መሞከር ሕጉ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዳልተሟላ መቁጠር ከመሆኑም በላይ፣ የጌታ ኢየሱስን የማዳን ሥራ፣ ሰው መሆኑን፣ መከራ መስቀሉን፣  መሞትና መነሣቱን እንደ መካድ ይቆጠራል። ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ  “በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል” (ገላ. 5፡4) ያለው።

ከመምህር ጌታቸው ተረፈ ፌስቡክ የተወሰደ

Friday, 5 June 2020

እንዘምር ለጌታ እንዘምር

           
የሰው ልጅ ከጥፋት ውሃ ያመልጥ ዘንድ ኖህን መርከብ ስራ አለው ይህ የእግዚአብሔር ፍቃድ ነበር። የእስራኤል ህዝብ ከግብፅ ባርነት ይወጣ ዘንድ በግ አርደው የቤታቸውን የበር መቃንና ጉበን ደም እንዲቀቡት አዘዘ አመለጡም ይህም የእግዚአብሔር ፍቃድ ነበር። የሰው ልጅ ከኃጢአት ባርነት ይላቀቅ ዘንድ፣ ከዘላለም ሞት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ይሻገር ዘንድ፣ ከኩነኔ ወጥቶ ይጸድቅ ዘንድ፣ ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን ይገባ ዘንድ፣ ከሲኦል ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት ይፈልስ ዘንድ፣ ልጁን ኢየሱስ ወደ ዓለም በመላክ የሁሉ ቤዛ አደረገው። ዛሬ ለእግዚአብሔር የምናቀርብለት ምስጋናና የከንፈራችን መስዋህት አዎንና አሜን በሆነው በኢየሱስ ስም ነው ይህም የእግዚአብሔር ፍቃድ ነው። ከዚህ ስም ውጪ እግዚአብሔር ምንም ነገር አይቀበልም ይህም የእግዚአብሔር ፍፁም ፈቃድ ነው። እንዲህ ተብሎ እንደተፃፈ:-

" እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። " (ቆላ 3፥17)

በኢየሱስ ስም ተመስገን እግዚአብሔር
በኢየሱስ ስም ከፍ በል በክብር
በኢየሱስ ስም ተባረክ አባታችን
ማደሪያህን ይክበበው ዝማሬያችን

Monday, 1 June 2020

911 ( የአደጋ ጊዜ ጥሪ )


ለመደወል ዝግጁ ኖት?

አብዛኛው የዓለማችን ሀገራት ይጠቀሙበታል። አንድ ሰው አደጋ ወይም ደግሞ የቀንም ሆነ የማታ ዘራፊ ሲያጋጥመው የመጀመሪያው ስራ ቢኖር 911 መደወል ነው። ዜጋው መንግስት ያዘጋጀውን የአደጋ ጊዜ እርዳታ በመተማመን ይደውላል። መንግስትም የቀረበለትን የእርዳታ ጥሪ በመቀበል እጁን ይዘረጋል። ልክ በአደጋ ጊዜ የይድረሱልኝ ጥሪ እንደሚያሰማ እንደ አንድ ዜጋ አማኞችም በምልልሳችን ወቅት በሚያጋጥመን ፈተናና መከራ እግዚአብሔር ፈጥኖ እንዲያስመልጠን የምንደውለው መንፈሳዊ ደውል 911 አለን።

በዚህ አሰራር እጅግ በረቀቀ መንፈሳዊ ስሌት ለአማኞች በሚልቅ መልኩ በፍጥነት የሚሰራና ዛሬም ወደፊትም ህያው ሆኖ የሚቀጥል የመንፈሳዊ አደጋ ጊዜ ጥሪ ነው። እርሱም መዝሙር 91:1( 91፥1ጀምሮ )

ይህ የመዝሙር ክፍል አማኞች እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ምን ያህል ዋስትና እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። እግዚአብሔር በአደጋዎች ሁል መጠጊያችን እንደሚሆን፣ ከዚህም የተነሣ መንፈሳዊና ሥጋዊ አደጋ ሲመጣ ቀድመን የእግዚአብሔርን ጥበቃ ልንፈልግ እንድምንችል የሚረጋግጥ ስንኝ ነው።

