Friday, 30 November 2018

ወንጌል ያንፃልም ያፈርሳልም


" የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን " (2ኛ ቆሮ 10፥5)

ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልን በመታዘዝ መገንባት ያለብንን እንገነባለን አመፅን ደግሞ በዛው ልክ እናፈርሳለን፣ የሰውን ሀሳብ፣ የስጋና ደም ምክክርን በመቃወም እንገለብጣለን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንፈፅማለን። እንደ ሰው አሰራር ወንጌልን የሚሸፍንም ሆነ የሚጋርድ እናፈርሳለን። መጋረጃም ቢሆን እንቀዳለን፣ እንጨት፣ ድንጋይ ኮብልስቶን ቢሆን እንፈልጣለን፣ መቆፈር ያለብን ድረስ ሳንታክት እንቆፍራለን መገለጥ ያለበትን እውነት ሁሉ እንገልጣለን። ወንጌል ያፈርሳል፣ ያወድማል፣ ይበቀላል፣ ይቆርጣል፣ ያስወግዳል፣ ይለያል፣ ገፍቶ ይጥላል ደስ የሚለው ግን በአንፃሩ ደግሞ '' ይገነባል'' ።

አንድ የሚታወቅ የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንመልከት። በዚህ ታሪክ መጀመሪያ ክርስቶስን እናያለን፣ በታሪኩ ውስጥም ክርስቶስን እንመለከታለን፣ በመጨረሻም እንዲሁ ክርስቶስን እናገኛለን። በታሩኩ ተዋረድ ሙሉ ክርስቶስ ይታያል። (በታሪኩ መጀመሪያ መሀል መጨረሻም ኢየሱስ ነው።) በውስጡ active እርሱ ብቻ ነው። ሲጀምር በራሱ ሲሰራም በራሱ አፍርሶም ሲገነባ ራሱ ነው።

በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ውስጥ ጌታ አምስት ነገሮችን አፍርሶ አምስት ነገሮችን ሲገነባ እናነባለን። ታሪኩን ስንዳስሰው ከአንዱ እርከን ወደ ሌላኛው እረከን ሲሸጋገር ክርስቶስ በነዚያ ሁሉ ውስጥ ባለመጥፋት አለ። በአጭሩ ከዚህ ታሪክ የምናገኘው ከክርስቶስ ጋር ትብብር ያለው ነገር ብቻ ነው ሲቆም የምናገኘው አላስፈላጊ ነገሮች ተቆርጠው ሲጣሉ እናነባለን። በስተመጨረሻም እርሱን ብቻ አናገኘዋለን።

ታሪኩን የምናገኘው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራት (በተለመደው አነጋገር የሳምራዊቷ ሴት ታሪክ) ሲሆን ፈርሰው የተገነቡትን በአጭሩ እንመልከት። 

1) ሕዝባዊ ማንነት (በሕዝብና በሕዝብ መካከል ያለውን ግድግዳ)
2) የአባቶች ታሪክ፣ ወግና ቅርፅ (የተወረሰ ፀረ ወንጌል)
3) የግል ማንነት
4) የአምልኮ ስፍራ
5) መንፈሳዊ እይታ

ዝርዝር ሀሳብ:- በቅድሚያ ሙሉውን ታሪክ አንብቡት

1) ሕዝባዊ ማንነት በሕዝብና በሕዝብ መካከል ያለውን ግድግዳ
              " በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት። "
                                              (ዮሐ 4፥4)

ግድ ሆነበት የሚለው የታሪኩ ጀማሬ ነው። በጂኦግራፊካል አቀማመጥ ብንመለከት በሰማሪያ ሊያልፍ  ኢየሱስ የሚያስገድደው ነገር አልነበረም። አይሁድ የሰማሪያን ሕዝብ ላለማየት መንገድ አርዝሞ ይሄዳል እንጂ በዚያ አያልፉም ነበር ምክንያቱም በሰፈሩ ማለፍ በራሱ ያረክሳል ብለው ስለሚያምኑ። ሰማሪያ በአጭሩ የአይሁድ ሕዝብ ጠላት ተደርገው ነው የሚወሰዱት የማንነታቸው ጠላት።

