ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።
1ኛ ቆሮ 15፥22
የሰው ልጅ አስቀድሞ ሲፈጠር ዘላለማዊነትን ከእግዚአብሔር ተሰጥቶት ነበረ፡፡ ሰው ደካማ ሆኖ በመገኘቱ የፈጣሪውን ትዕዛዝ ባለመጠበቁና በማሳዘኑ የተነሳ ዘላለማዊ መሆኑን አስቋርጦ ነበረ፡፡ ቋሚ የነበረው በገዛ ስራውና እምነት በማጉደሉ በሞት ቅጣት የመኖሪያ ገደብ መጣበት፡፡
ታዲያ የሰው ልጅ ምንም እንኳ በገዛ ፈቃዱ ወዶና ፈቅዶ አምላኩን ቢበድልም እግዚአብሔር ግን በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ (ኤፌ 2÷4) የሰውን ልጅ ከፍጥረቱ በሙሉ አክብሮና አልቆ በራሱ መልክና አምሳል ስለፈጠረው የአሳቹ የዲያብሎስ ተገዥ ሆኖ እንዲቀር አልወደደምና ለትዕዛዝ ተላላፊው አዳም የመዳን ተስፋ ተሰጠው እርሱም የዓለምን ኋጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ (ዮሐ 1÷29) የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
እግዚአብሔር እኛን ሲፈጥረን እንዳችን ከአንዳችን እንዳንመሳሰል አድርጎ ነው፡፡ ሁላችንም የየራሳችን መልክና ገጽታ እንዲኖረን አድርጎ ነው የፈጠረን፡፡ ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ፍትሃዊ አይደለም አያስብልም ምክንያቱም የሁላችንንም ልዩነት አንድ አካል ወደምንሆንበት ወደ ልጁ ህብረት ጠርቶናልና (1ኛ ቆሮ 1÷9) ለዚህም አንድያ ልጁን እስከማይራራ ድረስ ለሞት አሳልፎ ሰቷልና፡፡ የሰው ልጅም ትልቁ ድል በጌታ የመሆኑ ጉዳይ የሆነውም ለዚህ ነው፡፡ የቱንም ያህል የአሰተሳሰብም ሆነ߹ ሌላ ልዩነት በመካከላችን ቢኖርም በዚህ ልዩነት ውስጥ ተስማምተን በፍቅር እንድንኖር ቃሉ ይነግረናል (ሮሜ 12÷18)፡፡ ፍቅር ነውና ያዳነን፡፡
እኛ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች ተሽለን የምንታይበትን ነገር እንፈልጋለን፡፡ ሰዎች በአትኩሮት እንዲመለከቱን ከመፈለጋችን የተነሳ እይታ ውስጥ ለመግባት ብዙ እንጥራለን ነገር ግን እግዚአብሔር እንደሚያየው ሰው አንኖርም፡፡ በሰው ፊት እንጂ በእርሱ ፊት ለመኖር አናስብም፡፡ ለምድራዊ ሕይወት ብዙ እንለፋለን የሰማያዊውን (ዘላለማዊውን) ግን በዳተኝነት እንኖራለን፡፡ ለስጋዊ ሕይወት የምንደክመውን ያህል ለመንፈሳዊ ሕይወት እምብዛም ነን፡፡ ለዚህ ነው እግዚአብሔር የሰው ልጅ የልቡ ሀሳብና ምኞት ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ ተብሎ የተጻፈው ዘፍ 6÷5፡፡
የሰው ልጅ ውድቀት በአዳም አለመታዘዝ እንደመጣና (ዘፍ 3÷17 ) ደሞዝ የሆነውን ሞት ለትውልዱም ጭምር ደረሰበት ሮሜ 5÷12፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ገዢ እንደመሆኑ በቃሉ በኩል እንድናደርገውና ደግሞ እንድንታቀብ የሚከለክል ትዕዛዝ አለው፡፡ ፊተኛው አዳም የተሰጠውን ትዕዛዝ በመተላለፉ በኋጢአት ሲወድቅና ሲራቆት እናነባለን። ነገር ግን ኋለኛው አዳም (ጌታ ኢየሱስ) በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረዶ ለሞትም ይኽውም የመስቀል ሞት የታዘዘ ሆነ (ፊልጵ 2÷8)፡፡
ፊተኛው አዳም በማጥፋቱ ራቁቱን ሲሆን (ዘፍ 2÷25) ኋለኛው ግን ሁላችንን ስለ ማጽደቅ ያለ ኋጢአቱ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ እርቃኑን ሆነ (ሉቃ 23÷34)፡፡
ፊተኛው አዳም ባለመታመኑ በእርሱ በኩል ኋጢአት በሰው ልጅ ላይ በሙሉ ነገሰ ነገር ግን ቅዱስና ጻድቅ ያለ ተንኮልና ነውር በንጽህና የኖረው ከኋጢአተኞችም የተለየ ኋለኛው አዳም በመስቀል ላይ በሰራው ስራ ነውራችንን ሸፈነ፡፡ ፊተኛው አዳም የስራውን ደሞዝ ወስዶ ለትውልዱም የክፋት ስራውን አጋራ ኋለኛው አዳም ግን ስለ በደላችን ሞቶ ስለ ጽድቃችን ከሙታን ተነሳ፡፡
በፊተኛው አዳም የሁላችንም እጣ ፈንታ ሞት ሲሆን እንደ እግዚአብሔር ያለ ይቅር ባይ የለምና በልጁ በኢየሱስ በኩል ያጣነውን የዘላለም ሕይወት መስጠት ነው (ሮሜ 6÷23)፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችንም ይህን በአጽንሆት ይነግረናል በፊተኛው አዳም ምክንያት እግዚአብሔር በሞት ሲቀጣን ነገር ግን በኋለኛው አዳም የዘላለም ሕይወት ሰጠን፡፡ እውተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኽውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት (ዮሐ 17÷3)፡፡
ውድ እንባቢያን ከሰው የምንጠብቀው አንዳች ነገር እንዳይኖር አርጎ ጌታ ኢየሱስ ጽድቅን አድርጎልናል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው በእግዚአብሔር ፍቃድ ላይ መመስረት ብቻ ነው እርሱም እርሱ በላከው በልጁና በሰራው ስራ ማመን ነው፡፡ ይህን መቀበል ላመነ ሰው ቀላል ነው ነገር ግን እንዴት የዚህን ያህል ይቀላል በማለት ብዙዎች ለመቀበል ተቸግረዋል፡፡ በፊተኛው አዳም የመጣውን ኩነኔ ያለማቅማማት ተቀብለው ሲኖሩ በሚበልጥ የረዳንንና ሌላ ስራ ሳያስፈልግ ዘላለም በሚያድን የኪዳን ደም የገዛንን የኢየሱስን የማዳን ስራ ግን አይቀበሉም፡፡
ቅዱስ ቃሉ በተደጋጋሚ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት እንደሆነ ይነግረናል ከዚህ የሚበልጥ ነገር ከየት ይምጣ?፡ ግልጽና ጥርጥር በማያስነሳ መልኩ እንዲህ ይላል እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፡፡ (ዮሐ 6÷47) የእግዚአብሔር ቃል ሊነግረን በፈለገው መጠን በቃሉ እንድናምን የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ህብረት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።
No comments:
Post a Comment