ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌ 2፥4-5
Monday, 6 April 2020
ደኅና ነው!!!
" መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው '' (ሮሜ 10፥15)
መቼም በዚህ ጊዜ መልካም ወሬ መስማት የማይፈልግ ይኖራል ብዬ አላስብም። የሰው ሁሉ ወይይት፣ የዜና አውታሩ ሰበር ዜና፣ የማህበራዊ ሚዲያ ዘገባ፣ የቴሌቪዥኖች ዳሰሳ የራዲዮኖች ድምፅ፣ የባለሙያዎች ምክር፣ የመንግስት መግለጫ .....ወዘተ ስለ ሰሞንኛው ኮሮና ቫይረስ ነው። በሁሉም አቅጣጭ ማለት በሚቻል መልኩ የሚነገሩት አዳዲስ ክስተቶች ሁሉ የሚያሳዩት ነገሩ እየባሰ እንደሆነም ጭምር ነው።
መልካም ነገር መስማት የተጠማ ብዙ ጆሮዎች ስለመኖራቸው ማስረጃ ማቅረብ የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም። ስንት ታማሚ ጨመረ፣ ምን ያህል ሰው ሞተ፣ የት ሀገር ደረሰ፣ ብሎ የሚጠይቅ እንጂ ስንቱ አገገመ የሚል እምብዛም ነው።
ታዲያ በዚህ ጊዜ የበረታ የተጨነቁትን ማበርታት፣ መልካም ወሬ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንኳ ብንሆን ሰውን የሚያፅናና ቃላትን መጠቀም ያስፈልጋል። በተለይ ክርስቲያኖች ሁሉን ያደርግ ዘንድ ቻይ፤ ሀሳቡም ይከለከል ዘንድ የማይቻል አምላክ ዛሬ በብርታት በላይ በራማ በዙፋኑ ከዚህ ነገር በእርግጥ ያወጣናል ብለን ለምድሪቱ መፅናናት ጉልበት መሆን አለብን።
ያቺ ልጇ ሞቶባት አልጋ ላይ አስተኝታው የቤቱን በር ዘግታበት በመንገድ ላይ ሁለት ጊዜ ምን እንደሆነች ስትጠየቅ '' ደኀና ነው '' እንዳለችው ሱነማዊቷ ሴት (መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 4፥17-26) እኛም '' የደኀና ነው '' ወሬ መናገር አለብን። እግዚአብሔር አይተወንም ክንዱን ያነሳል ዓለምን ያስጨነቀ ለእርሱ ምንም ነው ማለት ይጠበቅብናል።
በያለንበት ከፀሎትም ባሻገር በዘንዳችን ያሉትን እናበርታ እግዚአብሔር ይህን ጊዜ ያለ ሞት ሀገራችንን በኢየሱስ ስም ያሳልፍልን።
ለሰው የማይቻል
ለእርሱ ይቻላል
ደኀና ይሆናል
በነበር ይቀራል
ይህም ጊዜ ያልፋል።
እያልን እንመስክር
እስኪሰማን ሀገር
ተስፋው እስኪጨምር
ክርስቲያን ተናገር
ይሰራል እግዚአብሔር።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment