ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌ 2፥4-5
Monday, 1 October 2018
በባሪያ ዋጋ
ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን የከፈው ዋጋ እጅግ ውድ ነው። ይህም ፍቅሩን ያሳያል። እርሱ ስለወደደን ስለእኛ ራሱን አዋረደ ዝቅም አለ። ፍቅርን በዝቅታ ያስተማረ ሆኖም ያሳየ እንደ ጌታ ማንም የለም። ያ እስራኤልን ነፃ ያወጣል ተብሎ በቤተመንግስ የተጠበቀው ጌታ ከመንበሩ በመውረድ በከብቶች በረት ተገኘ። ሐዋርያው ጳውሎስ የጌታ ነገር ቢደንቀው እንዲህ አለ:-
እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። (ፊልጵ 2፥6-8)
ሰው አማራጭ በማጣቱ ያለ ፍላጎቱ ዝቅ ብሎ ሊኖር ይችላል ነገር ግን እንደ ጌታ ወዶና ፈቅዶ ዝቅ የሚል ማን አለ? ፍቅር ያላሸነፈው ዝቅታ፣ ፍቅር ያልገዛው ዝቅታ፣ፍቅር ያላንበረከከው ዝቅታ ከንቱ ነው። እርሱ ግን......
በፍቅር ተስቦ ወረደ ለእኛ ሲል
የፍቅሩን ትርጓሜ ገለፀው በመስቀል
ለእኛ ያላረገው ከቶ ምን አለና
አፋችን ዝም አይበል እናቅርብ ምሰጋና። ..... ተብሎ የተዘመረለትም ለዚህ ነው።
ጌታ ኢየሱስ ስለ እኔን እናንተ የዝቅታውን ጣሪያ ነካ። አምላክ ሆኖ ሳለ በባሪያ ዋጋ ተሸጠ። በሙሴ መፅሐፍ እንደምናነበው የአንድ ባሪያ መስፈሪያ ወይም መተመኛ ዋጋ ሠላሳ ብር ነው። ለዚያውም በበሬ ለተወጋ ባሪያ የተተመነ የባሪያ ዋጋ።
" በሬው ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ ቢወጋ፥ የበሬው ባለቤት ሠላሳ የብር ሰቅል ለጌታቸው ይስጥ፥ በሬውም ይወገር። " (ዘጸ 21፥32)
ሰይጣን ወደ ልቡ ሹክ ያለውና ጌታን አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ከሰቃዮች ጋር የተስማማውም በዚህ ዋጋ ነው።
" ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ? እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። " (ማቴ 26፥15)
እኛ አይደለም ራሳችንን ያለንን ነገር (ቁስ) እንኳ ዝቅ አድርገው ሲገምቱብን አንወድም እርሱ ግን በበሬ በተወጋ ባሪያ ሚዛን አስቀመጡት። ዋጋ የማይተመንለት ሂሳብ አወጡለት። ስፍር የሌለውን እርሱ ስለእኛ እጅግ በመዋረድ ዛሬ እኛን እርሱ ባለበት በከፍታ ላይ አስቀመጠን። ጌታ ሆይ እጅግ ተመስገን ስላንተ ማውራት እንድወድ ስላደረከኝ። ስላንተ በእያንዳንዱ ዛሬ ብመሰክር አልጠግብም ይህን መፈለግንም ማደረግንም በእኔ ያኖርክ አባቴ ዘላለም ክበርልኝ።
ምክር:-
1) "ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። " (ገላ 5፥13)
2) " አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ። " (1ኛ ጴጥ 2፥16)
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
amen
ReplyDeleteamen amen amennnnnn
ReplyDelete