በእግዚአብሔር ለተወደድን ይኸውም ራሳችንን ለልዑል እግዚአብሔር ፈቃድና ጥበቃ አሳልፈን ለምንሰጥ፣ በእግዚአብሔር ሀልዎት ዕለት ዕለት መኖር ለምንፈልግ እጅግ ዋስትና ይሰጣል። እንዳለው ነብዪ በእጁ ጥላ ሰወረኝ፤  የተወለወለ ፍላጻ አደረገኝ፤ በሰገባውም ውስጥ ሸሸገኝ። (ኢሳ 49፥2) በእርግጥ እግዚአብሔር የእውነት መደበቂያችን ነው። ተሸጉጠን ክፉውን የምናሳልፍበት ምሽጋችን።

የዚህን መዝሙር ስንኞች ሲያነቡ ከነችግሩና ከነመከራው አንብቦ የሚጨርስ ማነው? ስትጀምር የነበረው አደጋ ወይም መከራ ሁሉ ቁጥር አንድ (ቁ1) ጋር አብቅቶ ሌላ ርዕስ ውስጥ ትገባላችሁ። እስኪ ከፋፍለን የእግዚአብሔርን ጥበቃ እንቃኘው

1) መዝሙሩ 91፥1-2 ( ከአደጋ መውጫ አንድ)
'' በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።እግዚአብሔርን። አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ። ''

ከሁሉ በላይ የሆነውንና የኃይሉን አምላክ መጠጊያው አድርጎ የሚኖር ሰው የሕይወቱ ዋስትና የሚያስተማምን በመሆኑ እግዚአብሔር መጠጊያዬና ምሽጌ የምተማመንበት ፈጣሪዬም ነው ብሎ ይመሰክራል።
=} ምሳሌ:- አንድ ህፃን አባቱ እቅፍ ውስጥ ሆኖ ወደ ላይ እየወረወረ ሲያጫውተው ከሚተማመነው በላይ አደጋ ውስጥ ሆነን በእግዚአብሔር መተማመን። ይህንንም በእምነት መመስክር ያጋጠመን አደጋ ከእኛ ዘንድ ያሸሸዋል።

2) መዝሙር 91፥3-4 (ከአደጋ መውጫ ሁለት)
'' እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። ''

እግዚአብሔር ሕዝቡን ከጠላት ይጠብቃል፣ በላባዎቹ ይጋርዳቸዋል፣ ጋሻ እና መከታ ይሆናቸዋል። ለእርሱ የአደጋውም ሆነ የችግሩ ግዝፈት እኛን ከመጠበቅ አያስቀረውም።
=} አባባል:- ለእግዚአብሔር የችግርህን መጠን ከምትነግረው ይልቅ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለችግርህ ንገረው። የተባለውም ለዚህ ነው።

3) መዝሙር 91፥5-6 (ከአደጋ መውጫ ሦስት)
'' ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። ''

የእግዚአብሔር እንክብካቤ ጽኑና በቂ ነው ምክንያቱም ጥበቃው የተመሰረተው በማንነቱ ላይ ስለሆነ። እርሱ ሲጠብቅ ቀን አይል ሌሊት አይል ሁልጊዜ ነው። በጊዜ አይወሰን  በስፍራም እንዲሁ በመዞር የተደረገ ጥላ የለበትምና። የእግዚአብሔር ጥበቃ በቀንና በሌሊት እንደ ሆነ ተፈጥሮአዊ በሆኑ ምክንያቶች ከሚመጣ ፍርሀትና  ድንጋጤ ይጠብቀናል።
=} ሰባኪው:- እንኳን ሌሊት ተኝተን አይደለም ቆመንም አይተን ከምናልፈው አደጋ ሳናየው ጠብቆን ያሳለፈን እጅግ ብዙ ነው።  ተውት ያስተዋልነውን!!!

