Tuesday, 17 September 2019

ታላቅ መዳን


ሰው ከብዙ ነገር ሊድን ይችላል ነገር ግን በመፅሐፍ ቅዱሳችን እንደምናነበው ዘላለማዊ መዳንን የሚያክል ታላቅ መዳን የለም። ይህ መዳን አጠቃላይ የክርስትናን እምነት ማዕከል ያደረገና ከሞት ወደ ዘላለማዊ የሕይወት አቅጣጫ ያሻገረም ጉዳይ ነው። ታላቅነቱም በጊዜ የተገደበ ስላልሆነ (ህያው በመሆኑ) እና ራሱ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው ወይም ያደረገው ምህረት በመሆኑ ታላቅ አሰኝቶታል።

የሰው ልጅ ይህ ታላቅ መዳን ለምን አስፈለገው? ያሉ እንደሆነ:- መፅሐፍ ቅዱስ ሲናገር ሰው ሁሉ ኋጢአተኛ እንደሆነ ነው። ኋጢአተኝነቱም የመጣው በአዳም ኋጢአተኛ ማንነት ስለተወለድን እንደ ሆነ ሮሜ 5፥12 ይናገራል። ስለሆነም አዳም እግዚአብሔር ያዘዘውን ትዕዛዝ በተላለፈ ጊዜ ኋጢአት ወደ ዓለም ከመግባቱም ባሻገር ባለመታዘዝ ጠንቅ እግዚአብሔር የፈረደው የሞት ፍርድ ለሰው ሁሉ ሊደርስ ችሏል። እስኪ ሰለ ሰው ኋጢአተኝነት መፅሐፍ ቅዱስ ምን ይላል የሚለውን በጥቂቱ ተመልከቱ:-                                       

ብሉይ (አሮጌው) ኪዳን

=}} "ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። " (ኢሳ 64፥6)

=}} "ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም። " (መዝ 14፥3)       

አዲስ ኪዳን           
                                                                               
=}} "ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል " (ሮሜ 3፥23)           
                                                   
=}} '' ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ (ሮሜ 3፥11-12)

በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። ''

በነዚህ የመፅሐፍ ቅዱስ ንባቦች መሰረት የሰው ዘር በሙሉ በኋጢአት ውስጥ እንደሆነና በራሱ ኋጢአት ከሚያስከትለው የሞት ፍርድ (ሮሜ 6፥23 የኋጢአት ደሞዝ ሞት ነው) ሊያድን ባለመቻሉ የእግዚአብሔር ማዳን አስፈልጎታል። የሰው ዘር በአጠቃላይ ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ያለን ሰው ሁሉ ከነበረበት መሰረታዊ ችግር እንዲድን በምህረቱ ብዛት ባለጠጋ የሆነው አባታችን እግዚአብሔር አንድ የመዳን መንገድ አዘጋጀ እርሱም አንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዮሐ 14፥6)

ኢየሱስ                             
                                                               
ከስሙ ትርጉም ብንነሳ ኢየሱስ ማለት ሕዝቡን ከኋጢአታቸው የሚያድን ማለት ነው (ማቴ 1፥23)። ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ በመታዘዝ እስከ ሞት ድረስ ዋጋ በመክፈል የሰውን ልጅ ከነበረበት ኩነኔ ነፃ አድርጎአል። እስኪ እነዚህ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንብቡ 

" የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና"
(ሉቃ19፥10)                                                                                                " በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ" (ዮሐ 1፥29)                                                                                                           " ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው " (1ኛጢሞ1፥15)                                                                                            " ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ " (1ኛ ጴጥ 2፥24)           

እነዚህ ጥቅሶች ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር በሙሉ የማዳን ዓላማ ይዞ ከሰማይ እንደመጣ ያሳያሉ። በመሆኑም እርሱ ኋጢአት ስለሌለበት ስለእኛ መሞትና ከኋጢአታችንም ማዳን ተችሎታል። ይህን የማዳን ስራ በሰማይም ሆነ በምድር ከጌታችን ከመድሃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር የተቻለውም የሚቻለውም የለም። የእግዚአብሔር ቃል በሐዋርያት ሥራ 4: 12 ተፅፎ እንደምናነበው "፤ መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና። "                 
                                                                   
ይህ መዳን እግዚአብሔር አባታችን እንደባለጠግነቱ መጠን እንዲያው በፀጋው ያደለን ነፃ ስጦታችን ነው። በመስራት ያላይደለ በመቀበል የሚገኝ መዳን። ለዚህም አሁንም መፅሐፍ ቅዱሳችን ያረጋግጥልናል። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም። (ኤፌ 2፥4-9)

እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው። (ቲቶ 3፥4-7)

ኢየሱስ ከእያንዳንዳችን የጎደለብንን የእግዚአብሔር ክብር ደግሞም ከኋጢአታችን የተነሳ ተላልፎብን ከነበረው ዘላለማዊ የሞት ፍርድ (ሮሜ 6፥23) ውስጥ ለሚኖር ሁሉ ይህን የኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነት መስማት ታላቅ የምስራች ነው።

ይህን የምታነቡ ወንድምና እህቶች የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ያደረገልንን ይህን ታላቅ መዳን ቸል ብንል ከሞት ፍርድ እንዴት እናመልጣለን? አይምሰላችሁ እንዴትም አናመልጥም። ይልቅስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በፃፈው መልእከቱ ላይ " እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ " (ኤፌ 1፥13) እንዳለው ኢየሱስን የሕይወታችን መድሃኒት በማድረግና እርሱን በማመን በሚገኝ ቅድስና ቀሪውን ዘመናችሁን በእርሱ ለመኖር አሁኑኑ ይወስኑ።

ይህንንም ለማድረግ ቀጠሮ አትያዙ ለመልካም ነገር ቀጠሮ አያስፈልገውምና አሁኑኑ ወስኑ። መፅሐፍ ቅዱስ '' እነሆ የተወደደ ሰዓት አሁን ነው እነሆ የመዳንም ቀን አሁን ነው '' ይላልና (2ኛ ቆሮ 6፥2) " በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። " (ዮሐ 3፥16) ተብሎም እንደተፃፈ እግዚአብሔር ያዘጋጀውን ዘላለማዊ መፍትሄ ልጁን ኢየሱስን በማመንና ራስህን ወይም ራስሽን በንሰሐ መንፈስ በክርስቶስ ደም በመታጠብ ብቻ ወደሚገኝ ቅድስና በመምጣት ክፉ ከሆነው ከዚህ ዓለም ድነው የዘላለም ሕይወት ያገኙ ዘንድ በፀሎት መንፈስ ይህ ተፃፈ።

No comments:

Post a Comment