ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌ 2፥4-5
Tuesday, 18 September 2018
አንድ መካከለኛ
" አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። "
(1ኛ ጢሞ 2፥5)
(1ኛ ጢሞ 2፥5)
ጽድቅ ሆኖልናል!
" ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። "
(ትንቢተ ኢሳይያስ 64፥6)
(ትንቢተ ኢሳይያስ 64፥6)
Tuesday, 4 September 2018
አዲስ ፍጥረት
እውነተኛ ክርስቲያኖች እምነታቸውን በክርስቶስ ያደረጉና የደህንነታቸውም ብቸኛ መንገድ ህግን መፈፀም ሳይሆን በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት የሆኑ እንደሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ይናገራል (ገላ 6፥15) እና (2ኛ ቆሮ 5፥17)
አዲስ ማለት ፍፁም የተለወጠ ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ይለውጣል (ፊሊጵ 3፥21) እንጂ አያሻሽልም። ይህ መለወጥ መሰረታዊና ከመቅፅበት የሚሆን ምስጢራዊና የማይመረመር መለኮታዊ ስራ ነው። በሰው ካልኩሌሽን የማይሆን በመደመርና በመቀነስ የማይመጣ፣ ጥናትና ምርምር በማድረግ የማይደረስበት፣ የስጋና ደም ምክክር የሌለበት፣ ከሰው እጅ የፀዳ ነው። በምሳሌ ለመግለፅ ያህል:- ከዚህ በፊት አንድ ሰው ሃያ(20) ጃምቦ ድራፍት ይጠጣ ከነበረና በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ አዲስ ማንነት ሲመጣ መጠጣቱን ያቆማል እንጂ ቀንሶ አምስት(5) ጃንቦ ድራፍት ወደመጠጣት ይመጣል ማለት አይደለም። በክርስቶስ አዲስ መሆን ማለት ያ አሮጌውን ሰው አስወግዶ አዲሱን መንፈሳዊ ሰውነት መልበስ ነው።
ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐ 3፥3 ላይ
" እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። "
እንዳለው በዚህ ዳግም ልደት ወይም በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት መሆን የግድ ነው።
ተፈጥሮአዊ ማንነትን ትተን የነፍሳችንን አቅጣጫ በመቀየር ክርስቶስን ወደ መምሰል ሕይወት ማቅናት ይኖርብናል። በዚህ ለውጥ ውስጥ የእግዚአብሔርን ድምፅ እንሰማ ዘንድ አዲስ ጆሮ ይሰጠናል (ከምትሰሙት ተጠበቁ ስሚል ቃሉ)፣ እግሮቻችን በቀናው ጎዳና ቃሉን ለመፈፀም ይራመዳሉ፣ ከሕግ በታች ሳይሆን ዓለምን በሞላውና ባጥለቀለቀው በክርስቶስ ፀጋ በመደገፍ እንደ ቃሉ በሕይወት በመኖር የኋላችንን እየረሳን ወደ ፊት መዘርጋት ወደ ፊት.........
በመለወጥ ውስጥ ባለ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ቃል ልንገለጥ ይገባናል። ከእኛ የሚጠበቀው ለዚህ ዓለም የማይመች ወይም የማይስማማ በመሆን አዲስ ፍጥረት መሆናችንን በመግለጥ ለሌሎች መትረፍ ይጠበቅብናል።
በእኛ ውስጥ መፈለግንም ማድረግም የሚሰራ ቅዱስ አባታችን እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ስም በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳንን ፀጋ ያብዛልን።
Monday, 3 September 2018
ሰባቱ ''እኔ''ዎች
