Monday, 8 November 2021

ተሀድሶአዊ የወንጌል እንቅስቃሴን በወንጌል የማዳን ጥሪ

 


የተሀድሶ ቤተክርስቲያን የተነሳባትን ነፋስ ንጹዉን ወንጌል ሰባኪነቷን ጥላሸት የሚቀቡባት ላይ እንደ ቃሉ የሆነ አጸፋዊ መልስ ልትሰጥ ይገባል። በእርግጥ በየአጥቢያው የተደረጉ እንቅስቃሴዎችና የማጽኛ ፕሮግራሞች እንደነበሩ ባውቅም በቂ ነው ብዬ አላስብም። ስለሆነም በሰሞኑ የወንጌል እንቅሳቃሴን የመረበሽ ተግባርን በተመለከተ በጉባኤያት ብቻ ሳይሆን በዚህ ስሟንና ተግባሯን እያቀለሉ በሚያሰራጩቧት በማህበራዊ ሚዲያ ምዕመኗቿም ጭምር ተሀድሶአዊውን የወንጌል እንቅስቃሴን የተከበረውን ስሟንና ስራዋን ኢየሱስን በመስበክና በስሙ የሚመጣውን ማንኛውንም ተግዳሮት ተጋፍጣ በወንጌል እንቅስቃሴ ፊታውራሪ ልንሆን ይገባል።

የዳንበትን ቅዱስን ወንጌል ያለ ሽቀጣ የሰማንበትን ብዙ የሕይወት መስዋህትነት የተከፈለበትን የከበረው የወንጌል እንቅስቃሴ ዛሬ ላይ በተወሰኑ በአገልግሎቱ ውስጥ በነበሩ ሰዎች በግል ባላቸው ፍላጎትና ችግር የተነሳ ወዳልተገባ ስም ማጥፋትና አገልግሎቱን ወደ ማርከስ እንዲሁም ወደ ማቃለል እንቅስቃሴ ውስጥ እንደገቡ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ለእነዚህ ሰዎች ምህረትን እየለመንን ለአገልግሎቱ ደግሞ ብርታት እንዲጨምር መትጋት ይኖርብናል። ስደትና ወታወክ(መበታተን) ሲፈጥር የምናውቀው ወደ ተሻለ አገልግሎት ነውና (ሐዋ 8) አንፍራ።

እናም ይህ መጥፎና አደገኛ ወደ እያንዳንዱ ማህበረ ምዕመናን ቤት እየገባ በተለይም ከቅርብ ጊዜአት ወዲህ ለወንጌል ልባቸውን ከፍተው መሰራት ለጀመሩ ወንድምና እህቶች ልባቸው በብዙ ስለተጎዳና ስለተከፈለ ቤተክርስቲያናትም ሆነ ልጆችዋ እንዲሁም በዚህ የወንጌል እንቅስቃሴ ቃሉን በመስማት ያተረፋችሁ በሙሉ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ከፍ ብሎ የተነሳውን የሰውን ሀሳብ በማፍረስና ለክርስቶስ ኢየሱስ መታዘዝም አእምሮን ሁሉ ወደሚማርክ ዘመቻ ከሁላችሁ እጅግ የማንስ እኔ እንድትገቡ  ላነቃ እወዳለው። 

ወንጌልን ከየትኛው ጊዜ በበለጠ ሊሰበክ ይገባዋል እግዚአብሔርም በነገር ሁሉ በእርግጥ ይረዳናል። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። (ዕብራውያን 4፥16)

ለአገልግሎት ነውን?

የኢየሱስ የክብሩ ወንጌል የሚሰበከው ወንጌሉ ራሱ በሚሰጠው አቅምና ጸጋ ነው። አሁን አሁን እያየን ያለነው ከጸጋው ውጪ በውሸትና በማስመሰል ወንጌል እንሰራለን የሚሉ መበራከታቸው ነው። ወንጌል ቀጥተኛ መንገድ ይፈልጋል ይህም ኢየሱስን ብቻውን በመግለጥ በጨለማ ላሉት ብርሃን እንዲበራላቸው ወንጌሉ ራሱ የሚጠይቀውን መንገድ መከተል። ሐዋርያት በእጃቸው የተቀበሉትን ይህን ቅዱስ ወንጌል ያበዙት በቀጥተኛ መንገድ እስከ ሕይወት መስዋህትነት በመክፈል ነው። በዚህ ሁሉ ግን ወንጌልን ለጥቅማቸውና በግል ፍላጎታቸው ተነድተው እንዳላገለገሉ ለማንም ግልፅ ነው። ለዛም ነው የሕይወት መስዋህተንት ያስከፈላቸው። 

እንደዘመኑ አገልጋዬች ቢሆኑ በአይሁድ መቅደስ ገብተው ራሱን በመሰዋት ለዓለም ያበረከተውን ቅዱሱን ደም በማክፋፋት የኮርማና የበግ ጠቦት መስዋህት እያቀረቡ፣ አይሁድ እንዳይከፋው ኢየሱስ በበረት የተወለደ የዮሴፍ ልጅ ነው እያሉ ወንጌልን እንሰብካለን ቢሉ ዛሬ ላይ ንጹህ ወንጌል  ባላየን ነበር። 

