አብዛኛው የዓለማችን ሀገራት ይጠቀሙበታል። አንድ ሰው አደጋ ወይም ደግሞ የቀንም ሆነ የማታ ዘራፊ ሲያጋጥመው የመጀመሪያው ስራ ቢኖር 911 መደወል ነው። ዜጋው መንግስት ያዘጋጀውን የአደጋ ጊዜ እርዳታ በመተማመን ይደውላል። መንግስትም የቀረበለትን የእርዳታ ጥሪ በመቀበል እጁን ይዘረጋል። ልክ በአደጋ ጊዜ የይድረሱልኝ ጥሪ እንደሚያሰማ እንደ አንድ ዜጋ አማኞችም በምልልሳችን ወቅት በሚያጋጥመን ፈተናና መከራ እግዚአብሔር ፈጥኖ እንዲያስመልጠን የምንደውለው መንፈሳዊ ደውል 911 አለን።
በዚህ አሰራር እጅግ በረቀቀ መንፈሳዊ ስሌት ለአማኞች በሚልቅ መልኩ በፍጥነት የሚሰራና ዛሬም ወደፊትም ህያው ሆኖ የሚቀጥል የመንፈሳዊ አደጋ ጊዜ ጥሪ ነው። እርሱም መዝሙር 91:1( 91፥1ጀምሮ )
ይህ የመዝሙር ክፍል አማኞች እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ምን ያህል ዋስትና እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። እግዚአብሔር በአደጋዎች ሁል መጠጊያችን እንደሚሆን፣ ከዚህም የተነሣ መንፈሳዊና ሥጋዊ አደጋ ሲመጣ ቀድመን የእግዚአብሔርን ጥበቃ ልንፈልግ እንድምንችል የሚረጋግጥ ስንኝ ነው።
በእግዚአብሔር ለተወደድን ይኸውም ራሳችንን ለልዑል እግዚአብሔር ፈቃድና ጥበቃ አሳልፈን ለምንሰጥ፣ በእግዚአብሔር ሀልዎት ዕለት ዕለት መኖር ለምንፈልግ እጅግ ዋስትና ይሰጣል። እንዳለው ነብዪ በእጁ ጥላ ሰወረኝ፤ የተወለወለ ፍላጻ አደረገኝ፤ በሰገባውም ውስጥ ሸሸገኝ። (ኢሳ 49፥2) በእርግጥ እግዚአብሔር የእውነት መደበቂያችን ነው። ተሸጉጠን ክፉውን የምናሳልፍበት ምሽጋችን።
የዚህን መዝሙር ስንኞች ሲያነቡ ከነችግሩና ከነመከራው አንብቦ የሚጨርስ ማነው? ስትጀምር የነበረው አደጋ ወይም መከራ ሁሉ ቁጥር አንድ (ቁ1) ጋር አብቅቶ ሌላ ርዕስ ውስጥ ትገባላችሁ። እስኪ ከፋፍለን የእግዚአብሔርን ጥበቃ እንቃኘው
1) መዝሙሩ 91፥1-2 ( ከአደጋ መውጫ አንድ)
'' በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።እግዚአብሔርን። አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ። ''
ከሁሉ በላይ የሆነውንና የኃይሉን አምላክ መጠጊያው አድርጎ የሚኖር ሰው የሕይወቱ ዋስትና የሚያስተማምን በመሆኑ እግዚአብሔር መጠጊያዬና ምሽጌ የምተማመንበት ፈጣሪዬም ነው ብሎ ይመሰክራል።
=} ምሳሌ:- አንድ ህፃን አባቱ እቅፍ ውስጥ ሆኖ ወደ ላይ እየወረወረ ሲያጫውተው ከሚተማመነው በላይ አደጋ ውስጥ ሆነን በእግዚአብሔር መተማመን። ይህንንም በእምነት መመስክር ያጋጠመን አደጋ ከእኛ ዘንድ ያሸሸዋል።
2) መዝሙር 91፥3-4 (ከአደጋ መውጫ ሁለት)
'' እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። ''
እግዚአብሔር ሕዝቡን ከጠላት ይጠብቃል፣ በላባዎቹ ይጋርዳቸዋል፣ ጋሻ እና መከታ ይሆናቸዋል። ለእርሱ የአደጋውም ሆነ የችግሩ ግዝፈት እኛን ከመጠበቅ አያስቀረውም።
=} አባባል:- ለእግዚአብሔር የችግርህን መጠን ከምትነግረው ይልቅ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለችግርህ ንገረው። የተባለውም ለዚህ ነው።
3) መዝሙር 91፥5-6 (ከአደጋ መውጫ ሦስት)
'' ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። ''
የእግዚአብሔር እንክብካቤ ጽኑና በቂ ነው ምክንያቱም ጥበቃው የተመሰረተው በማንነቱ ላይ ስለሆነ። እርሱ ሲጠብቅ ቀን አይል ሌሊት አይል ሁልጊዜ ነው። በጊዜ አይወሰን በስፍራም እንዲሁ በመዞር የተደረገ ጥላ የለበትምና። የእግዚአብሔር ጥበቃ በቀንና በሌሊት እንደ ሆነ ተፈጥሮአዊ በሆኑ ምክንያቶች ከሚመጣ ፍርሀትና ድንጋጤ ይጠብቀናል።
=} ሰባኪው:- እንኳን ሌሊት ተኝተን አይደለም ቆመንም አይተን ከምናልፈው አደጋ ሳናየው ጠብቆን ያሳለፈን እጅግ ብዙ ነው። ተውት ያስተዋልነውን!!!
