Thursday, 19 December 2019

የፍቅር ሽፋኑ


ለሰው ልጅ ለኑሮው እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ውስጥ በዋነኛነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ልብስና መጠለያ ናቸው። ሁለቱም የሰውን ልጅ ከተፈጥሮና ከእይታ የሚከልሉ ወሳኝ ነገሮች ናቸው። እንደው በአጠቃላይ እኛ ሰዎች ስንባል፤ ካልተሸፈንን መኖር እንደማንችል ከሚያስፈልገን ነገሮች መረዳት እንችላልን። ህልውናችንም የሚቀጥለው በመሸፈን ውስጥ ነው ብንል ይቀላል። ማንም ከእንቅልፉ እንደተነሳ ራቁቱን ወደ ውጭ አይወጣም ወይም መሸብኝ ብሎ መንገድ ዳር አይተኛም። 

የመጀመሪያ ፍጥረታት የሆኑት አዳምና ሄዋን ከተላለፉ በኃላ በመጀመሪያ ያደረጉት ነገር ቢኖር ራሳቸውን መሸፈን ነበር። በበለስ ቅጠል ግልድም አሰሩ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዘመናችን ጅንስ እስከምንለው ድረስ ሁሉም ሰውነቱን በመሸፈን ይኖራል። እግዚአብሔር ግን መልካም ነውና የሰው ልጅ ያገለደመው ቅጠል ቶሎ የሚደርቅ በመሆኑ የልጁን መሰዋት ምሳሌ በማድረግ ዘላቂውን ቁርበት አለበሳቸው። 

ይህ በሥጋ መሸፈን ዛሬም የሚያስፈልግ ቢሆንም እንኳ አዳምና ሄዋን ያደረጉት ቅጠል የሰውን ጽድቅ ያሳያል። እንደ ጠዋት ጤዛ ታይቶ የሚጠፋ፣ በቶሎ የሚደርቅ፣ አለ ሲባል የሌለ ነው። ሁሉቱም ይህን ሲያደርጉ መንፈሳዊ ስሌት የሌለበት ሥጋን ብቻ ያተኮረ መፍትሄ ነበር የወሰዱት እግዚአብሔር ግን ጉዳዩን ቀየረው እንጂ። ቁርበት የእግዚአሔርን ጽድቅ ሲወክል  ዘላቂነትንም የሚያሳይና መሸፈን ለሚያስፈልገው ማንነት በመስዋህትነት የሚቀርብ ሥጦታ እንደሆነ መረዳት እንችላልን። 

ከብሉይ ኪዳን የጽድቅ ስራዎች ተብለው ከሚዘረዘሩት ውስጥ አንዱ ማጋለጥ ነው። ሕጉ በሚያዘው መጠን መጋለጥ ያለበት ነገር፣ መውጣት ያለበት፣ መነገር ያለበት ወሬ ያለ ርእራሄ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ዋጋ ቢያስከፍል ጉዳዩ ለእስራኤል ሕዝብ ይጋለጣል። እንዲህ ተብሎ እንደተፃፈ ማንም ሌሎች አማልክት እናምልክ ብሎ ቢያስትህ፥ እሺ አትበለው፥ አትስማውም፤ ዓይንህም አይራራለት፥ አትማረውም፥ አትሸሽገውም፤ ነገር ግን ፈጽመህ ግደለው፤ (ዘዳ 13፥6-10)

ለአብነት ያህል ሌላ ከዚሁ ከዘዳግም መፅሐፍ አንድ ምሳሌ እንውሰድ:- 

ማንም ሰው ለአባቱ ቃልና ለእናቱ ቃል የማይታዘዝ ቢቀጡትም የማይሰማቸው እልከኛና ዓመፀኛ ልጅ ቢኖረው፥ አባቱና እናቱ ይዘው ወደ ከተማው ሽማግሌዎች ወደሚኖሩበትም ስፍራ በር ያምጡት፤ የከተማውንም ሽማግሌዎች። ይህ ልጃችን እልከኛና ዓመፀኛ ነው፥ ለቃላችንም አይታዘዝም ስስታምና ሰካራም ነው ይበሉአቸው። የከተማውም ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፤ እንዲህም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታርቃለህ፥ እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ። (ዘዳ 21፥18-21)

