ኢየሱስ የሚለው ስም በየመንገዱ ሲጠራ ደስ የማይላቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ መናገር የሚከብድ ነገር አይደለም። በአብዛኛው ሰዎች ሞቅ ባለ ጨዋታቸው ይሁን በስራ ጊዜአቸው ሊሰሙት የማይፈልጉት ስም ጥራ ብትሉኝ ይህን ስም ብቻ ነው።
በሀገራችን በተለያዩ ስፍራዎች ከወዳጆቻችን ጋር ተሰብስበን የማውራት ልማድ አለን። በእነዚህ መሰል ጊዜአት የማይነሳ ርዕሰ ጉዳይ አይኖርም ብንል ማጋነን አይሆንም። ፖለቲካ ቢሉ ሃይማኖት፣ ቅልድ ቢሉ ፌዝ፣ የስራ መቀዝቀዝ ቢሉ የኑሮ ውድነት፣ ሽንኩርት ቢሉ ዘይት፣ ዘፋኝ ቢሉ ተዋናይ፣ ደራሲ ቢሉ ፈላስፋ፣ ሜሲ ቢሉ ሮናልዶ፣ አርሴናል ቢሉ ማንቼ፣ ሀይሌ ቢሉ ደራርቱ፣ የሃይማኖት አባት ቢሉ ሰይጣን ጭምር ብዙ አልባሌ ነገሮች............ ብቻ የማይወራ የለም። ሁሉም ጫወታ ይወዳል ጆሮውን ቀስሮ ያዳምጣል የሚያስቅ ያስቀዋል።
በዚህ መሀል ድንገት ስለ ኢየሱስ ከተነሳ ወይም አንድ ሰው በአቅራቢያ ሆኖ ይህን ስም እየጠራ ሰዎች ወደ እግዚብሔር እንዲቀርቡ የማንቂያ ደውል ለማሰማት ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ ብቸኛ አዳኝነቱን (መድሃኒትነቱን)፣ እውነተኝነቱን፣ መንገድነቱን፣ ተስፋነቱን፣ አጽናኝነቱን መናገር ሲጀምር አታስዋሹኝ ብዙ ፊቶች መቀያየር ይጀምራሉ። ከፊል ፊቶች እንደ ቲማቲም ይቀላሉ ከፊሉ ደግሞ ጥርሱን ያፏጫል አንዳንዱም ሊማታ ይዳዳውል።
ስለቀልድና ዋዛ ፈዛዛው ቦታ ሳይመርጥ ሲያውካካና ሲያሽካካ የነበረ ስለ ኢየሱስ መስማት ቦታ ያጡና '' ወንጌል ቦታ አለው '' በማለት ይደነፋሉ። ጭራሽ ጫወታችንን አታበላሽ ብለው የሚያጉረመርሙም አይጠፉም። ስለፖለቲካ ፣ ፌዝ፣ እርባና ስለሌለው ቀልድና ስለብልግና ማውራት እንደጥሩ ጫወታ ተቆጥሮ ስለ ኢየሱስ መስማት ግን ጫወታን እንደማበላሸት ሆኖ የሚቆጠርባቸው ጊዜአት ብዙ ናቸው።
ዘፈንና ቀልዱ፣ ቧልትና ፌዙ ሲነገር ሁሉ ያለምንም ልዩነት አንድ ሆነው ሲስቁና ሲፈነድቁ እንዳልነበር '' ኢየሱስ '' የሚለው ስም ሲጠራ የሚበሳጩበት ምክንያት ምንድነው? ዛሬም ድረስ የሚያሳዝነኝ ጥያቄ ነው። ስለ ምድራዊ ነገር ማውራት ለሁሉም የተፈቀ ተግባር ለሰው ልጆች ሁሉ ስለሞተው ስለ ኢየሱስ ብቸኛ መድሃኒትነት መናገር ደግሞ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተሰጠ ስጦታ ሆኖ መመስከርን የሚያስወቅስ ተግባር ሆኖ የሚቆጠርበት ምክንያት መኖር ይበልጥ ያሳዝነኛል። በምድራዊ ጉዳይ ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር ስለ ኢየሱስ ሲሆን ግን ራሱን ያገላል።
ብዙ ኢትዮጵያዊያን ወንጌል በመንገድ ተመስክሮልን እንደተቀበልነው ይስማማሉ ነገር ግን በመንገድ ላይ ከተነገረን ወንጌል ይልቅ ወንጌሉን ስለ ተቀበለው ሰው ማቀንቀን ይቀናናል። ስለ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በስፋት ይነገራል ግን እንዴት ባለ ሁኔታ እንደተቀበለው ልብ የሚል አናሳ ነው። ኢትዮያዊው ጃንደረባ ፊልጶስ ስለ ኢየሱስ በመንገድ ከሰበከለት በኃላ የነበረው ምላሽ ሁለት ነው ጥምቀትን መሻቱና በልቡ ደስ ተሰኝቶ መመለሱ እንጂ ስፍራው አይደለም፣ የእናትና አባቴን ሃይማኖቴ ተከትዬ ከኢትዮጵያ ኢየሩሳሌም ድረስ ለስግደት ያስመጣኝን፣ ተራራ የወጣሁበትን፣ ዳገት ቁልቁለቱን የወረድኩበትን፣ ወንዝ የተሻገርከበትን፣ ይህን ምድር የረገጥኩበትን፣ ታላቅ የበረከት ጉዞ አድርጌ ከመመለስ ባለፈ የእናንተን ኢየሱስን ለመስማት አልመጣሁም ብሎ ፊት አልነሳም። ይልቅስ ለመስማት እጅጉን ጓጓ።
ስለ ኢየሱስ መስማት ደስ የሚያሰኝ እንጂ የሚያስኮርፍም የሚያሳፍርም አይደለም። በመፅሐፍ እንደተፃፈ የኤማሁስ መንገደኞችን ብንመለከት ስለ ኢየሱስ ሲሰሙ የተሰማቸውን እኛም በዘመናችን ሊሰማን ያስፈልጋል።
" እርስ በርሳቸውም። በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ። "
(የሉቃስ ወንጌል 24: 32)
ከጥቂት ጊዜአት ጀምሮ ብዙ ሰው በሚያልፍባቸው ስፍራዎች በተለይ በገበያ አካቢዎች ቀልቤን የሳበው ነገር ቢኖር '' ዘራ መድሃኒት '' እየተባለ ስለሚሸጠው የአይጥና የበረሮ መርዝ ነው። የዚህ መድሃኒት ማስታወቂያን ልብ ብላችሁ ካዳመጣችሁት '' ታላቅ የምስራች '' ብሎ ነው የሚጀምረው እውነት የቱ መድሃኒት ነው ታላቅ የምስራች?
የማያናድደው? ቦታ ማይገድበው? የማያበሳጨው? የማያስቆጣው?
እኔ እያወራውት ያለሁት ከኃጢአት የሚያድን እርሱን ብቻ በማመን የዘላለም ሕይወት ስለሚያስገኘው ኢየሱስ ነው። ስለ ዘራ መድሃኒት ሲሰማ ያልተሸማቀቀው ጆሮ ኢየሱስ ስለሚባለው መድሃኒት ጆሮውን የሚያከው ለምንደነው? እስኪ መልሱልኝ?
የሰማይ ማስተዋል በኢየሱስ ለኢትዮጵያዊያን ይብዛ አሜን።
No comments:
Post a Comment