አንዳንድ ጊዜ ብዙ ከመጠንቀቅ እና ሕይወታችንን በማስተዋል ከመምራታችን የተነሳ ስኬታማ ወይም ውጤታማ ኑሮ እንዳለን የምንቆጥር ልንኖር እንችላለን። በእርግጥ መጠንቀቅም ሆነ ማስተዋል አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። '' ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል '' (ምሳሌ 2፥11) እንደሚል መፅሐፍ። ነገር ግን ለደረስንበት ደረጃ ራሳችንን ድጋፍ የምናደርግ ከሆነ ተሳስተናል።
እኔ እንደገባኝ በራስ መደገፍን የሚያክል አደገኛና ከንቱ ነገር ያለ አይመስለኝም። የቱንም ያህል ብዙ ነገሮችን ያወቅንና አስተዋዮች ብንመስልም የእኛ ማስተዋል ለመደገፍ የሚያበቃ አይደለም። የእኛ ማስተዋል ከሸንበቆነት አይበልጥም ቆመናል ስንል ወድቀን እንገኛለን።
እስኪ ስንቶቻችን ነን ገና ያልተፈጠን ነገር ሊፈጠር ይችላል ብለን ፍርሃት በፈጠረው በገዛ ፈቃዳችን ተመስርተን ነገሮችን እንዳይሆኑ ያደረግን/የተከላከልን የሚመስለን? ለራሳችን ልክ የሆንባቸው ጉዳዮች ላይ ሰው አለማሳዘናችን እርግጠኞች ነን ወይ? ደግሞም ማስተዋል አለኝ ተብሎ ክርስቲያን ብልጣብልጥ እንዲሆን ተፈቅዶለታል ወይ? ራሳችንን እንጠይቅ
እውነት እውነት እላችኃለው የእኛ ማስተዋል ከእግዚአብሔር ሞኝነት አይበልጥም። '' ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። '' (1ኛ ቆሮ 1፥25)
እኛ ችሎታችንና አቅማችን እጅግ ውሱን ስለሆነ ያለ እግዚአብሔር እርዳታ በማስተዋልና በጥንቃቄ እንኳ ቢሆን አንዳች ልናደርግ አንችልምና ለደረስንበት ማንኛውም ደረጃ ክብሩን ለእርሱ እንስጥ። እግዚአብሔር አደረገልን ማለትን እናብዛ በማንኛውም ሰበብ ክብሩን ለሌላ አንስጥ።
እንዴት እንደሚሠራና ነገሮችን እንደሚያቀናጅ ዝርዝሩንና ስሌቱን ወይም ቀመሩን አናውቅምና ለአሠራሩ ፍፁም እንድንመች ፍፁም እንመነው ፍፁም ይሰራብናል።
ሁሉን ቻይነቱና ሀሳቡም ይከለከል ዘንድ በማይቻል በእርሱ እንደገፍ ባይዋጥልንም የራሳችንን አካሄድ ትተን ፍለጋውን እንከተል! እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና '' የነፋስ መንገድ እንዴት እንደ ሆነች፣አጥንትም በእርጉዝ ሆድ እንዴት እንድትዋደድ እንደማታውቅ፣ እንዲሁም ሁሉን የሚሠራውን ሥራ አታውቅም '' (መክብብ 11፡4-5)
በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ፤ ይህም ለሥጋህ ፈውስ ይሆንልሃል፥ ለአጥንትህም ጠገን። እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር፥ ከፍሬህም ሁሉ በኵራት፤ (ምሳ 3፥5-9)
ቸር እንሰንብት !