4) መዝሙር 91፥7 (ከአደጋ መውጫ አራት)
'' በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። ''

እርሱ በምድር ላይ በሚሆኑ ነገሮች ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን ስላለው ለጥበቃው ወሰን የለውም። እንክብካቤውና ጥበቃው የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለማሳየት ሺህ እና አሥር ሺህ በማለት ይገልፀዋል። እግዚአብሔርን የሚያልፍ ችግር የለም።
=} መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ:- ሕዝቅያስ እንዳጽናናቸው
(መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 32፥7-8 ) ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው ብሎ አጸናናቸው። ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናና።

5) መዝሙር 91፥8 (ከአደጋ ጊዜ መውጫ አምስት)
'' በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ብድራት ታያለህ። ''

ጻድቃን የእግዚአብሔርን ማዳን በእምነት ዐይን ማየታቸው ይበለጥ እንዲበረቱ ያደርጋቸዋል እግዚአብሔር ጻድቃንን ለመጠበቅና ለመባረክ ቃል ገብቷል ጻድቃን የእግዚአብሔርን ፍትሕና ታማኝነት እንዲሁም የክፉዎችን መቀጣት በዐይናቸው ይመለከታሉ።
=} አመለካከት:- ሰው በሚያየው ሳይሆን በሚያምነው ይኖራልና።

6) መዝሙር 91፥9-10(የአደጋ መውጫ ስድስት)
'' አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፤ ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። ''

ልዑሉን መጠጊያችን በማድረግ የጥበብን መንገድ እንድንከተል ያበረታታል እርሱ መጠጊያችን ነው በምድር ላይ የሚሆነው ማንኛውም ነገር በእርሱ ቁጥጥር ሥር ነው ክፉ ነገር ወይም መቅሠፍት ቢሆን ያል እርሱ ፈቃድ አይሆንምና።
=} ሂሳባዊ ቀመር:- ይጠጌ አይነኬ (asymptote)፤ ቅርብ ቢመስልህም፣ ሊነካ የቀረበ ቢመስልም ሁሉን ማድረግ በሚቻለው ሀሳቡም ይከለከል ዘንድ ከቶ በማይቸለው ተአምር አድራጊነት ሳይነካህ ያልፋል። ይታከክሃል፣ ይቀርብሃል አይደርስብህም፣ ይመጣብሃል አያገኝህም።

7) መዝሙር 91፥11-13( ከአደጋ ጊዜ መውጫ ሰባት)
'' በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። ''

እግዚአብሔር እኛን አማኞችን በምንሄድበት ሁሉ ይጠብቁን ዘንድ መላእክቱን ያዛቸዋል። መላእክቱ እኛን ከአደጋ ለማስመለጥ እንዲጠብቁን ዘወትር  እንዲታደጉን በተጠንቀቅ በዙሪያችን አሉ። እግዚአብሔር በልጆቹ ላይ ብዙ ነገር እንዲደርስ ሊፈቅድ ይችላል ይሁንና አንድም ኅይል ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጭ አንዳልሆነ ያውቃሉ።
=} እንቆቅልህ:- እነሱ የሚያዩን እኛ የማናያቸው ዘወትር አብረውን ያሉ የእግዚአብሔር ታዛዦች። ካላወቃችሁት ሀገር አልሰጣችሁም ሰማይ ግን እንካኅሁ።

8) መዝሙር 91፥14(የአደጋ ጊዜ መውጫ ስምነት)
'' በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ። ''

እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱት እና ስሙም ለሚያውቁ ሁሉ የማዳኑን ንግግር ያበሰረበት ክፍል ነው። መውደድ የሚለው ቃል እግዚአብሔርን ከልብ መናፈቅንና መሻትን ይሆንላቸዋል።
=} የጌታ ቃል:- ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ በታች እንደምትሰበሰብ እንዴት ይልቅ እርሱ እንደሚጋርደን።

9) መዝሙር 91፥15( የአደጋ ጊዜ መውጫ ዘጠኝ)
'' ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ አከብረውማለሁ። ''