ሕጉ የሚያሳየው ምን ያህል ማጋለጥ ዋጋ ያለው ነገር እንደሆነ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን እንኳ ለሞት አሳልፈው እስኪሰጡ ድረስ የሚያሰጨክን የማጋለጥ ስራ የታዘዙበት ሕግ ነው። ነገር ግን ማጋለጥ ብቻ እውነት አይደለም ይልቁንስ መሸፈን በሙላት የሚሰራ እግዚአብሔር ያዘጋጀው የአዲስ ኪዳን ጽድቅ ነው። አዳምንና ሄዋንን በቁርበት የሸፈነው እርሱ የዓለምን ኃጢአት ሁሉ ውድ ልጁን ኢየሱስን በመስጠት ከድኖታል። 

መፅሐፍ እንደሚል "፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። " (ዮሐ 3፥16) ይህ መውደድ ነው የዓለም ኃጢአት የሸፈነው። የሰው ልጅ የኃጢአቱ ብዛት ግንባሩ ላይ ቢፃፍ አይደለም ከእግዚአብሔር ፊት ሊቆም፤ እርስ በራሳችን እንኳ ለመተያየት ባልደፈርን ነበር። መወደድ ያመጣው መሸፈን ማለት ይህ ነው። እግዚአብሔር ስሙ ይባረክ በባሕሪው ሸፋኝ ነው። እንዲህ ተብሎ እንደተፃፈ " የእግዚአብሔር ክብር ነገርን መሰወር ነው፤ የነገሥታት ክብር ግን ነገርን መመርመር ነው። " (ምሳ 25፥2) 

መሸፈን የኢዲስ ኪዳን ጽድቅ ነው። ክርስቲያን ከክርስቲያን ጋር በሚኖረው ግንኙነት ውስጥ አንዱ ቢበድለው በመጀመሪያ ብቻውን ያናግረው የተባለውም መሸፈን ስላለብን ነው። በማጋለጥ ውስጥ ብዙ ትርፍ አለው ለዚህም ቀዱሱ መፅሐፍ ሲመሰክር '' ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥ ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ። '' (ያዕ 5፥19-20)

ዛሬ ላይ ሰው ለሰው የማይተኛበት ዘመን ላይ ነን። በምዕራባዊያን ዘንድ እንደተለመደው የሰውን ገመና ፈልፍሎ እንደሚያወጣው ፓፓራዚ የሰውን ምስጢር መጠበቅ አቅቶን ጭራሽ ገመና ፈላጊዎች ሆነናል። ጌታ ኢየሱስ ማስተዋል ያብዛልን። ስለ ሰው ድካም መቁጠር አቁመን የተተወልልን በደላችንን እያሰብን፣ የቀረልንን ቁጣ እያሰላሰልን አመስጋኝ እንድንሆንና አንድ ሰው በድካም ውስጥ ብናየው ያ ሰው እንዲመለሰ የፀሎት ርዕስ እንዲሆነን እመክራለው። 

" ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። " (1ኛ ጴጥ 4፥8) እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን '' ከሁሉ በፊት '' የሚለውን ኃይለ ቃል ነው። አዎ ከምንም በፊት ፍቅር ይቀድማል። በሌላ ስፍራ እንደምናነበው ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ እንደሚል ለየትኛውም የመንፈሳዊ ሕይወት እንቅስቃሴ ይህ ፍቅር መሰረት ነው። ይህ ፍቅር ሲኖረን ነው የወዳጆቻችንን ሰንፍና የምንሸፍነው። ከላይ እንዳነበብነው ፍቅር የኃጢአትን ብዛት የመሸፈን አቅምና ጉልበት አለው። ስለተሸፈነልን እንሸፍን። በመሸፈን ውስጥ እጅግ ብዙ ትርፍ አለና። 

ጌታ ኢየሱስ በቀራኒዮ መስቀል ላይ ያፈሰሰው ደም ከፍቅር የተነሳ ነው። " ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። " (ሮሜ 5፥8) የዚህን የክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን ለማወቅ እንበረቱ ዘንድ ዓለምን የሞላት የእርሱ ጸጋ ሁላችንንም ይርዳን አሜን። 

በየትኛውም ስፍራ በማንኛውም ሰዓት ሁሉም ሰው ማየት ያለበት ይህን ፍቅር ነው። ዓለምን በደሙ የከደነ የኢየሱስ ደም ዛሬም ትኩስ ነው ከኃጢአት ያነፃል፣ በደልን ይሸፍናል፣ አዲስ ሰው ያደርጋል፣ ለዘላለም ያድናል።

No comments:

Post a Comment