Saturday, 6 April 2019

መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት

መጽሐፍ እንደሚል " እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። " (ሮሜ 10፥17) በዚህ መሰረት ካለመስማት የሚጀምር እምነት እንደሌለ እንረዳለን። የወለዱንን ወላጆች ወይም ያሳደጉንን ሰዎች ሃይማኖት በመከተል ልናድግ እንችል ይሆናል ነገር ግን በማስተዋል የእድሜ ክልል ስንደርስ ስለምናምነው እምነት በቂ የሆነ እውቀት ያስፈልገናል። የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ቀጥሎም በማወቅ እምነት እንደሚጀምር ቃሉ በግልፅ ይናገራል። በዘፈቀደ የሚኖር እምነት በእግዚአብሔር ላይ ያለ እምነት ሊሆን አይችልም።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ወደ ጎን ያደረገ ክርስትና ሊኖር አይችልም '' ገንዘብ ላደረገው ሰው፣ እውቀት የሕይወት ምንጭ ነው '' (ምሳሌ 16፥22)። ጥያቄው ግን  '' እውቀት ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም ሳይሆን የያዝነው እውቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይስ ባህላዊ የአባቶች ወግ ወይስ ስርአት? '' የሚለው ነው። በመሰረቱ እውቀት ሁሉ እውነት አይደለም። ከ2000/ከ3000 ዓመት በላይ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣም ሆነ ትላንት የገበየነው እውቀት፣ የሁለቱም ትክክለኛነት ከእግዚአብሔር ቃል አንፃር ሲጣራ እንጂ ያ እውቀት ዘመን ስለጠገበ እውነት ሊሆን አይችልም በአንፃሩም ስለዘገየም ውሸት ሊባል አይችልም። እውቀትን እውነት የሚያደርገው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑ ብቻ ነው።

እግዚአብሔርን በተሳሳተ መንገድ የሚያመልኩት ትክክለኛ እውቀት ያላቸው ሳይሆኑ እውቀት የሌላቸው ናቸው ። ጌታ እንዳለውም '' የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል '' (ማቴዎስ 15፥9)። ከንቱ አምልኮ በሰው ስርአት ያለ እውቀት እግዚአብሔርን ማምለክ ነው።

'' እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፥ ተሰብስባችሁ ኑ በአንድነትም ቅረቡ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ እውቀት የላቸውም '' (ኢሳይያስ 45፥20)።

ያለ እግዚአብሔር ቃል እውቀት ስላሉ ሰዎች መጽሐፍ ሲናገር '' ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአልና '' (ትንቢተ ሆሴዕ 4፥6) እንደሚል ውጤቱ መጥፋት ነው። በመሆኑም በዚህ ሰዓት የእግዚአብሔርን ቃል እውቀት ችላ ብሎ ነገር ግን ራሱን አማኝ አድርጎ እያሰበ ያለ አይሳሳት። " እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? " (ሮሜ 10፥14) ይላልና #በመስማት_ጀምረህ_እመን የዛሬው ምክሬ ነው።

" የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ። " (ቆላ 3፥16)

No comments:

Post a Comment