ይህ ቃል የአማኝ የድምፅ ብክነት የሚባል ነገር እንደሌለ ያሳያል። ሲጣራ ደመና አይከለክለውም፣ የፀሐይ ግርዶሽ አይዘውም፣ ንፋስ አይወስደውም፣ ዝናብ አይመልሰውም። አቤት የሚል ብቻ ሳይሆን በመከራ የማይተወን አብሮን የሚሆን ደግሞም የሚያድነን ጌታ አለ።
=} መዝሙር ዘ ማስተካከል:-
ደጅ ጠናሁ ቆይቼ ኪዳነ ምህረትን
ተፅናናሁኝ ረሳው ሀዘኔንን
ጌታ ኢየሱስ የሕይወት መድህን
ዋስትዬ መላው ዘመኔን

10) መዝሙር 91፥16(የአደጋ ጊዜ መውጫ)
'' ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ። ''

ሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ ሲገረም ''እንግዲህ ምን እንላለን''  ይላል ደግሞስ ምንስ ይባላል እኔም ከምናገር እጅህን አፍህ ላይ ጫን ይለኛል። ይህ ሁሉ ጥበቃ ለእኔና ለእናንተ ነው። እውን ከዚህ የቀረበ ደግሞም ህያው የሆነ ነገር ምን አለ?
=}መዝሙር
 እረ ስንቱ ስንቱ ታለፈ
   ጌታዬ እየደገፈ።

ወዳጆቼ የትኛውም አደጋ ሲያጋጥማችሁ
ደውል/ደውይ/ደውሉ ወደ መዝሙር 911(መዝ 91፥1ጀምሮ)
በእርግጥም መውጣት ይሆንላችኃል።

Sunday, 31 May 2020

የቃል ኪዳኑ ታቦት


ኦሪት ዘጸአት 25÷10-22
ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን።በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ።መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው። ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጐን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ።መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከቶም አይውጡ። በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ።ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ።ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ። የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።

የማደሪያው ድንኳን



ኦሪት ዘጸአት 25
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦

2ስጦታ ያመጡልኝ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ በገዛ እጁ ሊሰጠኝ በልቡ ከሚያምረው ሰው ሁሉ መባ ተቀበሉ።

3ከእነርሱም የምትቀበሉት መባ ይህ ነው፤

4ወርቅ፥ ብር፥ ናስም፥ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀይም ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም፥

5የፍየልም ጠጕር፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣ ቁርበት፥ የግራርም እንጨት፥

6የመብራትም ዘይት፥ ለቅብዓት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፥

7መረግድም፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ።

8በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ።

9እኔ እንደማሳይህ ሁሉ፥ እንደ ማደሪያው ምሳሌ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት።

10ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን።

11በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት።

12አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ።

13መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው።

14ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጐን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ።

15መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከቶም አይውጡ።

16በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ።

17ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ።

18ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ።

19ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ።

20ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ።

21የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ።

22በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።

23ርዝመቱም ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ገበታ ከግራር እንጨት ሥራ።

24በጥሩም ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አድርግለት፤
25በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አድርግለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አድርግለት።

26አራትም የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አድርግ።

27ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶቹ በክፈፉ አቅራቢያ ይሁኑ።

28ገበታውን ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው።

29ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ ወጭቶችዋን ጭልፋዎችዋንም መቅጃዎችዋንም ጽዋዎችዋንም አድርግ፤ እነርሱንም ከጥሩ ወርቅ አድርጋቸው።

30በገበታም ላይ የገጽ ኅብስት ሁልጊዜ በፊቴ ታደርጋለህ።

31መቅረዝንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ፤ መቅረዙ ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀጠቀጠ ሥራ ይደረግ፤ ጽዋዎቹም ጕብጕቦቹም አበቦቹም አንድነት በእርሱ ይደረጉበት።

32በስተጎኑ ስድስት ቅርንጫፎች ይውጡለት፤ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስትም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ይውጡ።

33በአንደኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፤ እንዲሁም ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አድርግ።

34በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አድርግ።

35ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ይሁን።

36ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከእርሱ ጋር አንድ ይሁኑ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ይደረግ።

