Thursday, 12 September 2019

ከየቤታችሁ አንፃር

ነህምያ የፈረሰውን የእስራኤልን ቅጥር ሲያድስ ከፈረሱት በሮች ውስጥ የበጉ በር ተብሎ ከሚጠራው እንደ ጀመረ መፅሐፍ ቅዱሳችን ይናገራል (መፅሐፈ ነህምያ 3፥1)። በጣም የሚደንቀው ግን የእስራኤል ቅጥር ማደስ ያለቀውም በበጉ በር ነው(መፅሐፈ ነህምያ 3፥32) ። በበጉ በር ተጀምሮ በበጉ በር ያለቀ ስራ ለእኛ ለክርስቲያኖች ትልቅ መልእክት አለው። በሕይወታችን እግዚአብሔር ዘመን ሲጨምርልን በክርስቶስ ኢየሱስ ፀጋ ተቀብለን ደግሞም በእርሱ ላይ ባለን እምነት በመፅናት መደምደም እንዳለብን ይነግረናል።

እኔን እጅግ የሚገርመኝ አንድ ነገር አለ። ነህምያ የፈረሰውን ቅጥር እንዲሰራ ከተጠቀመባቸው መንገዶች አንዱ ከየቤታችው አንፃር የነበሩትን የፈረሱትን ቅጥር ወይም በር ማደስ ነበር (መፅሐፈ ነህምያ 3፥28)። ሰው ከፊቱ የተደቀነበትን ችግር መፍታት ከቻለ የእርሱ ችግር ሌላ ሰው ጋር ጉዳት እንዳይደርስ ያደርጋል። በጨረስነው ዓመት በአእምሮዬ የሚመላለስ አቋም አለ። " የድርሻህን ተወጣ " (Play Your Part) የሚል።

ሁሉም ክርስቲያን በአገልግሎት የድርሻውን ቢወጣ ምን ያህል ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ሳስብ እደነቃለው። አንዱ ከሌላው ሳይጠብቅ በራሱ ማድረግ ያለበትን ቢያደርግ ችግር የምንለውን ነገር በቀላሉ ማለፍ እንችላለን። ከአገልግሎት አንፃር ክርስቲያን የሚሞተው ከሰው የጠበቀ ቀን ነው የሚል ፅሁፍ ያነበብኩት ይህን ለማለት የፈለገ ይመስለኛል።

በዚህ ምድሪቱን በከደነው በጌታ ኢየሱስ ፀጋ የተቀበልነው 2012 ዓመተ ምህረት ጌታን በታማኝነት በማገልገል በየአንፃራችን ያለውን ድርሻችንን የምንወጣበት ዓመት እንዲሆንልንና በእርሱ ላይ ባለን እምነት እንድንፀና ፀጋው ይርዳን። ከሰው የምንጠብቅበት ሳይሆን የድርሻችንን የምንወጣበት ደግሞም ከመገልገል አልፈን የምናገለግልበትና የምንዘረጋበት ዓመት ይሁንልን።

እስራኤላዊያን በነህምያ አስተባባሪነት እያንዳንዳቸው በቤታቸው አንፃር ያለውን ቅጥር እንዳደሱ፥ እያንዳንዱም በቅጥሩ ሥራላይ ድርሻ እንዳላቸው ሁሉ ዛሬም በአዲስ ኪዳን የምንገኝ አማኞች ሁላችን ደግሞም የክርስቶስ አካልብልቶች እንደመሆናችን መጠን በ1ኛ ቆሮንጦስ በምዕራፍ 12 በቁጥር 14 - 31 ላይ እንደተገለፀው ሁላችንም በአካሉ ውስጥ እኛ ብቻ ልንወጣው ወይም ልናደርገው የተገባ ኃላፊነትና ሥራአለን። የማያስፈልግ የአካል ክፍል እንደሌለ ሁሉ የማያስፈልግ (ሥራ የሌለው) ክርስቲያን በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥየለም። እያንዳንዳችን በአንፃራችን ያለውን የእግዚአብሔር ሥራ በትጋት እየሰራን የምንኖርበት ዘመን እንዲሆን እርሱ ይርዳን።

እንደ ነህምያበቅንዓት፥ በሙሉ መሰጠትና ቁርጠኝነት በክርስቶስ የተፈጠርንለትን መልካሙን ሥራ ለማድረግ እኛም ፈቃዳችንን ለፈቃዱበማስገዛት፥ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም፥ ማድረግንም በእኛ የሚሰራ አምላክ በእኛ የጀመረውን መልካም ሥራእርሱ ራሱ ይፈፅመዋልና እርሱ ላይ በመደገፍ ማገልገል ይሁንልን።

የተወደደው ዓመታችን በኢየሱስ ስም ይባረከ።

No comments:

Post a Comment