ጌታ ግን ሰማርይ ለመሄድ ባልተለመደ መንገድ ሄዶአል። ሰማርያን ለመርገጥ በአይሁድ ሀጢአት ተደርጎ ስለሚታሰብ እንኳን ግድ ለማስኬድ አይደለም ጭራሽ ለማለፍ አይጠቀሙበትም። ትልቅ የሕዝብ ግድግዳ ነበር። ሁለቱን ለይቶ የያዘ የሕዝብ ማንነት ጥያቄ። ስለዚህ ጌታ ይህን አመለካከት በመጣስ በስፍራው ከ60 ኪሎ ሜትር በላይ ለአንዲት ሴት ግድ ብሎት በመሄድና በመገኘት የነበረውን ልዩነት አፈረሰው። በአይሁድና በሰማርያ ያለውን የሕዝብን ልዩነት በማፍረስ አንድነትን ገነባ።

አንዱ የክራስቶስ ስራ ሁለት አንፃራዊ ውጤት አለው አንድም ማፍረስ ነው አንድም መገንባት ነው። በመካከላቸው የነበረው ጥል መሲሁን ሸፍኖ ነበር ነገር ግን ሁለቱም ተስፋ አድርገው የሚጠብቁት እርሱን ነበር። ተስፋቸው እንኳ አንድ አላረጋቸውም ነበር።

ጌታ ኢየሱስ ጊዜ ለመቀነስ አይደለም በዛ ግድ ብሎት የሄደው መለኮታዊ ተልእኮ (Divine Mission) ነበረው። የሕዝቡን አንድነት የመገንባት ዓላማ ነበረው ማለት በሙሉነት እንችላለን ምክንያቱም እርሱ ያለ ዓላማ ወይም ያለ እቅድ አንድ እርምጃ አይጓዝምና።
ፍርስራሽ አንድ ግንባታ አንድ አትሉም?

2) የአባቶች ታሪክና ቅርፅ የወረስነውን/ፀረ ወንጌል

ጌታ ኢየሱስ ሳምራዊቷ ሴት ወደ ጉድጓዱ እንደመጣች ወደ '' ውሃ አጠጪኝ '' ጥያቄ ገባና ተልእኮውን መፈፀም ጀመረ። (click መሆኗ ነው) ይህ ጥያቄ ወደ ተፈለገው መነጋገር እንዲያመጣ አስጀማሪ ሆና የተደረገች መጠይቅ ናት። (አንድ አናፂ መዶሻ ጥሎ አቀብሉኝ እንደማለቱ ነው) ሳምራዊቷ ግን የመለሰችው ተገቢውን ሳይሆን በሁለቱ ሕዝብ መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳይ ነው። መልሱ ኢየሱስ ከሚፈልገው ጥያቄ ጋር አልተገጣጠመም።

'' አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። " (ዮሐ 4፥9)

ጌታም ሁለት ነገር እንደማታውቅ ነገራት
1) የእግዚአብሔር ስጦታ
1) ውሃ አጠጪኝ ያለሽ ማን መሆኑንስ
ይህን ብታውቂ አጠጣኝ ብለሽ ራስሽ ትጠይቀው ነበር። እርሱ ውሃን የፈጠረ ውሃ ፍለጋ አልመጣም ለዚህም የእሱ ጥማት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር:-

"ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው።" (ዮሐ 4፥34)

ከዚህ በኃላ ነበር መፍረስ የሚገባው ሌላኛው አጀንዳ የተነሳው።

" በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው። "  (ዮሐ 4፥12)

ብዙ ዘመን የተቆጠረውን የአባቶቻቸውን ትውፊት አመጣች። #አባቶቻችን #ቤተሰቦቻቸው #ከብቶቻቸው ከዚህ ጠጡ እኛም እስካሁን ከአንድ ሺ ዓመት በላይ ጠብቀነዋል (ባይፃፍም አባባሏ ወገኛ ነው) የእኛም ዘመን መልክ ይህን ተላብሷል በተለይ በሀገራችን ኢትዮጵያ። ፉከራና ቀረርቶ በዝቷል። ከወንጌል ይልቅ ወግና ስርአት ነግሷል። ከንቱ ትምክህት ተንሰራፍቷል። እንደነዚህ ያሉ መንፈሳዊ ሽፋን ያላቸው ተቃውሞች ለጌታም ተደጋግመውበታል። አይሁድ ኢየሱስን የሚጋፉት በአባቶች ስም ነበርና። አንተ '' ከእከሌ '' ትበልጣለህን እያሉ ነበር ነገር የሚፈልጉት (ዮሐ 8፥53 ተመልከቱ)። ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሚሳነው የለምና ይህንን ከንቱ መታበይ ፍርስርሱን አወጣው። እንዲህ በማለት:-