37ሰባቱንም መብራቶች ሥራ፤ በፊቱ ያበሩ ዘንድ መብራቶቹን ያቀጣጥሉአቸዋል።

38መኰስተሪያዎችዋን የኵስታሪ ማድረጊያዎችዋንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ።

39መቅረዙም ዕቃውም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ ይሠሩ።

40በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ።

Monday, 6 April 2020

መጠንቀቅ መፍራት አይደለም


" ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። " (ኢሳ 26፥20)

ሰሞኑን የሁሉም ሰው ጸሎትና ምልጃ ዓለምን እያዳረሰ ያለውን የኮሮና በሽታ መፍትሄ ከእግአብሔር ይመጣ ዘንድ ነው። በሌላ ጎን ደግሞ የዓለም ጠቢባን፣ ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ዶክተሮች ኃያላን ተብለው የሚጠሩ ሀገራት በሙሉ በጭንቅ መፍትሄ ፍለጋ ቫይረሱን እንዳይዛመትና እንዳይሰራጭ ለማድረግ ብሎም ማጥፋት የሚቻልበትን መንገድ ለማግኘት ያለ እንቅልፍ ይዳክራሉ ግን እስካሁን ምንም አላገኙም።

እኔ የማመልከው ጌታ ኢየሱስ ግን ቫይረሱ ለመስፉፉት፣ ለመባዛት እንዲሁም ለመግደል የሚመቸውንም ነገሮች ቢሆን ተጠቅሞ ሊያስወግደው እንደሚችል አምናለው። ያለ እርሱ ይህን ጊዜ ማለፍ አይቻልም።

የዚህ በሽታ መስፋፋት ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በግልና በተቋም እንዲሁም በመንግስትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ጊዜአዊ የተባሉትን የመከላከያ ዘዴዎች እየተከናወኑ ይገኛል። በመሆኑም የሚደረጉትን ጥንቃቄዎች እንደፍራቻ የተመለከቱት ሰዎች ገጥመውኛል በተለይ ክርስቲያኖች።

መፍራትና መጠንቀቅ እጅግ መቀላቀል የሌለባቸው የተለያዩ ሀሳቦች ናቸው። ሁለቱንም ሀሳቦች በልቶ ማየት ያስፈልጋል። መጽሐፍ ሲናገር "፤ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥ " (ምሳ 2፥11) ይላል ይህን ቃል የሚያምን ሁሉ በሕይወት ዘመኑ ይጠነቀቃል በማስተዋል ይራመዳል ነገር ግን የመኖሩ ህልውና በመጠንቀቁና በማስተዋሉ እንዳልሆነ በመረዳት ጭምር ማለት ነው። የሚገርመው ነገር እንደዛም ሆኖ መጠንቀቅ ግድ ነው። " በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ " (ምሳ 3፥5) ተብሎም እንደተፃፈ።

ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር  " ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። " (ማቴ 10፥28) እንዳለው አማኝ ማንን መፍራት እንዳለበት የተረዳ ይመስለኛል። አሁን እየተደረጉ ያሉት መከላከያዎች ቫይረሱን ፍራቻ ሳይሆን ከጥንቃቄ አንፃር ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። በመንግስትም ሆነ በጤና ባለሙያዎች የሚነገረውን መከላከያ (መታጠብ፣ መራራቅ ፣ መሸፈን፣ መቀመጥ/ቤት)  መተግበር የክርስቲያን ግዴትም ጭምር ነው። ጊዜውን የሚዋጅና ለሌላውም ምሳሌ የሚሆን ልበ ሙሉ ክርስቲያን ሆኖ መገኘት ያሻል።

ያለዚያማ ..... ያለዚያማ........ " እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና " (1ኛ ጢሞ 1፥19) እንዳይሆን ነገሩ።

እርሱ አሰራሩ ብዙ የሆነ ጌታ ባሻው መንገድ ይጠብቅሃል ካሻውም ደግሞ በአንተ መጠንቀቅ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ይጋርድሃል። ካስፈለገም ምንም ጥንቃቄ ባላረክበትም ሁኔታ ይጠብቅሃል። ስለሆነም ያንተ ድርሻ በጥንቃቄ መሄድ ቀሪውን ለሠሪው መተው ይህ የበዛ ማስተዋል ነውና። ደግሞም መጠንቀቅ ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ነውና የሚበረታታ ጉዳይ ነው።

