ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌ 2፥4-5
Tuesday, 14 August 2018
ከፍተኛ በዓል
ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ (መዝ 81፥2-3)
በዓለማችን ብዙ ዓይነት በዓላት አሉ ደግሞም ይከበራሉ። ነገር ግን ሁሉም ታላላቅ ወይም ከፍተኛ በዓላት አይደሉም። በክርስቲያኖች ዘንድ እጅግ የላቀ በዓል አለ እርሱንም ሁልጊዜ በልባቸው ይዘውት ይዞራሉ። ይህም በዓል እግዚአብሔር በልጁ በጌታ ኢየሱስ ደም የተነሳ የሁላችንንም በደልና ኋጢአት ይቅር ያለበት ነው።
መፅሐፍ ቅዱስ ሲናገር በክርስቶስ መስዋህትነት የእግዚአብሔር ማዳን የጀመረው ወይም የታቀደው በመለኮት ጉባኤ ከዓለም ፍጥረት በፊት ሲሆን (ራእ 13፥8 እና 1ኛ ጴጥ 1፥18-21) በማስመለጥ ተምሳሌነቱ የታየው የእስራኤል ህዝብ ዓለምን ከምትወክለው ከግብፅ ባርነት አስወጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲያስገባ ነው። በመጨረሻም ይህ ማዳን ህያው የሆነው/ የተገለጠው በቀራኒዬ መስቀል ላይ የዓለም ቤዛ ኢየሱስ ቅዱስ ደሙን ሲያፈስ ነው።
እስራኤላዊያን ለብዙ ዘመናት ከነበሩበት ባርነት እግዚአብሔር በራሱ የጊዜ ሰሌዳ ቀጥሮ የሚያወጣበት ቀን አመጣ። ይህ ቀን ለግብፅ ቤት የሀዘን፤ ለእስራኤል ቤት የምህረት ቀን ነበር። እግዚአብሔር በአንድ ሌሊት ሁለት ስራ ሰራ። አንዱም ህዝቡን ከግብፅ አወጣ አንድም ደግሞ ግብፅን በመቅሰፍት መታ።
ለአንዱ ሞት
ለአንዱ ነፃነት
በአንዱ ሌሊት
ታዲያ በግብፅ የሚኖሩ እስራኤላውያን መቅሰፍቱ ባለፈ ጊዜ እንዳያገኛቸው እግዚአብሔር እንዲያደርጉት ያዘዛቸው አንድ ነገር ነበር። ነውር የሌለበትን የበግ ወይም የፍየል ጠቦት ወስደው እንዲያርዱ፤ ከደምም ወስደው በሚገቡበት ቤት መቃኑንና ጉበኑን እንዲቀቡት ነበር። ደሙ በጉበኑና በመቃኑ ያለ ሰው መቅሰፍቱ ያልፈው ነበር። ደሙ በመቃኑና በጉበኑ የሌለ የግብፅ ቤት ግን መቅሰፍቱ ያገኘው ነበር።
እግዚአብሔር ይህን ብቻ አይደለም ለእስራኤል ያደረገው '' በዚያም ቀን እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ከሠራዊታቸው ጋር ከግብፅ ምድር አወጣ። '' (ዘጸ 12፥51) መውጣታቸውን ተከትሎ ምርኮ ሊያደርግ ከኋላ የመጣውን እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠው መፍትሄ የፈርኣንን ሰራዊት ዋጣቸው።
ለአንዱ መንገድ
ለሌላው ሞገድ
ከዚህም የተነሳ ሙሴና የእስራኤል ህዝብ ለእግዚአብሔር እንዲህ ብለው ዘመሩ
'' በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው። '' (ዘፀ 15፥1-3)
እስራኤል ይህን የዘመሩት እግዚአብሔር ያደረገላቸው ትልቅ ስራ ስለነበረ ነው። ይህንን ነብየ እግዚአብሔር ዳዊት በመግቢያ ባለው መዝሙር እንደምናነበው በከፍተኛ በዓላችን ለእግዚአብሔቅ ዘምሩ ከግብፅ ባርነት መውጣታችን ይህ ለእስራኤል ስርአቱ ነውና ብሏል። (መዝ 81፥5)። አዎ ለእስራኤል እንደ ፋሲካ ያለ ከፍተኛ በዓል የለም። ለእኛ ለክርስቲያንስ?
እግዚአብሔር ነውር የሌለበት በግና ፍየል ሰውተው በመቃንና ጉበን ላይ እንዲቀቡ ያዘዘው ደም ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ ደም ያመለከተ ነበር። የእግዚአብሔር በግ የሆነው ክርስቶስ ለእኛ መስዋዕት ሆኖ ደሙን አፍስሶ ከነበርንበት ጨለማ ነፃ መውጣታችን ወደሚደነቅ ብርሃን መምጣታችንን ከሚናገሩ ምሳሌ ዋንኛው ነው ማለት ይቻላል። የኤፊሶን መልእክት ፀሐፊ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው በበደልና በኋጢአታችን ሙታን የነበርን እኛን ክርስቶስ ባፈሰሰው ደም እንዲሁ በፀጋው ሕይወት ሰጠን ስሙ ይባረክ።
ዛሬ እኛ ክርስቲያኖች የቤታችን መቃንና ጉበን ላይ የበግና የፍየል ደም አንቀባም። ይልቁን በልባችን መቃንና ጉበን ላይ የጌታ ኢየሱስን ደም እረጭተናል በመሆኑም ከደሙ ኋይል የተነሳ የእግዚአብሔር ቁጣ ልክ የእስራኤልን ቤት ደሙን እያየ እንዳለፈ ሁሉ የእኛም የዘላለም መቅሰፍት ከእኛ አልፏል።
ዓመት እየጠበቅነው የምናከብረው በዓል ሳይሆን በእያንዳንዱ ዛሬ በተሰጠን የቀን እድል ማዳኑን እያወራን ወደ ፊት የምንዘረጋበት የዘላለም በዓል። ይህ በዓል በፍፁም በሌላ የማይተካና የማይደበዝዝ ሳያቋርጥ እስከ ወዲያኛው እጅግ በልባችን የታተመ ከፍተኛ በዓላችን ነው። በዓል ስል ስርአት አይደለም መለኮታዊ ሙላት እንጂ። ዓለም የማይሰጠን በጌታ ብቻ የሆነ ፍፁም ሰላም፣ መውጣት የሌለበት ፍፁም እረፍት፣ ሀዘን የሌለበት ፍፁም ደስታ፣ ግብዝነት የማያውቀው ፍፁም ፍቅር እረ ስሙ ይባረክ። ማን ይሄን ይሰጣል???
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
tsega yabzlih bro.
ReplyDeleteአሜን ወንድሜ ዘመንህ በኢየሱስ ይባረክ።
ReplyDelete