ኢየሱስም መልሶ። ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። (ዮሐ 4፥13-14)

የአባቶቻቸው ጉድጓድ የሚሰጠው ውሃ ሲጠጣ ያረካ ይሆን ይሆናል ነገር ግን ጊዜአዊ እርካታ ስጋን እንጂ የነፍስ ጥያቄን ሊመልስ አይችልም። የነፍስ መልስ ያለው ጌታ ኢየሱስ ጋር ብቻ ነው። የሚልቀው ወንጌል መጥቶ ሳለ ይህን የሚጋፋ ወግና ስርአት ቆርጦ መጣል ነው እንጂ።
ፍርስራሽ ሁለት አትሉም?

3) የግል ማንነት

አሁን ጉዳዩ ወደ ተልእኮው እየገባ ነው። ርቀት ከነበረው  ወይም ከሕዝብ፣ ታሪክ፣ ትውፊትና ወግ ወጥቶ ጉዳዩ ወደ ግለኝነት መጣ። የነበረው ውይይት ውጫዊ ይዘት ነበረው፤ ውጪውን ጠርጎ ወደ ውስጥ ገባ። የተመካችበት ሁሉ ገደል ከተተው። ኢየሱስ ሲናገር የነበራት፣ አለኝ ብላ የተመካችበት ሁሉ ቀሎ አገኘችው። እጅግ በሚገርም ፍጥነት የነበራትን የሚያስተው እርካታ ፍለጋ ውስጥ ገባች። እንዲህም አለች:-

" ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ አለችው። " (ዮሐ 4፥15)

የዓለሙ ቤዛ አለኝ የምትለውን የሚያስጥል፥ ይጠቅመኛል የምትለውን አቅልሎ የዘላለም በረከት የሚሰጥ ጌታ ነው ስሙ ብሩክ ይሁን።

ይህች ሴት 3 መሰረታዊች ችግሮች ነበሩባት።
ሀ) ሳምራዊነት:- ከላይ በመጀመሪያ የተገለፀው ሕዝባዊ ግለላ። ከአይሁድ ጋር የማትተባበር። ከተናቁ ሕዝብ ወገን በመሆኗ ያለባት ችግር ነው።
ለ) የጋብቻ ችግር:- ለአምስት ጊዜ ያህል ባል ሞቶባታል። ምን ያህል በማህበረሰቡ ተፅህኖ ሊደርስባት እንደሚችል መገመት ቀላል ነው።
ሐ) ሴትነት:- በአይሁድ ልማድ አንድ ወንድ ከሴት ጋር ብቻቸውን ማውራት ያልተለመደና እንደ ነውር የሚቆጠር ነው። ሴትን የማግለል ልማድ እጅግ ክልክል ነበር ለዚህም '' ሴትን ሕግ ከምታስተምር መጽሐፉን አቃጥለው '' የሚል የአይሁድ አክራሪነት አባባል አለ የሚባለው። ይህን ማሳያ ቀጥሎ ታሪኩን ስናነብ ግልፅ ይሆንልናል።

"በዚያም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን። ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም። ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም።"(ዮሐ 4፥27)

በመሆኑም ጌታ እጅግ መልካም ነው ይህን የሴትነት አነሳነትን ከእርሷ ጋር በመሆን አፈረሰው። ሴትን በተመለከተ በትምህርት ሳይሆን በተግባር ከልማድ ወጥቶ ከሴቷ ጋር በመቆም ናደው። ማንነቷ መገንባት ጀመረ። ጌታን አግኝታ ወደ ከፍታ ጉዞ ጀመረች። አዎ ኢየሱስ ሁለንተና ቀዳሽ ነው። አንተ አይሁዳዊ ስትሆን ብላ ንግግር የጀመረችው የጌታ የማንነት  ፀዳል በልቦናዋ መብራት ጀመረና '' አንተ ነብይ እንደሆንህ አያለው አለችው ''
ፍርስራሽ ሶስት አትሉም?