ብርሃን ሁሉን እንዲያሳይ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ሁሉ ይጠቀምበት ዘንድ የሰጠው ፀጋ ነው። አልታይ ያለንን ወይም ለእይታ አዳጋች የሆነብንን ነገር ብርሃን በዓይናችን እንድናይ ዋናውን ሚና ይጫወታል። እግዚአብሔር አባታችን እኛን ከመፍጠሩ አስቀድሞ በሰማይና በምድር ላይ አስቀድሞ የፈጠረው ነገር ቢኖር ብርሃን ነው። " እግዚአብሔርም ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ። "
(ዘፍ 1፥3) ለዚህም የሰው ልጅ መልካሙ ነገሮችን በሙሉ በብርሃን ይመስለዋል፡፡ ነገር ግን እርሱን እንድንረዳውና እንድናውቀው የልቦናችንን ዓይኖቻች ለማብራት አንድያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ የዓለም ብርሃን አድርጎ ላከልን።
በተፈጥሮ ፀጋ ካገኘነው ብርሃናት (ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ መብራት፣ እሳት፣ ወዘተ) ተቃራኒ የሆነ ጨለማ ስላለው እነዚህ ብርሃናት ጊዜያዊ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከፀሐይ የሚገኝ ብርሃን ጊዜያዊ እንጂ ቋሚና አስተማማኝ ስላልሆነ አንድ ጊዜ ይበራል ሌላ ጊዜ ደግሞ ይጠፋል፡፡ ምክንያቱም የፀሐይ ብርሃን በቀን በርቶ በሌሊት ጨለማ ይጋርደዋልና በቀንም ደመና ይከልለዋልና፡፡ በተፈጥሮ ሂደቶች የሚገኙት ብርሃን ሁሉ ተቃራኒ ሁኔታ ስላላቸው እውነተኛ ብርሃን ሊባሉ አይችልም።
እግዚአብሔር አምላክ ሙሴን እንዲህ አለው።
በምስክሩ መጋረጃ ውጭ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አሮን ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ያሰናዳው፤ ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ይሁን። በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁልጊዜ ያሰናዳቸው። (ዘሌ 24፥3-4)
ይህ በጨለመ ጊዜ እንዲበራ የታዘዘው ብርሃን የጌታችን የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃንነት የሚያሳይ ሲሆን በጨለማ ለነበርን ለእኝ የበራልን እውነተኛ ብርሃን ነው። መፅሐፍም እንደሚል " ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ " (ኤፌ 5፥8) ። የመቅረዙ መብራት የጨለማው ጊዜ እስከሚልቅ ድረስ እንደማይጠፋ ሁሉ የጌታም ብርሃንነት የማይጠፉና ፍፁም የሆነ ዘላለማዊ ነው። እርሱ ጨለማን ያሸነፈ ለሁሉ የሚያበራ ለዓለም የሚበቃ የማያቋርጥ ስፍራና ጊዜ የማይወስነው የማይጠልቅ ፀሐይ ነው።
መቅረዙ ዘይት የሚይዝና ብርሃን ማብሪያ ያሉት ሰባት ዘንግ ሲኖረው በሰባቱም ቀዳዳዎች ብርሃን ያለማቋረጥ ሌሊቱን በሙሉ ያበራል። ሰባት ቁጥር በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአንድን ነገር ፍፁምነት ወይም ሙሉነት ያሳያል። በበደልና በኋጢአታችን ሙታን በነበርን ጊዜ፣ በሞት ጥላ ውስጥ ሆነን ጨለማ ውጦን ሳለ ለእኛ '' እኔ '' ብሎ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ተፅፈው የምናገኛቸውን የክርስቶስ ኢየሱስ ሰባቱ እኔዎች በጥላነት ያሳያል።
እነዚህ እኔዎች ፍፁም ናቸው። ጨለማ ከቶ የማይችላቸው ተወዳዳሪም ተገዳዳሪም ብሎም ምትክና ተወካይ የሌላቸው ፍፁምና የፀኑ የጌታና የጌታ እኔዎች ናቸው። ይህን ማለት የሚቻለው ከጌታ በቀር ማንም የለም። የመቅረዙ መብራት በጨለማ ወይም በሌሊት እንደማይጠፋ ሁሉ የጌታም እኔዎች በጨለማ ለነበርነው የመጣልን ዘላለማዊ ብርሃን ናቸው። ፀንተን የመቆማችን ምስጢር።
