Monday, 14 October 2019

የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል

የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል

<< ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። >> (ፊልጵ 4፥11-12)

ይህን ሲል ሐዋርያው ሁሉ ነገር ቢኖረው እንደማይጨመርለት ምንም ባይኖረው አንዳች እንደማይቀንስበት ከማወቅ ባለፈ ተምሯል። እርሱ በብልፅግና እንደማይበረታ በድህነት እንደማይደክም ተረድቷል። መማር ከማወቅ ያልፋል፣ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ማወቅና ክርስቶስ ኢየሱስን ማወቅ ልዩነት እንዳላቸው መቼም ግልፅ ነው። ስለ ክርስቶስ የሰማና የተረዳ አንድ አይደለም። አብዛኛው ሰው ስለ ጌታ ብዙ የሰማ ግን ጥቂት እንኳ መማር ወይም መረዳት ያልቻለ ነው። መማር የሌለበት መስማት ጥቅም የሌለው ከንቱ ድካም ነው።

መማር ማለት የተነገረውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ እርምጃ መውሰድ ማለት ነው።  ሐዋርያው ተምሬአለው ሲል በኑሮ በተግባር  ያለፈበት እንጂ ከእውቀት አንፃር አይደለም። ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው አልፋ ኣሜጋ መድሃኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ ዮሐንስ በምዕራፍ 2 በቁጥር 9 ላይ ዮሐንስን ለሰምርኔስ  ቤተክርስቲያን እንዲፅፍ በራእይ እንደነገረው

<< መከራህንና ድህነትህን አውቃለው >>

እንደ ጌታ ኢየሱስ መከራን በመቀበል በድህነት ውስጥም ያለፈ ማንም የለም። ጌታ ይህን ጉዳይህን አውቃለው ሲል በዛ ነገር ውስጥ በሕይወት ማለፉንም ጭምር እንጂ በእውቀት ደረጃ ብቻ አይደለም። (ዕብ 2፥18, ዕብ 13፥12, 1ኛ ጴጥ 4፥1-2, ፊሊጵ 2፥7, 2ኛ ቆሮ 8፥9) መማር በመተግበር የሚገለፅ አልፈነው የምናወራው እንጂ ሰምተነው የምንገነዘበው አይደለም።

<<የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል>> ብዙ ጊዜ እንሰማዋለን ነገር ግን ተግባር ላይ ሲመጣ ግን ጭራሽ ትዝም የማይለን ብዙዎች ነን። ክርሰትና ከባድ የሚሆንብንም ቃሉን በሰማነው ልክ በሕይወታችን ተግባራዊ ስለማናደርገው ነው። እንደኔ እንደኔ  ትልቁ የክርስቲያን ፈተና በኑሮአችን የሚገጥመንን ፈተና በቃሉ ያለመመዘን ችግር ነው። <<የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል>> የሚለው ቃል ለሁሉም ክርስቲያን አዲስ አይደለም ነገር ግን ተግባር ላይ ብዙዎቻችን የምንፈተንበት ጉዳይ ነው። ሰው መስራት አለበት በሰራውም ደግሞ መጠን ማግኘት አለበት እዚህ ላይ ጥያቄ የለኝም ነገር ግን የሰው ልጅ በኑሮ ከሚያገኘው ሀብት ንብረት በጨመረ ቁጥር አለመርካቱም ባገኘው መጠን እየጨመረ መሄድ የለበትም። የምንፈልገው ከሚያስፈልገን ካለፈ አደጋ ይሆንብናል።

ተወዳጆች ባለን ነገር ረክተን ተጨማሪ ለማግኘት መስራት እጅግ መልካም ነው። ብዙ ኖሮን ምኞታችን ግን ከበለጠ ወይም ካመዘነ  <<የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል>> እንዴት ማለት እንችላለን? ያለን ከበቂ በላይ ሆኖ ሳለ መስገብገብ ያለንን ያሳጣል ምክንያቱም የምኞት ክፋቱ ባለን ነገር  እንዴት መጠቀም እንዳለብን እንኳ እንዳንችል አርጎ ያሳውራልና።

ለኑሮ የሚያስፈልገን ምን ያህል እንደሆነ ካላወቅን ባለን ነገር አጣጥመን መጠቀም አንችልም። ያለንን ነገር እንኳን ለሰው ለራሳችን እንኳ በማይጠቅም መልኩ እናባክነዋለን። ስለዚህ ያለንን እንወቅ ባለንም እንርካ ያን ጊዜ ያለንን እንደሚበቃን እናውቃለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ የእውነተኛ እርካታ ምንጭ ጌታ ኢየሱስ አለን። እንስራ አስትቶ ደስታ የሚሞላ አንዳችን የሌለን ስንሆን ሁሉ እኛ ሆኗል የሚያስብል ጌታ ይባረክ። እርሱ ብቻ እስከ ዘላለም ከበቂ በላይ ነው።

No comments:

Post a Comment