4) የአምልኮ ስፍራችን

ስግደትና ስርአተ አምልኮ ለመፈፀም ብዙ ሰው ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ነበር። በአሮጌው ኪዳን የአምልኮ ቦታ ውስንነት ነበርና (ሐዋ 8፥27 እና ዮሐ 12፥20 ተመልከቱ)።
ጌታ ኢየሱስ ከሴቲቱ ለመጣለት ጥያቄ:-

" አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም። ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። " (ዮሐ 4፥20)እርሱ ግን ከእንግዲህ የሚቀደስ ሰው እንጂ ቦታ እንዳልሆነ በግልፅ መናገር ጀመረ።
ገሪዛንም ሆነ የኢየሩሳሌም የነበረውን የአምልኮ ቦታነት አፈረሰው።  በአንድ ላይ ሁለቱንም አእምሮዋ ውስጥ የተቋጠረውን ገመድ ፈታው። የእውነተኛ የሕያው አምልኮ ምንነት ተናገረ:-

" እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። " (ዮሐ 4፥24)

እግዚአብሔርን ለማምለክ መድከም ቀረ። ጋራና ቁልቁለት፣ ዳገትና አቀበት፤ ሜዳና ተራራ፣ ወንዝና ውቂያኖስ፣ ባህርና የብስ መንከራተት ቀረ። ለወሰኑ ድንበር ለመገኘቱ አጥር የሌለው፣ ሰማይንም ምድርንም ከቦ የሰፈረው አምላክ በእውነት (በእርሱ መገኘት በማመን) በመንፈስ (ሁለንተናዊ ራስን በመስጠት) እንደሚመለክ አበሰረና የነበረውን አፈረሰው።

አንድ መዝሙር ትዝ አለኝ:-
ባንተ መንፈስ የተነካ
ቦታ አይመርጥም የማምለኪያ
ይዘምራል በሄደበት
አያስችለው የሆንክለት።

ፈረሰ መባል ያንሰዋል።
ፍርስራሽ አራት አትሉም?

5) ስለ መንፈሳዊነት ያለንን እይታ

ዘመን ተሻጋሪ በተለይ ለተዛባ አስተምህሮ ለተጋለጠ የሚያሳርፍ ወሳኝ ጥያቄዎች።
=}አሁን የት እናምልክ? ሁሉም ቦታ!
=}መች እናምልክ? ሁሌም በሁሉ! 
=}እንዴት እናምልክ? በእውነትና በመንፈስ!
=}በምን ሕይወት እናምልክ? በክርስቶስ በዳነ ሕይወት።
ሴቲቱ ውስጧ የነበሩት ሁሉ ፈራርሰውባት ግንባታው ሊጠናቀቅ አንድ ነገር ብቻ መስማት ቀርቷታል። ውስጧ ከነበረው መሲህና ከምታየው ኢየሱስ ጋር ይበልጥ ተቀራረበች። ይጠጌ አይነኬ ደርሳለች ማግኘቷ ግን አይቀርም።

''  ሴቲቱ። ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። (ዮሐ 4፥25) አሁን የምትሰማው የዘላለም ሕይወትን የሚያሰገኝ ደሰታ፣ ለዘመናት የጠበቀችው ይነገራት ዘንድ የጓጓችለት ሕያው ዜና።

'' ኢየሱስ። የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት። '' (ዮሐ 4፥26)

መስማት ያለባትን የምስራች ሰማች ከያዕቆብ ጉድጓድ ልትቀዳ የመጣችው ከኢየሱስ ቀድታ እንስራዋን ጥላ ሄደች። ያ እንስራ መጣል ያለበት፣ መተው ያለበት፣ መራቅ ያለበት ከንቱ የአባቶችን ወግ ይመስላል። ያ እንስራ በመንፈሳዊ ሽፋን የተሸፈነ ሃይማኖታዊ ከንቱ ስርአትን ይመስላል። ያ እንስራ ኢየሱስ ሊሸፍን ወይም ሊጋራ ያለን ከንቱ ትውፊት ይመስላል። እረ ወገኖች ይቆርጥላችሁ ዘንድ የሚረዳ ጸጋ አይለያችሁ። አሜን።

እሷም ሕይወት አግኝታ እንስራዋን ጥላ ሄደች እኔም መፃፌን ጨርሼ ጌታዬን በሁሉ አመስግኜ ወደ መኝታዬ አመራሁ።
መልካም አዳር።
ሼር።

No comments:

Post a Comment