4) መዝሙር 91፥7 (ከአደጋ መውጫ አራት)
'' በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። ''
እርሱ በምድር ላይ በሚሆኑ ነገሮች ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን ስላለው ለጥበቃው ወሰን የለውም። እንክብካቤውና ጥበቃው የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለማሳየት ሺህ እና አሥር ሺህ በማለት ይገልፀዋል። እግዚአብሔርን የሚያልፍ ችግር የለም።
=} መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ:- ሕዝቅያስ እንዳጽናናቸው
(መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 32፥7-8 ) ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው ብሎ አጸናናቸው። ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናና።
5) መዝሙር 91፥8 (ከአደጋ ጊዜ መውጫ አምስት)
'' በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ብድራት ታያለህ። ''
ጻድቃን የእግዚአብሔርን ማዳን በእምነት ዐይን ማየታቸው ይበለጥ እንዲበረቱ ያደርጋቸዋል እግዚአብሔር ጻድቃንን ለመጠበቅና ለመባረክ ቃል ገብቷል ጻድቃን የእግዚአብሔርን ፍትሕና ታማኝነት እንዲሁም የክፉዎችን መቀጣት በዐይናቸው ይመለከታሉ።
=} አመለካከት:- ሰው በሚያየው ሳይሆን በሚያምነው ይኖራልና።
6) መዝሙር 91፥9-10(የአደጋ መውጫ ስድስት)
'' አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፤ ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። ''
ልዑሉን መጠጊያችን በማድረግ የጥበብን መንገድ እንድንከተል ያበረታታል እርሱ መጠጊያችን ነው በምድር ላይ የሚሆነው ማንኛውም ነገር በእርሱ ቁጥጥር ሥር ነው ክፉ ነገር ወይም መቅሠፍት ቢሆን ያል እርሱ ፈቃድ አይሆንምና።
=} ሂሳባዊ ቀመር:- ይጠጌ አይነኬ (asymptote)፤ ቅርብ ቢመስልህም፣ ሊነካ የቀረበ ቢመስልም ሁሉን ማድረግ በሚቻለው ሀሳቡም ይከለከል ዘንድ ከቶ በማይቸለው ተአምር አድራጊነት ሳይነካህ ያልፋል። ይታከክሃል፣ ይቀርብሃል አይደርስብህም፣ ይመጣብሃል አያገኝህም።
7) መዝሙር 91፥11-13( ከአደጋ ጊዜ መውጫ ሰባት)
'' በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። ''
እግዚአብሔር እኛን አማኞችን በምንሄድበት ሁሉ ይጠብቁን ዘንድ መላእክቱን ያዛቸዋል። መላእክቱ እኛን ከአደጋ ለማስመለጥ እንዲጠብቁን ዘወትር እንዲታደጉን በተጠንቀቅ በዙሪያችን አሉ። እግዚአብሔር በልጆቹ ላይ ብዙ ነገር እንዲደርስ ሊፈቅድ ይችላል ይሁንና አንድም ኅይል ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጭ አንዳልሆነ ያውቃሉ።
=} እንቆቅልህ:- እነሱ የሚያዩን እኛ የማናያቸው ዘወትር አብረውን ያሉ የእግዚአብሔር ታዛዦች። ካላወቃችሁት ሀገር አልሰጣችሁም ሰማይ ግን እንካኅሁ።
8) መዝሙር 91፥14(የአደጋ ጊዜ መውጫ ስምነት)
'' በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ። ''
እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱት እና ስሙም ለሚያውቁ ሁሉ የማዳኑን ንግግር ያበሰረበት ክፍል ነው። መውደድ የሚለው ቃል እግዚአብሔርን ከልብ መናፈቅንና መሻትን ይሆንላቸዋል።
=} የጌታ ቃል:- ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ በታች እንደምትሰበሰብ እንዴት ይልቅ እርሱ እንደሚጋርደን።
9) መዝሙር 91፥15( የአደጋ ጊዜ መውጫ ዘጠኝ)
'' ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ አከብረውማለሁ። ''
ይህ ቃል የአማኝ የድምፅ ብክነት የሚባል ነገር እንደሌለ ያሳያል። ሲጣራ ደመና አይከለክለውም፣ የፀሐይ ግርዶሽ አይዘውም፣ ንፋስ አይወስደውም፣ ዝናብ አይመልሰውም። አቤት የሚል ብቻ ሳይሆን በመከራ የማይተወን አብሮን የሚሆን ደግሞም የሚያድነን ጌታ አለ።
=} መዝሙር ዘ ማስተካከል:-
ደጅ ጠናሁ ቆይቼ ኪዳነ ምህረትን
ተፅናናሁኝ ረሳው ሀዘኔንን
ጌታ ኢየሱስ የሕይወት መድህን
ዋስትዬ መላው ዘመኔን
10) መዝሙር 91፥16(የአደጋ ጊዜ መውጫ)
'' ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ። ''
ሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ ሲገረም ''እንግዲህ ምን እንላለን'' ይላል ደግሞስ ምንስ ይባላል እኔም ከምናገር እጅህን አፍህ ላይ ጫን ይለኛል። ይህ ሁሉ ጥበቃ ለእኔና ለእናንተ ነው። እውን ከዚህ የቀረበ ደግሞም ህያው የሆነ ነገር ምን አለ?
=}መዝሙር
እረ ስንቱ ስንቱ ታለፈ
ጌታዬ እየደገፈ።
ወዳጆቼ የትኛውም አደጋ ሲያጋጥማችሁ
ደውል/ደውይ/ደውሉ ወደ መዝሙር 911(መዝ 91፥1ጀምሮ)
በእርግጥም መውጣት ይሆንላችኃል።
No comments:
Post a Comment