አዎ መጠንቀቅ መፍራት አይደለምና የድርሻችንን በመወጣት በጌታ ሁሉን አድራጊነት ሁላችንም ማለፍ ይሁንልን። አሜን

ምሽጌን በደም ገንብተህ
ማማዬን በፍቅር ሰርተህ
አንግቼ ያንተን ጦር ዕቃ
ኃይልህን ነፍሴ ሰንቃ
አሸነፍኩ ሆነህ ደጀኔ
ተጋድለህ ድልነሳሁ እኔ
ተሰዷል የሚያሳድደኝ
በትርና ምርኩዝ ሆነኸኝ
ማይገፉህ ፅኑ ድንበሬ
መኖርያ እናት ሀገሬ
አላውቅም ባንተ ድርድር
መውደዴ ያልፋል መቃብር

ደኅና ነው!!!



" መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው '' (ሮሜ 10፥15)

መቼም በዚህ ጊዜ መልካም ወሬ መስማት የማይፈልግ ይኖራል ብዬ አላስብም። የሰው ሁሉ ወይይት፣ የዜና አውታሩ ሰበር ዜና፣ የማህበራዊ ሚዲያ ዘገባ፣ የቴሌቪዥኖች ዳሰሳ የራዲዮኖች ድምፅ፣ የባለሙያዎች ምክር፣ የመንግስት መግለጫ .....ወዘተ  ስለ ሰሞንኛው ኮሮና ቫይረስ ነው። በሁሉም አቅጣጭ ማለት በሚቻል መልኩ የሚነገሩት አዳዲስ ክስተቶች ሁሉ የሚያሳዩት ነገሩ እየባሰ እንደሆነም ጭምር ነው።

መልካም ነገር መስማት የተጠማ ብዙ ጆሮዎች ስለመኖራቸው ማስረጃ ማቅረብ የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም። ስንት ታማሚ ጨመረ፣ ምን ያህል ሰው ሞተ፣ የት ሀገር ደረሰ፣ ብሎ የሚጠይቅ እንጂ ስንቱ አገገመ የሚል እምብዛም ነው።

ታዲያ በዚህ ጊዜ የበረታ የተጨነቁትን ማበርታት፣ መልካም ወሬ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንኳ ብንሆን ሰውን የሚያፅናና ቃላትን መጠቀም ያስፈልጋል። በተለይ ክርስቲያኖች ሁሉን ያደርግ ዘንድ ቻይ፤ ሀሳቡም ይከለከል ዘንድ የማይቻል አምላክ ዛሬ በብርታት በላይ በራማ በዙፋኑ ከዚህ ነገር በእርግጥ ያወጣናል ብለን ለምድሪቱ መፅናናት ጉልበት መሆን አለብን።

ያቺ ልጇ ሞቶባት አልጋ ላይ አስተኝታው የቤቱን በር ዘግታበት በመንገድ ላይ ሁለት ጊዜ ምን እንደሆነች ስትጠየቅ '' ደኀና ነው '' እንዳለችው ሱነማዊቷ ሴት (መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 4፥17-26) እኛም '' የደኀና ነው '' ወሬ መናገር አለብን። እግዚአብሔር አይተወንም ክንዱን ያነሳል ዓለምን ያስጨነቀ ለእርሱ ምንም ነው ማለት ይጠበቅብናል።

በያለንበት ከፀሎትም ባሻገር በዘንዳችን ያሉትን እናበርታ እግዚአብሔር ይህን ጊዜ ያለ ሞት ሀገራችንን በኢየሱስ ስም ያሳልፍልን።

ለሰው የማይቻል
ለእርሱ ይቻላል
ደኀና ይሆናል
በነበር ይቀራል
ይህም ጊዜ ያልፋል።
እያልን እንመስክር
እስኪሰማን ሀገር
ተስፋው እስኪጨምር
ክርስቲያን ተናገር
ይሰራል እግዚአብሔር።