እግዚአብሔር እኛን ከፈጠረበት አንዱ ምክንያት ከእርሱ ጋር ህብረት እንድናደርግ ነው። ለዚህም ነው '' በመልካችን እንደ ምሳሌአችን '' እንፍጠር (ዘፍ 1፥26) ያለው። ከእርሱ ጋር ብቻ ሳይሆን ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድም መልካም እንዳልሆነ በመናገር አጋር እንደሚያስፈልገው ስላወቀ የሚመቸውን ረዳት ፈጠረለት። ሰው ብቸኛ መሆን እንደሌለበት ከፍጥረቱ መረዳት ይቻላል።
በመፅሐፍ እንደምናነበው ሰው ብቻውን ሲሆን መልካም ያልነው በኅብረት ሲሆን ደግሞ በዛው ልክ መልካምና ያማረ ነው። እንዲህ ተብሎም እንደተፃፈ
'' ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። '' (መዝ 133፥1-3)
አሮን በበረሃ ጉዞ ላይ በሊቀካህንነት ሲሾም የበረሀው ንዳድ ያደረቀውን በራሱ ላይ የፈሰሰው ዘይት ራሱን እንዳረሰረሰው መልካም፣ በበረሀ ያለው አድካሚ ጉዞ አልቦ የሰውነትን ጠረን እንደሚቀየር በልብሰ ተክህኖውም ላይ ያማረ ልዩና ጥሩ መአዛ ያለው ሽቱ እንደተረጨው መልካም፣ የበረሀ ንዳዱ ከፍተኛ የውሃ ጥምን ባመጣ ጊዜ ከበረዶሃማ ተራራ ጫፍ ላይ ጥምን የሚያረካ ቀዝቃዛ ውሃ እንደሚወርድ መልካም የወንድሞ በህብረት መሆን እጅግ መልካም ነው።
በሌሎች መሰብሰብ ውስጥ የማይገኝ በዚህ በወንድሞች በኅብረት መቀመጥ ብቻ ለዘላለም የታዘዘ በረከትና ሕይወት እግዚአብሔር አዟል። ይህ ደግሞ እንዴት ያለ መልካም ነገር መሆኑ ይበልጥ ያሰረዳል።
እንደ ልቡ ሀሳብና ምክር መቀመጥ ይሁንልን።
No comments:
Post a Comment