ሰሞኑን በዚህ '' ለአገልግሎት ነው '' በሚል ካባ የተሸፈኑ የተወሰኑ አገልጋዬች የኢየሱስን ብቸኛ የአዲስ ኪዳን መካከለኝነትንና ሊቀካህንነት ዝቅ በማድረግ ፍጡራንን በእርሱ ቦታ በመተካት ወደ ሚነገርበት አገልግሎት ፈቀቅ የማለታቸው  ሚስጢር ይህ ስጋና ደም የፈጠረው የማምለጫና ማታለያ መንገዳቸው '' ለአገልግሎት ነው '' የሚል ከባድ የዓለም መንገድ ነው። 

ኢየሱስ በእነሱ አባባል ለጊዜው ብቸኛ መድኃኒት አይደለም።  ሌሎች ፍጡራንና መላእክት በእርሱ ቦታ ተተክተው ወንጌል ተሸቃቅጦ ይሰበካል፣ የሚያገለግሉት ሕዝብም እንዳይከፋው መዝሙርና ምስጋና ይቀርብላቸውል ለምን? መልሳቸው '' ለአገልግሎት ሲባል ነው ''። 

ሁላችት የተዋጀነበትን ቅዱስ ደም ወደ ጎን በመተው መጽሐፍ ቅዱሳችንም በግልፅና በብቸኝነት የነገረንን (የኢሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻል) የሚለውን ችላ በማለት እልፍ መንገድ እንዳለ ወደሚነገርበት ምኩራብ መግባት ይህም የፈረደበት '' ለአገልግሎት ነው '' የሚል ታፔላ ነው። 

ቦታና ጊዜ የማይወሰንለት በእውነትና በመንፈስ የሚመለከው ጌታ እግዚአብሔርን በሁሉም ስፍራ ሆኖ ፀሎትንና ምስጋናን የሚቀበል ሆኖ ሳለ ከሞቱ በኃላ ወደ ሚዘምርላቸው እንዲሁም እንዲማልዱ ወደ ሚፀለይላቸውና ለእግዚአብሔር የሚደረገውን አምልኮታዊ ስርአት አንዳች ነገር ሳይቀነስባቸው ተጋርተው ወደሚሰጣቸው ድንኳን መግባት ብልሃት የተፈጠረው ይህ '' ለአገልግሎት ነው '' የሚል አመክንዬ ነው።  

ኢየሱስ የሚለውን ስም ብቻውን መጠራት የለበትም ድስት እንኳ ሁለት ጆሮ አለው ብለው ከሚያስቡ ጋር ገብተው ''ኢየሱስ'' ላለማለት ወልድ ብለው መናገር መጀመራቸውን ሳይ ለአገልግሎት ነው? ብዬ ለማሰብ ሞከርኩ በረገጡት ጫማ ራሴን ከትቼ ለማየት ተጣጣርኩ ግን ሊዋጥልኝ አልቻለም። ወልድ ማለት በራሱ ችግር አለው እያልኩ አይደለም ግን ወልድ ያሉት ኢየሱስ ላለማለት እንደሆነ በግልፅ ሳላየው ነው። 

የግድ ለመመሳሰል ዮሐንስ አፈወርቅ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እያሉ ጥሩ ጥሩ የሚመስሉ አባባሎችን እየተጠቀሙ ተሀድሶአዊያንን ላለማስከፋት፣ ተቀባይነት ለማግኘት ኦርቶዶክሳዊያንን ማስደሰት ደግሞም እግዚአብሔርንም ላለመበደል በሚደረግ ፍልሚያ ውስጥ እንዳሉ የተረዱት አልመሰለኝም። 

ከእግዚአብሔር በላይ ይራራሉ ከሚባሉት ከሰው አልፈው ሰይጣንን ከሚያሞነኩስና ከእግዚአበሔር ጋር ሊያስታርቁ ከሚወዱት ጋር ኢየሱስን እንዴት ባለ መንገድ ሊሰብኩት እንደፈለጉ አልገባኝም። ሰው የጎረቤቱን ቤት ሰርቶ ነው እንዴ የራሱን የሚሰራው? ምናለ ብትተዋቸው? የተሀድሶ አገልግሎት በሁለት እግሮቹ እንዳይቆምና ያስተማረቻቸውን አቅፋ ረዥም ርቀት እንዳትጓዝ ካደረጉት አንዱ ምክንያት ሌላ ቤት ላይ ተታኮ የሚደረገው እንቅስቃሴ ነው። እስከ መቼ ነው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ጫንቃ ተላቆ ይህን አገልግሎት ለማስፋት አንድነት የማይፈጠው? 

እረ ስንቱን ልናገር በጌታ.......... በጣም ከገረመኝ ነገር አንዳንዶች በዚህ መንገድ ብዙ ዓመት ያስቆጠሩና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለረዥም ዓመት ተቀጥረው ያሉ ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነ የሚናገሩት ነገር። በዚህ መንገድ የሚከፈል ዋጋ እኔ ሊታየኝ አልቻለም ቅዱሱ መጽሐፍም ይህንን አካሄድ ሲደግፍም ሆነ ሲያበረታታ አላየሁም አልሰማሁም። ዋጋ አለን ካሉም እንደኔ እንደኔ ደሞዛቸውን ይቁጠሩ ደግሞስ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብቻ ለምን ታያቸው? ይህ አካሄድ ለምን መስጂድ አይሰራም? ጂሆቫ ጋርና ካቶሊክ ቤተ እምነት ውስጥስ ለምን አይሞክሩትም? 

ነገ የምናፍርበትንና የማያዋጣንን መንገድ ዛሬ አንጠቀም!