Monday, 6 April 2020

መጠንቀቅ መፍራት አይደለም


" ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። " (ኢሳ 26፥20)

ሰሞኑን የሁሉም ሰው ጸሎትና ምልጃ ዓለምን እያዳረሰ ያለውን የኮሮና በሽታ መፍትሄ ከእግአብሔር ይመጣ ዘንድ ነው። በሌላ ጎን ደግሞ የዓለም ጠቢባን፣ ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ዶክተሮች ኃያላን ተብለው የሚጠሩ ሀገራት በሙሉ በጭንቅ መፍትሄ ፍለጋ ቫይረሱን እንዳይዛመትና እንዳይሰራጭ ለማድረግ ብሎም ማጥፋት የሚቻልበትን መንገድ ለማግኘት ያለ እንቅልፍ ይዳክራሉ ግን እስካሁን ምንም አላገኙም።

እኔ የማመልከው ጌታ ኢየሱስ ግን ቫይረሱ ለመስፉፉት፣ ለመባዛት እንዲሁም ለመግደል የሚመቸውንም ነገሮች ቢሆን ተጠቅሞ ሊያስወግደው እንደሚችል አምናለው። ያለ እርሱ ይህን ጊዜ ማለፍ አይቻልም።

የዚህ በሽታ መስፋፋት ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በግልና በተቋም እንዲሁም በመንግስትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ጊዜአዊ የተባሉትን የመከላከያ ዘዴዎች እየተከናወኑ ይገኛል። በመሆኑም የሚደረጉትን ጥንቃቄዎች እንደፍራቻ የተመለከቱት ሰዎች ገጥመውኛል በተለይ ክርስቲያኖች።

መፍራትና መጠንቀቅ እጅግ መቀላቀል የሌለባቸው የተለያዩ ሀሳቦች ናቸው። ሁለቱንም ሀሳቦች በልቶ ማየት ያስፈልጋል። መጽሐፍ ሲናገር "፤ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥ " (ምሳ 2፥11) ይላል ይህን ቃል የሚያምን ሁሉ በሕይወት ዘመኑ ይጠነቀቃል በማስተዋል ይራመዳል ነገር ግን የመኖሩ ህልውና በመጠንቀቁና በማስተዋሉ እንዳልሆነ በመረዳት ጭምር ማለት ነው። የሚገርመው ነገር እንደዛም ሆኖ መጠንቀቅ ግድ ነው። " በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ " (ምሳ 3፥5) ተብሎም እንደተፃፈ።

ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር  " ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። " (ማቴ 10፥28) እንዳለው አማኝ ማንን መፍራት እንዳለበት የተረዳ ይመስለኛል። አሁን እየተደረጉ ያሉት መከላከያዎች ቫይረሱን ፍራቻ ሳይሆን ከጥንቃቄ አንፃር ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። በመንግስትም ሆነ በጤና ባለሙያዎች የሚነገረውን መከላከያ (መታጠብ፣ መራራቅ ፣ መሸፈን፣ መቀመጥ/ቤት)  መተግበር የክርስቲያን ግዴትም ጭምር ነው። ጊዜውን የሚዋጅና ለሌላውም ምሳሌ የሚሆን ልበ ሙሉ ክርስቲያን ሆኖ መገኘት ያሻል።

ያለዚያማ ..... ያለዚያማ........ " እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና " (1ኛ ጢሞ 1፥19) እንዳይሆን ነገሩ።

እርሱ አሰራሩ ብዙ የሆነ ጌታ ባሻው መንገድ ይጠብቅሃል ካሻውም ደግሞ በአንተ መጠንቀቅ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ይጋርድሃል። ካስፈለገም ምንም ጥንቃቄ ባላረክበትም ሁኔታ ይጠብቅሃል። ስለሆነም ያንተ ድርሻ በጥንቃቄ መሄድ ቀሪውን ለሠሪው መተው ይህ የበዛ ማስተዋል ነውና። ደግሞም መጠንቀቅ ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ነውና የሚበረታታ ጉዳይ ነው።

አዎ መጠንቀቅ መፍራት አይደለምና የድርሻችንን በመወጣት በጌታ ሁሉን አድራጊነት ሁላችንም ማለፍ ይሁንልን። አሜን

ምሽጌን በደም ገንብተህ
ማማዬን በፍቅር ሰርተህ
አንግቼ ያንተን ጦር ዕቃ
ኃይልህን ነፍሴ ሰንቃ
አሸነፍኩ ሆነህ ደጀኔ
ተጋድለህ ድልነሳሁ እኔ
ተሰዷል የሚያሳድደኝ
በትርና ምርኩዝ ሆነኸኝ
ማይገፉህ ፅኑ ድንበሬ
መኖርያ እናት ሀገሬ
አላውቅም ባንተ ድርድር
መውደዴ ያልፋል መቃብር

No comments:

Post a Comment