Tuesday, 4 September 2018

አዲስ ፍጥረት


እውነተኛ ክርስቲያኖች እምነታቸውን በክርስቶስ ያደረጉና የደህንነታቸውም ብቸኛ መንገድ ህግን መፈፀም ሳይሆን በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት የሆኑ እንደሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ይናገራል (ገላ 6፥15) እና (2ኛ ቆሮ 5፥17) 

አዲስ ማለት ፍፁም የተለወጠ ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ይለውጣል (ፊሊጵ 3፥21) እንጂ አያሻሽልም። ይህ መለወጥ መሰረታዊና ከመቅፅበት የሚሆን ምስጢራዊና የማይመረመር መለኮታዊ ስራ ነው። በሰው ካልኩሌሽን የማይሆን በመደመርና በመቀነስ የማይመጣ፣ ጥናትና ምርምር በማድረግ የማይደረስበት፣ የስጋና ደም ምክክር የሌለበት፣ ከሰው እጅ የፀዳ ነው። በምሳሌ ለመግለፅ ያህል:- ከዚህ በፊት አንድ ሰው ሃያ(20) ጃምቦ ድራፍት ይጠጣ ከነበረና በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ አዲስ ማንነት ሲመጣ መጠጣቱን  ያቆማል እንጂ ቀንሶ አምስት(5) ጃንቦ ድራፍት ወደመጠጣት  ይመጣል ማለት አይደለም። በክርስቶስ አዲስ መሆን ማለት ያ አሮጌውን ሰው አስወግዶ አዲሱን መንፈሳዊ ሰውነት መልበስ ነው።

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐ 3፥3 ላይ
" እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። " 
እንዳለው በዚህ ዳግም ልደት ወይም በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት መሆን የግድ ነው።

ተፈጥሮአዊ ማንነትን ትተን የነፍሳችንን አቅጣጫ በመቀየር ክርስቶስን ወደ መምሰል ሕይወት ማቅናት ይኖርብናል። በዚህ ለውጥ ውስጥ የእግዚአብሔርን ድምፅ እንሰማ ዘንድ አዲስ ጆሮ ይሰጠናል (ከምትሰሙት ተጠበቁ ስሚል ቃሉ)፣ እግሮቻችን በቀናው ጎዳና ቃሉን ለመፈፀም ይራመዳሉ፣ ከሕግ በታች ሳይሆን ዓለምን በሞላውና ባጥለቀለቀው በክርስቶስ ፀጋ በመደገፍ እንደ ቃሉ በሕይወት በመኖር የኋላችንን እየረሳን ወደ ፊት መዘርጋት ወደ ፊት.........

በመለወጥ ውስጥ ባለ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ቃል ልንገለጥ ይገባናል። ከእኛ የሚጠበቀው ለዚህ ዓለም የማይመች ወይም የማይስማማ በመሆን አዲስ ፍጥረት መሆናችንን በመግለጥ ለሌሎች መትረፍ ይጠበቅብናል።
በእኛ ውስጥ መፈለግንም ማድረግም የሚሰራ ቅዱስ አባታችን እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ስም በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳንን ፀጋ ያብዛልን።

No comments:

Post a Comment