አዎ እውነተኛ ብርሃን ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ በፍቃዱ አሳልፎ የሰጠ የናዝሬቱ ኢየሱስ። አለ ዛሬም የፅድቅ ፀሐይ ባለማቋረጥ የሚያበራ በማያልፍ የሕይወት ኋይል በግርማው ቀኝ የተቀመጠው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ። ፀሐይ በሚበራባት ዓለም እኔ ነኝ እውነተኛ ብርሃን ብሎ የመጣ። በሚያልፍ ብርሃን ውስጥ እንመላለስ ለነበርን ለእኛ የማያልፍ ብርሃን ሆኖ የመጣ። ቀን በርቶልን ማታ የሚጨልምብን በብልጭ ድርግም ውስጥ ለነበርን ለእኛ ዘላለማዊ እውነተኛ ብርሃን የሆነልን ኢየሱስ ስሙ ብሩክ ይሁን።
ታዲያ በእርሱ ብርሃንነት እኛን ልጆቹን የዓለም ብርሃን አደረገን። '' እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ'' ብሏልና (ማቴ 5:14)። ጨረቃ ከፀሐይ ብርሃን ወስዳ እንደምታበራ ሁሉ እኛም በእርሱ ብርሃንነት እናበራለን። የመቅረዙ ዘይቱ ሲሞላ ክሩ በመንደድ ያበራል። ያለ ዘይቱ መቅረዙ አይበራም። ፀጋና እውነትን ተሞልቶ በእኛ ያደረው የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የምክርንና የኋይል መንፈስ፣ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራ የኢየሱስ መንፈስ፣ መንፈስ ቅዱስን እንድናበራ ያደርገናል። በተራራ ያለች ከተማ ብርሃኗ ልትሰወር እንደማይቻላት ሁሉ እኛም የጌታን ብርሃንነት በዓለም ላይ በማብራት በጨለማ ላሉት መፍትሄ ልንሆን ይገባል።
ሰዎች እንቅፋት ሊመታቸው ይችላል ብላችሁ የውጪ መብራት አብርታችሁ ሊሆን ይችላል በጨለማ ውስጥ ያለን ሰው ግን ከመውደቅ አያድነውም። የተፈጥሮ መብራት ምናልባት ከውጪ ወደ ቤት ሊያስገባን ይችል ይሆናል ነገር ግን ከድቅድቅ ጨለማ (ከኋጢአት) ወደ የማይጨልም የነፍስ ብርሃን ግን አያደርሰንም። የውስጥን ጨለማ የገፈፈ የነፍስን ዐይን የገለጠ ብርሃን ኢየሱስ ብቻ ነው። ስሙ ይቀደስ።
ወደ አንድ ታሪክ ልውሰዳችሁ። የተፈጥሮ ብርሃን ብለን ከገለፅናቸው ብርሃን ውስጥ አንዱ እሳት ነው። ይህ የተፈጥሮ ብርሃን እና እውነተኛ ብርሃን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ተገናኝተው ነበረ። ኢየሱስ ለስቅላት በአይሁድ እጅ ተይዞ ሳለ ጴጥሮስ እስከ ሊቀካህት ግቢ ድረስ ተከትሎት ለጨለማው ከተለኮሰው እሳት አጠገብ ነበረ። እሳቱ ውስጥ ከነበረው ብርሃን ይልቅ ኢየሱስ እጅግ የሚልቅ ብርሃን ሆኖ ሳለ ጴጥሮስ የክርስቶስን ብርሃንነት በጊዜው ሊገልጥ አልቻለም። ያ የእሳት ብርሃን አሳይቷቸው አንተ ከእርሱ ወገን አይደለህምን? ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ የዓለም ብርሃን አጠገቡ ቆሞ እርሱን በወቅቱ ሊገልጠው አልቻለም። ለከባድ ፀፀት ዳረገውም።
ከዚህ እጅግ ብዙ መማር አለብን። የእግዚአብሔር ዓላማ የጴጥሮስን ድካም ለመንገር ብቻ ሳይሆን እንድንማርበት ዘንዳ ነው። ወይ አርቴፊሻል ብርሃን ወይ የኢየሱስን ብርሃን አብርተን መኖር? በየትኛውም ሁኔታ ብንሆን እውነተኛውን ብርሃን መምረጥ ይሁንልን። በዚህ ዓለም እኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቃል '' ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ '' እንደሚል በተገኘንበት ቦታ በመንገዳችን ሁሉ በትንሳሄው ብርሃን ደምቀን፣ በሕይወት እንጀራችን ብርሃን ፍንትው ብለን፣ በመልካሙ እረኛ ብርሃን ተመርተን፣ በወይኑ ግንዳችን ብርሃን አድገን፣ በፅድቅ በራችን ብርሃን ገብተን፣ እንደ ብርሃን ልጆች እንመላለስ (ኤፌ 5፥10)። አሜን።
Subscribe to:
Posts (Atom)